ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤአይን በመጠቀም በቀላሉ በሚዘጋጁ ቪዲዮዎች ስኬታማ የሆኑ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች
ጂጂ ልክ እንደማንኛውም የማኅበራዊ ሚድያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናት።
ፍፁም ያማረ ፀጉር አላት። ሜካፗን ተቀብታ ከአድናቂዎቿ ጋር ታወራለች። ክሊፖች ታጋራለች። ስትበላ፣ ስትኳኳል፣ ሊፕስቲክ ስትቀባ ትታያለች። አንዳንድ ጊዜ ቆንጅየ ጨቅላ ልጇ ከኋላዋ ይታያል።
ከትንሽ ሰከንድ በኋላ ግን የሆነ ባዕድ ነገር ሊታይ ይችላል።
ከእሳተ ጎመራ የተሠራ ፒዛ ስትገምጥ ሊያይዋት ይችላሉ። አሊያም እንደ አስማተኛ እጇ በያዘችው ነገር በኩል ዘልቆ ሲገባ ይስተዋላል።
ይህ የሚሆነው ጂጂ በኤአይ የተሠራች እንጂ እውነተኛ ባለመሆኗ ነው። ጂጂን የሠራቻት የኢሊኖይ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ ሲሞን ማኬንዚ ናት። ዓላማዋ ደግሞ በትርፍ ጊዜዋ ገንዘብ የሚያስገኝላት ነገር ማምጣት ነበር።
የ21 ዓመቷ ማኬንዚ እና መሰሎቿ እንደ ጉግል ቭኦ 3 ያሉ የተለያዩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ቪድዮ ሠርተው በማኅበራዊ ሚድያ ይለቃሉ።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ በእንግሊዝኛው "ኤአይ ስሎፕ" የተሰኘ ክስተት ማኅበራዊ ሚድያውን እየተቆጣጠረው ነው።
ይህን የሚሠሩ ወጣቶች አስገራሚ የሚባል ስኬት እየተጎናጸፉ ይገኛሉ።
"በአንድ ቪድዮ በአራት ቀናት ውስጥ 1600 ዶላር አግኝቻለሁ" ትላለች ማኬንዚ። "ነው እንዴ አልኩና መሥራት ቀጠልኩ" ስትል ታክላለች።
ጂጂ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ተመልካች አግኝታለች። ማኬንዚም በዚህ ምክንያት ከቲክቶክ ሺህ ዶላሮችን እያፈሰች ነው።
ቲክቶክ ተመልካቾች በሚያገኙት ዕይታ ልክ ይከፍላል። ኤአይን ተጠቅመው ገንዘብ የሚሠሩ ቁጥር ስፍር የላቸውም።
"በአሁኑ ወቅት ይህን የሚሠሩ ሰዎች ቁጥር እየተመነደገ ነው። በቅርቡ የሚቆምም አይመስልም" የምትለው የፔንሲልቬኒያ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጄሳ ሊንግል ናት።
የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው በጥቂት ደቂቃዎች ቪድዮ ሠርተው የሚለጥፉ ሰዎች የተፅዕኖ ፈጣሪዎች ገበያ ላይ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።
አንዳንዶች ኤአይ ማኅበራዊ ሚድያውን እያበላሸው ነው ሲሉ ይከራከራሉ። ሌሎች ደግሞ ከማኅበራዊ ሚድያ ጥቅም የሚያገኙ ታዋቂዎች ብቻ ሊሆኑ አይገባም ባይ ናቸው።
ክፍላቸውን አሰማምረው፤ ዘመናዊ ካሜራ ገጥመው፤ ዓይን በሚስብ አርትኦት ለመቅረብ አቅሙም ሆነ ጊዜው የሌላቸው ሰዎች ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ።
የለመድናቸው ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እየተገፉ ነው?
የማኅበራዊ ሚደያ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሕጋዊ የገንዘብ ማግኛ መንገድ መሆን የጀመረው በቅርብ ዓመታት ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢንዱስትሪው የ250 ቢሊዮን ዶላር ገበያ መፍጠር ችሏል ይላል ከጎልድማን ሳክስ የተገኘው መረጃ።
ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የራሳቸውን ሕይወት፣ ሽርሽራቸውን፣ የቤት እንስሳትን እና ሜክአፕ አጠቃቀማቸውን እያሳዩን ብዙ ተከታዮች ማፍራት ችለዋል።
ኤአይን ተጠቅመው የሚለጥፉ ሰዎች ይህንን ማድረግ ጀምረዋል። እንዲያውም የዓለማችን እውነታ ሳይገድባቸው በጥቂት ደቂቃዎች ነው ይህን የሚያደርጉት።
"ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ሊያስከፋ የሚችል ክስተት ነው" የሚሉት በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የዲጂታል እና ማኅበራዊ ሚድያ ምሑር የሆኑት ብሩክ ዳፊ ናቸው።
የጂጂ ፈጣሪ የሆነችው ማኬንዚ እንደምትለው ቪድዮዎችን ለማውረድ የሚፈጅባት ደቂቃ ጥቂት በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ በቀን ሦስት ጊዜ ትለጥፋለች።
እንደ ካቪያ ሳምባሲቫም ላሉ ሰዎች ይህ የማይቻል ነው። የ26 ዓመቷ ካቪያ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚድያ ገፆቿ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሏት።
የምግብ አሠራር አሊያም የቀን አዋዋል ወይም ደግሞ የሜክአፕ አጠቃቀም ቀርፃ ለመለጠፍ ከጥቂት ሰዓታት እስከ ቀናት ሊወስድባት ይችላል። ገበያ ወጥታ ግብዓት መግዛት፣ የምትቀርፅበትን ቦታ ማመቻቸት፣ ከዚያም ቀርፆ ኤዲት ማድረግ ጊዜ ይወስዳል።
የኤአይ ፈጣሪዎች ይህን አያደርጉም።
"ከዚህ ክስተት ጋር መፎካከር እንችላለን ወይ የሚል ጥያቄ ያጭራል። እኔ ሰው ነኝ። አቅሜ የተገደበ ነው" ትላለች የሰሜን ካሮላይናዋ ካቪያ።
"አንዳንድ ጊዜ ለወራት ሳልለጥፍ የምቆይበት ጊዜ አለ። አሊያም የምችለውን አደርጋለሁ። ከሮቦት ጋር መፎካከር አልችልም።"
ቪድዮ መለጠፍ የጀመረችው ወላጆቿ ቤት ሳለች በኮቪድ ወቅት ነበር። ስትጀምር ስልኳን በፕላስተር ግድግዳ ላይ ለጥፋ ነበር የምትቀርፀው። ቀስ በቀስ ከማኅበራዊ ሚድያ በምታገኘው ገንዘብ ለቪድዮዎቿ የሚሆኑ ቁሳቁስ መግዛት ጀመረች። ተከታዮቿ ለማፍራት ዓመታት ወስዶባታል።
ማኬንዚ በበኩሏ በተለመደው መንገድ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን አስባ እንደነበር አትክድም። ነገር ግን ገንዘቡም ሆነ ጊዜው አልነበራትም። ለዚህ ነው ጂጂን የፈጠረቻት።
"ቤት ያለኝ ጠረጴዛ በመፅሐፍትና ሌሎች ኮተቶች የተሞላ ነው። ለዕይታ የሚማርክ አይደለም። ኤአይን ተጠቅሞ የፈለጉትን ማድረግ የተሻለው አማራጭ የሚሆነው ለዚህ ነው" ትላለች።
እውነተኛው ዓለም በኤአይ ቪድዮ
ማኬንዚ ስትጀምር ጉግል ቪኦ 3 ቻትቦት ላይ ገብታ አንዲት ሴት እንዲፈጥር ጠየቅችው። ልክ እንደሷ ሆና የምትተውን ሴት።
ጂጂ ልክ እንደሷ 21 ዓመቷ ነው። ውብ ቆዳ፣ አረንጓዴ ዐይን፣ ቆዳዋ ላይ ነጠብጣብ ያለባት ባለጥቁር ፀጉር ወጣት።
ቀጥላ ቴክኖሎጂው ጂጂ እንድታወራ እንዲያደርግ ነገረችው። ጂጂ አሁን ቪድዮዎችን የምትጀምረው ኤአይ ነሽ ብለው የሚወቅሷትን አስተያየት ሰጪዎች በመጎንተል ነው። ቀጥላ በሽሙጥ መልክ የሰው ልጅ ሊያደርገው የማይቻላቸውን ነገሮች ታደርጋለች።
ዳፊ እንደሚሉት በዲጂታል መንገድ እውነታን ማስመል ያልተለመደ ባይሆንም ዘንድሮ የምናያቸው ግን እውነት ስለሚመስሉ በፍጥነት የመስፋፋት ዕድል አላቸው።
አንዲት ድመት ማክዶናልድ ውስጥ ስትሠራ ከምናየው ጀምሮ የጥበቃ ካሜራ ላይ የተከሰተ የሚያስመስሉ እውነተኛ ይሁኑ ሐሰተኛ ለመለየት የሚያዳግቱ ቪድዮዎች ይለቀቃሉ። ግን ሁሉም ሐሰተኛ ናቸው።
በቲክቶክ የኤአይ ቪድዮዎችን ሠርተው ከሚለጥፉት እና ብዙ ተከታይ ካሏቸው መካከል አንዱ ዳንኤል ራይሊ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ቢኖሩትም መልኩን አይተውት አያውቁም።
በጊዜ ጎዳና ዓመታትን ወደኋላ ተጉዘው የሚያስጎበኙት ቪድዮዎቹ 600 ሺህ ተከታይና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾች አፍርተውለታል።
"ለወትሮው በሚሊዮን ዶላሮች ወጪ የሚሠሩ ቪድየዎችን በመሥራት ታሪክን መናገር እንደምችል ተገነዘብኩ" ይላል። አልፎም ሌሎች እንዴት መሰል ኤአይ ቪድዮዎችን መሥራት እንደሚችሉ ሥልጠና ይሰጣል።
ጂጂ "ኤአይ ብላችሁ አትጥሩኝ" ትላለች የቲክቶክ ቪድዮዋን ስትጀምር። ይህ ንግግሯ ሽሙጥ ቢሆንም እውነት ነው ብለው የሚያምኑ አሉ።
ሊንግል እንደምትለው እውነተኛ ይሁኑ ሐሰተኛ መለየት የሚያዳግቱ ቪድዮዎች ታዳጊዎች ላይ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ።
"የተሳሳተ መረጃ መሠራጨት ይጀምራል። የማጭበርበር ወንጀልም የበለጠ ይስፋፋል። እርባና የሌላቸው ይዘቶች እንዳሉ ሆነው ማለት ነው" ትለላች።