ቲክ ቶክ በአሜሪካ ላለመታገድ ከባለሃብቶች ቡድን ጋር ስምምነት ፈረመ

የቲክ ቶክ ኩባንያ ባለቤት ባይትዳንስ በአሜሪካ ውስጥ ላለው አብዛኛው ሥራው ከአሜሪካ እና ከዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ጋር አስገዳጅ ስምምነቶችን ተፈራረመ።

የቲክ ቲክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሹ ዚ ቼው ሐሙስ ዕለት ለሠራተኞቻቸው በላኩት ማስታወሻ መሠረት ግማሽ የንግዱ ባለቤትነት በኦራክል፣ ሲልቨር ሌክ እና የኢሚራቲ ኢንቨስትመንት ኩባንያ ኤምጂኤክስን ባካተተ የባለሀብቶች ቡድን የሚተዳደር ይሆናል።

ስምምነቱ ጥር 22 ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን ባይትዳንስ በአሜሪካ የሚያካሄዳቸውን ኢንቨስትመንቶች በብሔራዊ ደህንነት ስጋት ምክንያት እንዲሸጥ ለማስገደድ ዋሽንግተን ለዓመታት ያደረገውን ጥረት ያስቆማል ተብሏል።

ይህ ስምምነት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመስከረም ወር መተግበሪያው ካልተሸጠ በስተቀር እንዲታገድ የሚያደርገውን ውሳኔ ባዘገዩበት ወቅት ይፋ ከተደረገው ስምምነት ጋር የሚስማማ ነው።

በማስታወሻው ላይ ቲክ ቶክ እንደተናገረው ስምምነቱ "ከ170 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን ወሳኝ የሆነ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አካል በመሆን ማለቂያ የሌላቸውን ዕድሎች እንዲያገኙ ያስችላቸዋል" ብሏል።

በስምምነቱ መሠረት ባይትዳንስ 19.9 በመቶ ​​የሚሆነውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን፣ ኦራክል፣ ሲልቨር ሌክ እና መቀመጫውን አቡ ዳቢ ያደረገው ኤምጂኤክስ እያንዳንዳቸው 15 በመቶ ድርሻ ይኖራቸዋል።

በማስታወሻው መሠረት ሌላ 30.1 በመቶ የሚሆነው ከባይትዳንስ ጋር በትብብር የሚሰሩ ባለሀብቶች የሚይዙት ይሆናል።

ዋይት ሐውስ ቪዲዮ እየመረጠ ለተጠቃሚዎች የሚያቀርበውን የቲክቶክ አልጎሪዝም በትራምፕ ደጋፊ ላሪ ኤሊሰን በጋራ የተመሰረተው ኦራክል እንደሚቆጣጠሩት አስታውቋል።

በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ወቅት እአአ በሚያዚያ 2024 የአሜሪካ ኮንግረስ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮችን በምክንያትነት በመጥቀስ መተግበሪያው ለአሜሪካውያን ካልተሸጠ በስተቀር እንዲታገድ የሚያስገድድ ሕግ አጽድቋል።

አሜሪካ የተንቀሳቃሽ ምስል ማጋሪያ መተግበሪያውን ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት በሚል መቀመጫውን ቻይና ካደረገው የመተግበሪያው ባለቤት ባይትዳንስ ኩባንያ ለመቀበል ስትጥር ቆይታለች።

ቲክቶክ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ሥራውን እንዲሸጥ አሊያም እንደሚዘጋ መነገሩ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የመዘጋቱ ዜና ከተሰማ ካለፈው ዓመት ጥር ወር ወዲህ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተፈፃሚነቱን አራት ጊዜ ያዘገዩ ሲሆን በዚህ ሳምንትም የተቀመጠውን ቀነ ገደብ እስከ ታኅሳስ ድረስ አራዝመዋል።

ትራምፕ በመስከረም ወር ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር በስልክ እንደተነጋገሩ እና ስምምነት ላይ እነዲደረስ እንደፈቀዱተናግረዋል።

መሪዎቹ በጥቅምት ወር ፊት ለፊት ከተገናኙ በኋላ የመተግበሪያው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ግልጽ አልነበረም።

የመተግበሪያው ዕጣ ፈንታ በንግድ እና በሌሎች ጉዳዮች መካከል በሁለቱ አገራት መካከል በተፈጠረው ውጥረት የተነሳ ጥላ አጥልቶበት ነበር።

"ቲክቶክ በሰፊው የአሜሪካ እና የቻይና ግንኙነት ውስጥ የድርድር ማዕከል ሆኗል" ሲሉ በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም መምህር የሆኑት አልቪን ግሬሊን ተናግረዋል።

ዋይት ሐውስ በጉዳዩ ላይ ያለውን አስተያየት ሲጠየቅ ቲክቶክን ጠይቁ ብሏል።

ኦራክል እና ሲልቨር ሌክ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ቢቢሲ ከኤምጂኤክስ ምላሽ ለማግኘት ሞክሯል።

በዚህ ውል መሠረት የቲክ ቶክ አልጎሪዝም በአሜሪካ የተጠቃሚ መረጃ መሠረት ዳግም እንዲዋቀር ይደረጋል።

ይህም በመተግበሪየው ላይ የሚደረጉ የመልዕክት ልውውጦች ከውጭ ማጭበርበሮች የጸዱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ነው።

"የቲክ ቶክ አልጎሪዝምን ደህንነቱ በተጠበቀ እጅ ላይ የሚያስቀመጥ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም" ሲሉ ዲሞክራቱ ሴን ዋይደን ተናግረዋል።

ከ300,000 በላይ ተከታዮች እና በመተግበሪያው ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ 'ላይኮች' ያሏት የአነስተኛ ንግድ ባለቤት ቲፋኒ ሲያንቺ፣ የሚመጡት ባለሀብቶች እንደ እሷ ላሉ ሥራ ፈጣሪዎች የሚጠቅም አበርክቶ እንደሚኖራቸው ተናግራለች።

"አነስተኛ የንግድ ድርጅቶች ባለቤቶች ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ተስፋ አደርጋለሁ" ስትል ሲያንቺ ተስፋዋን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ቲክቶክ በአሜሪካ ከሰባት ሚሊዮን በላይ አነስተኛ ንግዶች ምርታቸውን ለማስተዋወቅ እንደሚጠቀሙበት ይናገራል።