ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእንግሊዝ እና በዌልስ ዝቅተኛው የጋብቻ እድሜ ወደ 18 ከፍ እንዲል ተወሰነ
በእንግሊዝ እና በዌልስ ሕጋዊ የጋብቻ እድሜ ወደ 18 ከፍ የሚያደርግ አዲስ ሕግ ተግባራዊ ሆነ።
ቀደም ብሎ የወላጅ ፈቃድ ያላቸው ታዳጊዎች በ16 አሊያም በ17 ዓመታቸው ማግባት ይችሉ የነበረ ሲሆን፣ በአካባቢ ምክር ቤት ባልተመዘገቡ ሥነ ሥርዓቶች ታዳጊዎች በዚህ እድሜያቸው እንዳያገቡ የሚከለክል ሕግ አልነበረም።
አዲሱ ሕግ ግን በሕግ በማይታወቁ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶች የሚፈጸሙ የግዳጅ ጋብቻዎች የእድሜ ገደቡን እንዲያከብሩ ያስገድዳል።
ሕጉ ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ ሕጻናት ተገደው እንዳይዳሩ ለመጠበቅ እንደሚረዳ መንግሥት አስታውቋል።
ቀደም ሲል የግዳጅ ጋብቻ እንደ ወንጀል የሚቆጠረው እንደ ማስፈራሪ ያሉ ጫናዎች ሲደረጉ ብቻ ነበር።
ይሁን እንጂ በአዲሱ የጋብቻ እና ሲቪል ጥምረት ዝቅተኛው የጋብቻ እድሜ ሕግ መሠረት፣ በማንኛውም ሁኔታ ሕጻናትን በማስገደድም ይሁን በፈቃዳቸው እንዲያገቡ ማድረግ ሕገ ወጥ ነው።
ይህንን ሕግ በመጣስ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙም እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ እስር ይጠብቃቸዋል።
ዝቅተኛው የጋብቻ እድሜ 16 በሆነባቸው በስኮትላንድ እና በሰሜን አየርላንድ ግን አዲሱ ሕግ ተግባራዊ አይሆንም።
በሰሜን አየርላንድ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ለማግባት የወላጅ ፈቃድ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ በስኮትላንድ ግን ይህም አያስፈልግም።
የሰሜን አየርላንድ ሚኒስትሮች ቀደም ብሎ ዝቅተኛውን የጋብቻ እድሜ ወደ 18 ከፍ ለማድረግ እቅድ እንዳላቸው አስታውቀው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ያለው መንግሥት ይህንን ሕግ ወደፊት ማምጣት አልቻለም።
በጉዳዩ ላይ ዘመቻ ስታካሂድ የነበረችው ፓይዚ ማህሙድ፣ የሕጻናት ጋብቻ ተጎጂ ስትሆን በ17 ዓመቷ በግድ የተዳረችው እህቷ ባናዝም፣ ባሏን ትታ ከወጣች በኋላ ለ“ክብር” የሚፈጸም ግድያ ሰለባ ሆናለች።
ፓይዚ፣ አዲሱ ሕግ በእንግሊዝ እና በዌልስ ተግባራዊ መሆኑ በሕይወቷ ወሳኝ ከምትላቸው ቀናት ውስጥ አንዱ መሆኑን ተናግራለች።
“ሕጉ በጣም ስሜታዊ አድርጎኛል። ምክንያቱም የሕጻናት ጋብቻ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ በደንብ አውቃለሁ” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
“እኔም በዚሁ ችግር ውስጥ አልፌያለሁ። እህቴም በዚሁ መንገድ ስታልፍ ተመልክቻለሁ ። በዚህ ምክንያት በርካታ ሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን እስከፊ ተፅዕኖ ተመልክቻለሁ” ብላለች ፓይዚ።
“የሕጻናት ጋብቻን ለማመለጥ ሲሞክሩም ቅጣታቸው ሞት ነው። በእህቴ ላይ የሆነውም ይህ ነው” ብላለች።
ፓይዚ ጨምራም ለውጡ ከዚህ በኋላ ልጆች ያለ ዕድሜ ጋብቻን ሲጋፈጡ ወላጆችንና ማኅበረሰቡን የመሞገት ኃላፊነት የልጆች እንደማይሆንም ተናግራለች።
እንደ አውሮፓውያኑ 2021 የግዳጅ ጋብቻ የሚመለከተው የመንግሥት ክፍል እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ 118 ተጎጂዎች ድጋፍ ሰጥቷል።
ይሁን እንጂ ተሟጋቾች ሌሎች በርካታ ተጠቂዎች ድጋፍ ላይደርሳቸው ይችላል በሚል አሃዙ የችግሩን ስፋት አያሳይም ይላሉ።
የግዳጅ ትዳር ተጎጂዎችን የሚረዳው ግብረ ሰናይ ድርጅት ካርማ ኒርቫና፣ አዲሱ ሕግ የሕጻናት ጋብቻን ለመለየት እና የሚሰጠውን ጥቆማ እንደሚጨምረው ተስፋ አድርጓል።
የድርጅቱ ዳይሬክተር ናታሻ ራቱ፣ “ይህንን ድብቅ የሆነውን ጥቃት ለማስቆም ሕጉ ትልቅ ስኬት ነው። ለጥቃት ተጋላጮችም ጥበቃ ያዳርጋል” ብለዋል።
የፍትሕ ሚኒስተሩ ዶሚኒክ ራብ በበኩላቸው “ልጆችን ያለ እድሜያቸው እንዲያገቡ የሚያደርጉ ሰዎች አሁን ሙሉ በሙሉ በሕግ ይጠየቃሉ” ብለዋል።
ሆኖም የሮማ የድጋፍ ሰጪ ቡድን ሚሃይ ቢካ፣ የተደረገው ለውጥ ለሕብረሰተቡ እና ሕግ አስፈፃሚዎች እንዴት እንደሚተላለፍ ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ቢካ “የሮማ ማኅበረሰብ ጋብቻ የሚለውን ቃል ለተቃራኒ ጾታ ግንኙነትም ይጠቀሙበታል በመሆኑም ባህልን አለመረዳት ለዚህ ሕግ መገዛት በማይገባቸው ቤተሰቦች ላይ ተፅዕኖ ሊያደርስ ይችላል” ሲሉም ያስረዳሉ።
በመሆኑም ቢካ በነበሩ አመለካከቶች ላይ ተፅዕኖ እንዳይኖር ለሮማ ቤተሰቦች ሥልጠና እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የተለያዩ ፓርቲዎች ድጋፍ ያለው ይህ ለውጥ፣ ወደ ፓርላማ የቀረበው በወግ አጥባቂው የፓርላማ አባል ፖሊን ላታም ነበር።