ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ብዙ ያልተነገረላቸው አሜሪካ ውስጥ የሚፈጸሙ ያለ ዕድሜ ጋብቻዎች
ፓትሪሺያ ሌን በዩናይትድ ስቴትስ ሚኒሶታ ዳርቻ በምትገኘው በኤደን ፕራሪ ውስጥ ነው ያደገችው። ለብዙዎች አካባቢው ማራኪ የሚባል ቦታ ነው። ለእሷ ግን ከዓለም የተገለለችበትን የልጅነት ጊዜን የሚወክል ነው።
"እኔ እና ወንድሜ በባህል ምክንያት በጣም ተገልለን ነበር። ምንም እንኳን ዋና ከሚባሉ የአሜሪካ ከተሞች በአንዷ ዳርቻ ብንኖርም፣ ሕይወቴ እጅግ ጥብቅ እና የማያወለዳ ነበር" ስትል ሌን ስትል ታስታውሳለች።
ገና ከልጅነቷ ጀምሮ የፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሆነችው ሌን በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ወደቀች። ይህም በ12 ዓመቷ ድጋፍ እንድትጠይቅ አደረጋት።
ቲምን ያገኘችው በዚህ አጋጣሚ ነበር። በዕለቱ "ድጋፍ እፈልጋለሁ" የሚለውን የስልክ ጥሪዋን የመለሰላት እሱ ነበር። ከወራት በኋላ ደግሞ ባሏ ሆነ።
ቲም 25 ዓመቱ ሲሆን በሃይማኖት ትምህርት ቤት ይማራል። ሚስዮናዊ ለመሆን ከሚከታተለው ሃይማኖታዊ ትምህርቱ ጎን ለጎን ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች እርዳታ ሚሰጥ ድርጅት ውስጥ የስልክ ጥሪዎችን በመቀበልም ይሠራል።
ብዙም ሳይቆይ ለመገናኘት ወሰኑ። ከአጭር ጊዜ በኋላ ሌን አረገዘች፤ ለማግባትም ወሰነች። ገና 14 ዓመቷ ነበር።
ሌን በወንጌላዊያን አማኞች ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደገችው። "ጸሎት እንደ እርግዝና መከላከያ እንደማይሠራ ተገነዘብኩ። እርጉዝ ብሆንም እሱን ማግባት አልፈለኩም" ስትል ሌን ታስታውሳለች።
ቲም ምድር ቤት ውስጥ እያለቀሰ ነበር። ሌን ለወላጆቿ ያልተጠበቀውን ዜና ነገረቻቸው። የእናቷ ምላሽ እንደጠበቀችው አልነበረም። "ቤተሰቡን በማዋረድ" ተወቀሰች።
"እናቴ ምንም አላመነታችም። በቤተሰቡ ላይ ላመጣሁት ሐፍረት ሁሉ ተጠያቂው እኔ ሆንኩኝ። ለማስተካከል ያለው ብቸኛው መንገድ ያንን ሰው ማግባት እና ጥሩ ሚስት መሆን ነበር" ትላለች ሌን።
ሕጻኑን በሕይወት ማቆየት ከፈለገች ማግባት ነበረባት።
አባቷ የስምምነት ቅጹን ፈረሙ። ሚኒሶታ ውስጥ በሌን ዕድሜ ማግባት ስለማይፈቀድ ከእናቷ እና ከቲም ፈቃድ ወደሚያገኙበት አካባቢ ጉዞ ጀመሩ።
"ሌላ አማራጭ እንዳለኝ አልተሰማኝም። እሱን ማግባት አልፈለኩም ነበር። ነገር ግን ልጅ ወልጄ ማሳደግ በጣም ፈልጌ ነበር። ጥሩ እናት መሆን እንደምችልም አውቅ ነበር።"
እርግዝናን እንደ ክፍተት
ሌን፣ እናቷ እና ቲም መጀመሪያ ወደ ኬንታኪ አቀኑ። የአካባቢው ባለሥልጣናት ጥያቄያቸውን ውድቅ አደረጉት።
"በፍፁም አሁንም። በጣም ትንንሾች ናቸው" መባላቸውን ሌን ታስታውሳለች። "ትክክልም ነበሩ። በጣም ትንሽ ነበርኩ።"
ከዚያም ወደ አላባማ ተጓዙ። በወቅቱ በወላጅ ፈቃድ ማግባት ትችል ነበር። ላውደርዴል ካውንቲ ደርሰው በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሌን እና ቲም ተጋቡ።
ቬሎ አልለበሰችም፤ ፀጉሯንም በአበባ አላስጌጠችም። እናቷ ብቻ ምስክር ሆና ቀረበች።
"እጅግ በጣም ፈጣን ነበር። እዚያ መሆን አልፈለግኩም። ያንን ሰው አልወደድኩትም። እናቴም በጣም ተናደደች። በጣም አስፈሪ ጊዜ ነበር" ስትል አሁን 58 ዓመት የሆናት ሌን ለቢቢሲ ተናግራለች።
የጋብቻ የምስክር ወረቀቱን ከተቀበለች ከደቂቃዎች በኋላ፣ ከፍርድ ቤቱ ፊት ለፊት ወዳለው መናፈሻ ሄዳ ዥዋዥዌ መጫወት ጀመረች። እናቷንም ሆነ አዲሱን ባሏን ያስቆጣ የልጅነት ስሜት ነበር።
"ማግባት ምን እንደሆነ ከገመትኩት ጋር አብሮ የሚሄድ ነገር አልገጠመኝም" ስትል ሌን ታስታውሳለች። በወቅቱ የእርግዝናዋ የመጀመሪያ ሳምንታት ላይ ነበረች። ስትወልድም ልጇን ለጉዲፈቻ አዘጋጀች።
"የጋብቻ ምስክር ወረቀቱን አልፈረምኩም። ስሜ ቢጻፍበትም መፈረም አልተጠበቅብኝም። እናቴ በእኔ ቦታ ፈርማ ሕይወቴን ለአንድ ወንድ አስረከበች። ጋብቻዎቹ የሚሠሩት በዚህ መንገድ ነው። ሌሎች ሰዎች አሳልፈው ይሰጡናል፤ 18 ዓመት እስኪሞላን ድረስ ማምለጥ አንችልም" ትላለች።
ፓትሪሺያ ቲምን ካገባች በኋላ ባሉት 46 ዓመታት ውስጥ የአላባማ ሕጎች ብዙም አልተለወጡም።
ዛሬም የ14 ዓመት ልጅ ማግባት አይችልም። የ16 ዓመት ልጅ ግን በወላጅ ፈቃድ ማግባት ይችላል። ለጋብቻ ዝቅተኛው ዕድሜ ተብሎ የተቀመጠው ግን 18 ዓመት ነው።
"ተጨማሪ መፍትሔዎች የሉም። ለአካለ መጠን ያልደረሰው ልጅ ብቻውን ሃሳቡን እንዲሰጥ ግዛቱ አይጠይቅም። የፍርድ ቤት ፈቃድም አያስፈልገውም" ሲል ሕጉ ያስረዳል።
በ2025 ዋሽንግተን ዲሲን ጨምሮ 16 የአሜሪካ ግዛቶች ብቻ ለጋብቻ የሚፈቀደው አነስተኛ ዕድሜ 18 ዓመት መሆኑን አስቀምጠዋል።
ይህ የሰብአዊ መብቶች ቡድኖች የሚጠይቁት መስፈርት ነው።
በሌሎች ግዛቶች ውስጥ የትዳር አጋር ከሚሆነው ሰው ማርገዝ፣ ልጅ መውለድ እና የወላጅ ፈቃድን የሚያካትቱ ተጨማሪ መስፈርቶች ተቀምጠዋል።
እርግዝና ዝቅተኛውን የጋብቻ ዕድሜ ለማንሳት እንደ ምክንያት ከሚቀርቡባቸው ግዛቶች አርካንሳስ፣ ኒው ሜክሲኮ እና ኦክላሆማ ይጠቀሳሉ።
ኢኳሊቲ ናው የተሰኘው የፆታ መብቶች ድርጅት ባልደረባ የሆኑት አናስታሲያ ሎው "በሕጋዊ መንገድ አስገድዶ መድፈር ወይም የሕጻናት ጥቃት ተብለው የሚታሰቡ ግንኙነቶችን እና የብዝበዛ ድርጊቶችን የበለጠ ሕጋዊ ከማድረግ ባለፈ አይጠቅሙም" ሲሉ ይከራከራሉ።
እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለጻ በ2025 በዓለም አቀፍ ደረጃ 12 ሚሊዮን የሚሆኑ ልጃገረዶች በየዓመቱ 18 ዓመት ሳይሞላቸው ያገባሉ።
ይህም የልጅነት ጋብቻ ተብሎ የሚገለጽበት የዕድሜ ገደብ ነው። በ2030 ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በሚስማማ መልኩ ድርጊቱ እንዲወገድ ከተፈለገ ጥረቶች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር እንዳለባቸው ድርጅቱ አስጠንቅቋል።
ይህ ልማድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደሆነ ይታወቃል።
በዩናይትድ ስቴትስ በፌዴራል ደረጃ ለጋብቻ የሚፈቀደው ዝቅተኛ የዕድሜ ገደብ አልተቀመጠም። በአገሪቱ ከአውሮፓውያኑ 2000 እስከ 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ300 ሺህ በላይ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች በሕጋዊ መንገድ ተጋብተዋል።
አንዳንዶቹ ገና በ10 ዓመታቸው ያገቡ ሲሆን፣ አብዛኞቹ በ16 ወይም በ17 ዓመታቸው ነው የተዳሩት። አብዛኞቹ ትዳር የመሠረቱት ከአዋቂ ወንዶች ጋር ነው።
"የፌዴራል ሕግ ቢኖር በአሁኑ ጊዜ የሕጻናት ጋብቻን እና በጋብቻ ሽፋን የሕጻናት ዝውውርን የሚፈቅዱ እና የሚያበረታቱ ክፍተቶችን ይዘጋዋል" ሲሉ ሎው ተናግረዋል።
'አሁንም ከብቸኝነት ጋር እታገላለሁ'
ከጋብቻዋ በኋላ በነበሩት ዓመታት ሌን ልጇን ለጉዲፈቻ መስጠት እና ባሏን መፍታትን ጨምሮ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ገጥመዋታል። በኋላም በድጋሚ በራሷ ፈቃድ አገባች።
በአሜሪካ የግዳጅ እና የሕጻናት ጋብቻን ለመዋጋት በሚሠሩ ድርጅቶች መሠረት በዚህ መንገድ የተዳሩ ልጃገረዶች ብዙውን ጊዜ ይገለላሉ። ከትምህርት ቤት የመውጣት ዕድላቸው ከፍተኛ በመሆኑም በባሎቻቸው ላይ የበለጠ ጥገኛ ያደርጋቸዋል።
"ለሁለት ዓመታት ትምህርቴን አቋርጫለሁ። በኋላ ላይ ትምህርቴን ብቀጥልም ግን ተመሳሳይ አልነበረም" ትላለች ሌን።
"ባለቤቴ ጓደኞች እንዲኖሩኝ አልፈቀደልኝም። ብቻዬን ነበርኩ። እስከ ዛሬ ድረስም ከብቸኝነት ጋር እታገላለሁ። እስካሁንም ሰዎችን ማመን አስቸጋሪ ስለሚሆንብኝ በቡድን ከመሆን ይልቅ ብቻዬን መሆን የበለጠ ምቾት ይሰጠኛል" ትላለች።
ምሥጋና ለዚህ ሕይወት ላለፉ እና ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ይሁንና ከአውሮፓውያኑ 2018 ወዲህ 16 ግዛቶች ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለመከልከል ሕጎቻቸውን ቀይረዋል። ነገር ግን ብዙ የሚቀር ነገር አለ።
"[ሰዎች] ይህ የሚከሰተው በታዳጊ አገራት ወይም በተወሰኑ ሃይማኖቶች ውስጥ ብቻ ነው ብለው ያስባሉ። ነገር ግን አይደለም. . . በዩናይትድ ስቴትስም ይከሰታል" ትላለች ሌን።
ባለሙያዎች በበኩላቸው የልጅነት ጋብቻ በአሜሪካ ውስጥ ችግር ነው። ከፆታ መድልኦ ጋር ተዳምሮ የሕግ ማሻሻያውን ለማሳካት አስቸጋሪ እንዳደረገው ያስረዳሉ።
"ለእነዚህ ወንዶች ጋብቻ የወንጀል ክሶችን የማስወገጃ መንገድ ነው። ሕግ አውጪዎች ይህንን እንዳይፈቅዱ እጠይቃለሁ" ትላለች ሌን።
"በ16 ወይም በ17 ዓመት እውነተኛ ፍቅር ነው ያለው ብለው ለሚከራከሩ፤ እውነተኛ ፍቅር ከሆነ ጥሩ። እውነተኛ ፍቅር ከሆነ በ18 ዓመታቸውም ፍቅሩ ይኖራል።"