የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግጭት ቀስቅሰዋል ሲሉ ወቀሱ

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የተናገሩት የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ "አንዳንዶቹ የተገደሉት ሰብአዊ ባልሆነ፣ ጭካኔ በተሞላው መንገድ ነው" ብለዋል። ለሰዎቹ ሞት አሜሪካን ተጠያቂ አድርገዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የአውሮፓ መሪዎች ትራምፕ ግሪንላንድን በታሪፍ ማስፈራራታቸው ተቀባይነት የለውም አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በግሪንላንድ ምክንያት ስምንት አጋር ሀገራት ላይ ታሪፍ መጣላቸውን የአውሮፓ መሪዎች ተቃወሙ።

    የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር የትራምፕ እርምጃ “ፍፁም ስህተት” ነው ሲሉ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማኽሮን በበኩላቸው “ተቀባይነት የሌለው” ብለውታል።

    ትራምፕ ከዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ዩኬ፣ ኔዘርላንድስ እና ፊንላንድ የሚመጡ ምርቶች ላይ 10 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል።

    ታሪፍ ከሚመጣው የአውሮፓውያኑ ወር ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን በግሪንላንድ ጉዳይ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ወደ 25 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ተሰምቷል።

    ትራምፕ የዴንማርክ ክፍል የሆነችው ራስ ገዟ ግሪንላንድ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አስፈላጊ ናት ይላሉ። ግሪንላንድ ለመቆጣጠር ኃይል ሊጠቀሙ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት የጣሉትን ታሪፍ ተከትሎ የአውሮፓው ኅብረት እሑድ ከሰዓት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።

    በተያያዘ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዴንማርክ እና ግሪንላንድ የአሜሪካን እርምጃ ተቃውመው ለሰላማዊ ሰልፍ አደባባይ ወጥተዋል።

    የሕዝብ ቁጥሯ በቅጡ 60 ሺህ የማይሞላው የዓለማችን ግዙፏ ደሴት በማዕድናት የበለፀገች ስትሆን በሰሜን አሜሪካ እና በአርክቲክ መካከል የምትገኝ ስትራቴጂካዊ ስፍራ ናት።

  2. በጓቲማላ ታራሚዎች እስር ቤቶችን ተቆጣጥረው 46 ሰዎችን አግተው ያዙ

    በጓቲማላ አመፅ የቀሰቀሱ ታራሚዎች እስር ቤቶች ተቆጣጥረው 46 ሰዎችን አግተው መያዛቸውን የሀገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ።

    የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ማርኮ አንቶኒዮ ቪሌዳ ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ የሞቱ ወይም የተጎዱ ሰዎች የሉም ቢሉም የእስር ቤቱ ሠራተኞች መታገታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ በሶስት እስር ቤቶች የተነሳው አመፅ ባሪዮ 18 በተባለው የወንበዴ ቡድን የተቀነባበረ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

    ቡድኑ አመፅ የቀሰቀሰው መሪው የተሻለ ሁኔታ ወዳለበት እስር ቤት ለመዘዋወር ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ መሆኑ ተሰምቷል።

    በማዕከላዊ አሜሪካዊቷ ሀገር የሚገኘው ሪኖቫሲዮን 1 የተሰኘ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት እስር ቤት በፀጥታ ኃይሎች ተከቦ እንደሚገኝ ታውቋል።

    የእስር ቤት ልብስ አድርገው ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ ታራሚዎች የእስር ቤቱን ማማ መቆጣጠራቸውም ተነግሯል።

    በጓቲማላ ከዚህ ቀደም ታራሚዎች በቀሰቀሱት አመፅ የእስር ቤት ጠባቂዎችን አግተው እንደነበር ይታወሳል።

  3. በኢራን ተቃውሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ አረጋገጡ

    በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን በይፋ የተናገሩት ጠቅላይ መሪው "አንዳንዶቹ የተገደሉት ሰብአዊ ባልሆነ፣ ጭካኔ በተሞላው መንገድ ነው" ብለዋል። ለሰዎቹ ሞት አሜሪካን ተጠያቂ አድርገዋል።

    መቀመጫውne አሜሪካ ያደረገው የኢራን መብት ተሟጋች ተቋም 'ሂውማን ራይትስ አክቲቪስትስ ኒውስ ኤጀንሲ' እንደገለጸው፤ ኢራን በተቃዋሚዎች ላይ በወሰደችው የኃይል እርምጃ የ3,090 ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል።

    ሌሎች የመብት ተሟጋቾች የሟቾችን ቁጥር ከፍ ያደርጉታል። ኢንተርኔት ከተቋረጠ ቀናት በማለፋቸው ትክክለኛውን ቁጥር ለማጣራት አዳጋች ሆኗል።

  4. ሀገራት በትራምፕ "የሰላም ቦርድ" ውስጥ ለመካተት 1 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ እንደሚጠየቁ ተሰማ

    የትራምፕ አስተዳደር ፕሬዝደንቱ በሚያቋቁሙት የሰላም ቦርድ ውስጥ ተሳታፊ መሆን የሚፈልጉ ሀገራት 1 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ እንደሚፈልግ ብሉምበርግን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ ዘግቧል።

    ብሉምበርግን የሰላም ቦርዱን ረቂቅ አዋጅ ተመልክቶ እንደዘገበው የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያው ሊቀ-መንበር ሆነው የሚያገልግሉ ሲሆን አባል ሀገራት በተራ ሊቀ-መንበር ሆነው ከሶስት ዓመት ያልበለጠ ጊዜ ያገለግላሉ።

    ዋይት ሐውስ ዘገባውን “አሳሳች” ሲል የወቀሰው ሲሆን “የሰላም ቦርዱን” ለመቀላቀል የሚያስፈልግ “አነስተኛ ክፍያ” የለም ብሏል።

    “ለሰላም፣ ለፀጥታ እና ለብልፅግና ቁርጠኝነት ለሚያሳዩ አጋር ሀገራት ቋሚ አባልነት እንሰጣለን” ይላል ዋይት ሐውስ በኤክስ ገፁ የለቀቀው መረጃ።

    ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና ልዩ መልዕክተኛቸው ስቲቭ ዊትኮፍ አሜሪካ የሰላም ቦርድ ለማቋቋም ሐሳብ እንዳላት በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው አጋርተዋል።

    ባለሥልጣናቱ ቦርዱን ለመቀላቀል ሀገራት ክፍያ ይከፍሉ እንደሆን የሚጠቁም ነገር አልጻፉም።

  5. የኡጋንዳው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ከቁም እስር ማምለጡን አስታወቀ

    በኡጋንዳ የተካሄደው ምርጫ ውጤት ሊገለጽ በተቃረበበት ጊዜ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ቦቢ ዋይን በቤቱ ውስጥ ከተፈጸመ የቁም እስር ማምለጡን አስታወቀ።

    የፖለቲከኛው ልጅ እና የፓርቲው አባላት ዋይን በፖሊስ ተገድዶ ከቤቱ በሄሊኮፕተር ወዳልታወቀ ቦታ ተወስዷል ካሉ በኋላ ፖሊስ ክሱን ያስተባበለ ቢሆንም፣ ቦቢ ዋይን ግን ማምለጡን ተናግሯል።

    በምርጫውን የፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ዋነኛ ተፎካካሪ የሆነው ፖለቲከኛ እንዳሳወቀው የፀጥታ ኃይሎች ሌሊት በቤቱ ላይ ከፈጸሙት ወረራ ማምለጡን እና ሚስቱ እንዲሁም ሌሎች ዘመዶቹ ግን በቁም አስር ላይ ናቸው ብሏል።

    እስካሁን ባለው ውጤት ሙሴቪኒ በኡጋንዳ መሪነት የቆዩበትን ጊዜ ወደ 40 ዓመታት ለማድረስ የሚስችላቸው ነው በተባለ ውጤት እየመሩ ነው።

    ሐሙስ በተካሄደው ምርጫ ከ94 በመቶ ከሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች በተገኘ ውጤት ሙሴቬኒ 72 በመቶ ድምጽ ሲያገኙ፣ ዋይን ማስረጃዎችን ሳያቀርብ ማጭበርበሮች ነበሩበት ብሎ በተቸው ምርጫ 24 በመቶ ድምጽ ማግኘቱ ተነግሯል።

    ቅዳሜ ጠዋት የፖሊስ ቃል አቀባይ ለጋዜጠኞች ቦቢ ዋይን ከሚስቱ እና ከዘመዶቹ ጋር ቤታቸው ውስጥ መሆናቸውን ገልጸው፣ ከእውነት የራቀ ክስ እያሰሙ ነው በማለት ቤት የደኅንነት ጥበቃ የሚደረግለት በመሆኑ እንቅስቃሴው የተገደበ ነው ብለዋል።

  6. "ጦርነት ውስጥ መግባት አንፈልግም፤ ወንጀለኞችን ግን አንምርም" የኢራኑ መሪ

    የኢራኑ የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉ ነገር ግን ለወንጀለኞች ምህረት እንደሌላቸው ተናገሩ።

    በኢራን ለሦስት ሳምንት የተካሄደውን ተቃውሞን በተመለከተ መሪው በዓል ለማክበር ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር “አገሪቱን ወደ ጦርነት የማስገባት ፍላጎት የለንም፤ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ወንጀለኞችን ግን አንምርም” ብለዋል።

    ጨምረውም "የአሜሪካ ግብ ኢራንን መዋጥ መሆኑን በእርግጠኝነት እናገራለሁ፤ ከአብዮቱ ጅማሬ አንስቶ የአሜሪካ ፍላጎት በኢራን ሕዝብ እና በመሪዎቹ ላይ ያጣችውን የበላይነት መመለስ ነው” ሲሉ ከሰዋል።

    "የሁሉም የአሜሪካ መንግሥታት ፖሊሲ ኢራንን የመሰሉ ነጻ አገራትን የሚታገስ አይደለም። የምዕራቡ መገናኛ ብዙኃን አባላት ከዚህ ቀደም በነበሩ አመጾች ጣልቃ ገብተው ነበር፤ አሁን ግን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እራሱ አመጸኞችን ሲያበረታታ ነበር” ብለዋል ኻሜኒ።

    የኢራኑ መሪ የተቃውሞው ተሳታፊዎችን ግርግር በመፍጠር በንብረት ላይ ውድመት አድርሰዋል በማለት በማስረጃ የተደገፈ ከባድ ክህደት በኢራን ላይ ፈጽመዋል ብለዋል። ለዚህም አሜሪካ እና እስራኤልን “ወንጀለኞች” በማለት ተጠያቂ አድርገዋል።

    የአሜሪካ እና የእስራኤል ነው ያሉትን አመጽ የአገሪቱ ሕግ አስከባሪዎች እና የደኅንነት አባላት ሕይወታቸውን ጭምር በመሰዋት በጠላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰው “ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረውታል” በማለት ኢራናውያን በአንድነት ቆመዋል ብለዋል።

    አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በኢራን ውስጥ በተካሄደው እና ከ2500 በላይ ሰዎች በተገደሉበት ሕዝባዊ ተቃመሞ ለደረሰው ውድመት እና ጉዳት የአሜሪካውን ፕሬዳንት ተጠያቂ አድርገው “ወንጀለኛ” ብለዋቸዋል።

    ሦስት ሳምንታትን ያስቆጠረው መላዋን ኢራንን ያናወጠው ተቃውሞ ቀዝቀዝ ያለ ቢመስልም አሁንም ሙሉ ለሙሉ አለመቆሙን የሚያመለክቱ ዜናዎች እየወጡ ነው።

  7. አይኤምኤፍ ኢትዮጵያ የ261 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ብድር እንድታገኝ ወሰነ

    የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የኢትዮጵያ የተራዘመ የብድር አቅርቦት አራተኛውን ግምገማ ማጠናቀቁን ተከትሎ የ261 ሚሊዮን ዶላር ብድር እንዲሰጣት አጸደቀ።

    ውሳኔው ላይ የተደረሰው “ከተጠበቀው በላይ ጠንካራ የማክሮኢኮኖሚ ውጤት እና በመርሃ ግብሩ ግዴታዎች ላይ አጠቃላይ አፈጻጸሞች በመታየታቸው ነው” ብሏል።

    ድርጅቱ ጥር 8/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሥራ አስፈጻሚው ቦርድ የኢትዮጵያን የፊሲካል ፋይናንስ ፍላጎት እና የክፍያ ሚዛን ለመደገፍ መወሰኑን አስታውቋል።

    ይህ ክፍያ በፕሮግራሙ ስር የተለቀቀውን አጠቃላይ የገንዘብ ድጋፍ ወደ 2.183 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያደርሰዋል።

    የድርጅቱ ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናይጄል ክላርክ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳው መሠረት እያከናወናቸው ያሉት ማሻሻያዎች ከሚጠበቀው በላይ ውጤት እያሳዩ ይገኛሉ ብለዋል።

    እንደ አይኤምኤፍ መረጃ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የወጪ ንግድ መጨመር፣ የተሻሻለ የገቢ አሰባሰብ፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እና የዋጋ ግሽበት በየጊዜው ማሽቆልቆል ታይቶበታል።

    እንደ ድርጅቱ ገለጻ በአውሮፓውያኑ 2025/26 የአገሪቱ የአጠቃላይ ዕድገት 9.3 በመቶ ሆኖ ይመዘገባል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፣ ይህም በ2024/2025 ከነበረው 9.2 በመቶ መሻሻል አሳይቷል።

    የዋጋ ግሽበት በ2023/24 ከነበረው 26.6 በመቶ ቀንሶ በ2024/25 በአማካይ 11.9 በመቶ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል።

  8. በኡጋንዳ ምርጫ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩው ቦቢ ዋይን ታፍኖ ተወስዷል መባሉን ፖሊስ አስተባበለ

    በኡጋንዳ ፕሬዚዳንታዊው ዕጩ ቦቢ ዋይን አርብ ምሽት በጸጥታ አካላት ተወስዷል በሚል የተሰራጨው መረጃ ሐሰት ነው ሲል ፖሊስ አስተባበለ።

    በኡጋንዳ ሐሙስ ዕለት አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን የድምጽ ቆጠራ እየተደረገ ነው።

    የቦቢ ዋይን ፓርቲ መሪያቸው አርብ ምሽት ካምፓላ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በሂሊኮፕተር ወደ ማይታወቅ ስፍራ በጉልበት መወሰዱን ገልጾ ነበር።

    መጀመርያ ላይ የዋይን ልጅ ሶሎሞን ካምፓላ፣ እናቱ እና አባቱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ይፋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ግን አባቱ “ማምለጡን” ተናግሯል።

    ሶሎሞን የሰጠው መረጃ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆነው ቦቢ ዋይን የት እንዳለ ግርታ ፈጥሯል።

    በአገሪቱ በተካሄደው ምርጫ ከ94 በመቶ የምርጫ ጣቢያዎች ከተሰበሰበ ድምጽ ይፋ በሆነው ጊዜያዊ ውጤት መሠረት ሙሴቪኒ 72 በመቶ ድምጽ ሲያገኙ ዋይን 24 በመቶ አግኝቷል።

    የፖሊስ ቃል አቀባይ ኪቱማ ሩሶኬ ቅዳሜ ማለዳ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የናሽናል ዩኒቲ ፕላትፎርም ፓርቲ መሪ በካምፓላ በሚገኘው ቤቱ እንደሚገኝ ተናግረው “መሠረተ ቢስ” የሆነ እና “ሐሰተኛ መረጃ” እያሰራጩ የሚገኙት ቤተሰቦቹ ናቸው ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።

    ዋይን በሚኖርበት ቤት “የደህንነት ትኩረት” ስላለ እንቅስቃሴያቸው መገደቡን ጨምረው ገልጸዋል።

    የኡጋንዳ ዴይሊ ሞኒተር “ለደህንነት ወሳኝ የሆኑትን አካባቢዎች ተቆጣጣረናል” ማለታቸውን ዘግቧል።

    “ሰዎች የተወሰኑ ቦታዎች በመሰባሰብ ቀውስ እንዲፈጥሩ አንፈቅድም። እርምጃችን ማንም አመጽ እንዳይፈጥር ወይም ደህንነታችን እዳያውክ ለማድረግ ነው” ብለዋል።

  9. በሊቢያ የስደተኞች አስከሬንን የያዘ የጅምላ መቃብር ተገኘ

    በምሥራቅ ሊቢያ በሚገኝ የእርሻ ቦታ ቢያንስ የ21 ስደተኞችን አስከሬን የያዘ የጅምላ መቃብር ተገኘ።

    የሊቢያ የጸጥታ አካላት በአካባቢው የተለያየ ዓይነት ስቅይት የደረሰባቸው 10 ስደተኞችን ማግኘታቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

    ሊቢያ ግጭቶችን እና ድህነትን በመሸሽ ወደአውሮፓ ለማቋረጥ የሚፈልጉ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን እንደመተላለፊያ የሚጠቀሙባት አገር ነች።

    ሁለት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ምንጮች ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩtእ በምሥራቅ ሊቢያ ከአጅዳቢያ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ እርሻ ቦታ ላይ የጅምላ መቃብር መኖሩን የሚገልጽ ጥቆማ ከደረሳቸው በኋላ ድንገተኛ ፍተሻ መደረጉን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    የእርሻው ባለቤት በቁጥጥር ሥር መዋሉን እና የጅምላ መቃብር መኖሩን መናገሩን የጸጥታ አካላት ተናግረዋል።

    "ስቅይት እንደደረሰባቸው የሚታይ ስደተኛ ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕጻናት አግኝተናል። ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፤ እዚያም ሌሎች ስደተኞች ከእነሱ ጋር እንደነበሩ እና ከዚያም የገቡበትን አለማወቃቸውን ተናግረዋል" ሲሉ አንድ የደህንነት ምንጭ ሐሙስ ዕለት ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    የጅምላ መቃብሩ የተገኘው ከሊቢያ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ቤንጋዚ 160 ኪሜትር ርቀት ላይ ነው።

    አካባቢው በካሊፍ ሃፍታር ጦር ቁጥጥር ሥር ያለ ነው ተብሏል።

    የአገር ውስጥ ደህንነት ኤጀንሲው የጅምላ መቃብር መገኘቱን አረጋግጦ፣ ስደተኞቹ የሞቱበት ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ተናግሯል።

  10. የኡጋንዳ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ቦቢ ዋይን ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዱ ተነገረ

    በኡጋንዳ ምርጫ ተቃዋሚው ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ቦቢ ዋይን ከባለቤቱ ጋር በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ካምፓላ ከሚገኘው ቤቱ መወሰዱን ልጁ አስታወቀ።

    የተቃመሚ ፖቲከኛው ልጅ ሶሎሞን ካምፓላ በኤክስ ላይ ባሰፈረው መልዕክት አባቱ እና እናቱ በኡጋንዳ መንግሥት ወታደሮች እና የልዩ ኃይል አባላት ተይዘው ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን ገልጿል።

    ቀደም ሲል ለቦቢ ዋይን ቅርብ የሆነ ምንጭ ወታደሮች አጥር ጥሰው በመግባት አስገድደው በሄሊኮፕተር እንደወሰዱት ተናገሮ ነበር።

    ቦቢ ዋይን ሐሙስ ተካሂዶ የድምጽ ቆጠራው እየተካሄደ ባለው ምርጫ ለሰባተኛ ጊዜ የሚወዳደሩት ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በሰፊ ልዩነት እየመሩበት ያለውን ሂደት ታማኝነት ላይ ጥያቄ አንስቶ ነበር።

    የአካበቢው ፖሊስ ስለክስተቱ በተጠየቀበት ጊዜ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጿል።

    በፕሬዝዳንታዊው ምርጫ በሥልጣን ላይ ያሉት ሙሴቬኒ ዋነኛ ተፎካካሪያቸው ሆነውን ቦቢ ዋይንን በከፍተኛ ልዩነት እየመሩ መሆናቸው ተነግሯል።

    የምርጫው የመጨረሻ ውጤት ዛሬ ቅዳሜ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

    ከሐሙስ ጀምሮ መንግሥት በመላዋ ኡጋንዳ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን እንዲቋረጡ አድርጓል።

  11. ትራምፕ በግሪንላንድ ላይ ያላቸውን ፍላጎት የሚቃወሙ አገራት ላይ አዲስ ታሪፍ ለመጣል ዛቱ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን ለመጠቅለል ያላቸውን ፍላጎት የሚቃወሙ አገራት ላይ ታሪፍ ለመጫን ዛቱ።

    ትራምፕ በዋይት ሐውስ በነበራቸው ስብሰባ ላይ “በግሪንላንድ ላይ ባለን አቋም የማይስማሙ አገራት ላይ ታሪፍ ልንጥል እንችላለን” ብለዋል።

    ግሪንላንድ የዴንማርክ ራስ ገዝ ግዛት ነች። ትራምፕ ይህ ታሪፍ በየትኛው አገር ላይ እንደሚጣል አልተናገሩም።

    እስካሁን ድረስ ዴንማርክ እና ግሪንላንድ እንዲሁም ሌሎች የአውሮፓ አገራት የትራምፐን ዕቅድ ተቃውመዋል።

    ትራምፕ ይሀንን ሲሉ 11 የኮንግረስ አባላት ለግሪንላንድ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ወደ ሥፍራው አቅንተዋል።

    ትራምፕ ግሪንላንድ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አስፈላጊ መሆኗን በመናገር “በቀላል መንገድ” ወይም ደግሞ "በከባድ ሁኔታ” የአሜሪካ አካል እንደሚያደርጓት ተናግረዋል።

    ይህም ግዛቲቱን በገንዘብ መግዛት አልያም በወታደራዊ ኃይል መጠቅለል ሊሆን እንደሚችል ተንታኞቸ ይናገራሉ።

  12. በለንደን በሚገኘው የኢራን ኤምባሲ የተደረገው ሠልፍ ወደ ሁከት ተለወጠ

    በለንደን በኢራን ኤምባሲ ፊት ለፊት ለተቃውሞ የተሰባሰቡ ሠልፈኞች ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸው እና በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘገበ።

    በኤምባሲው የተፈጠረውን ሁለት ተከትሎ ጉዳት የደረሰባቸው አራት ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጿል።

    አንድ የተቃውሞ ሠልፈኛ በኢራን ኤምባሲ ጣሪያ ላይ በመውጣት የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ያወረደ ሲሆን፣ ፖሊስ እርሱን እና ሌሎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።

    አርብ ዕለት በለንደን ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ እና በኢራን ኤምባሲ አካባቢ የተሰባሰቡ ሠልፈኞች ከፖሊስ ጋር የተጋጩ ሲሆን፣ "ቁሳቁሶች መወርወራቸውን" ፖሊስ ገልጿል።

    በዚህም የተነሳ የተወሰኑ ፖሊሶች ጉዳት እንዳጋጠማቸው እና “በርካታ ሰዎች ረብሻ በመፍጠር ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለዋል” ብሏል።

    የለንደን ፖሊስ በኤክስ ገጹ “በኢራን ኤምባሲ እየተካሄደው ባለው የተቃውሞ ሠልፍ አንድ ሠልፈኛ ሕገወጥ በሆነ መልኩ . . . በኤምባሲው ጣሪያ ላይ በመውጣት ባንዲራ አውርዷል” ሲል የተፈጠረውን አስፍሯል።

    የለንደን ፖሊስ የተቃውሞ ሠልፉ በሚካሄድበት የኢራን ኤምባሲ አካባቢ በርካታ አባላቱን ማሰማራቱን ገልጿል።

    ባለፈው ሳምንት በዚሁ ሥፍራ በነበረ የተቃውሞ ሠልፍ የኢራንን ይፋዊ ሰንደቅ ዓላማ በማውረድ ከአውሮፓውያኑ 1979 አብዮት በፊት የነበረውን ሰቅለዋል።

  13. ትራምፕ የኢራን አመራሮች ‘ተቃዋሚዎችን ባለመግደላቸው’ አመሰገኑ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አርብ ዕለት የኢራን መንግሥት በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ለመግደል የያዘውን ዕቅድ በማስቀረቱ አመሰገኑ።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አርብ ዕለት 800 ሰዎችን በስቅላት ለመቅጣት ተይዞ የነበረው ቀጠሮን በመቅረቱ ባልተለመደ ሁኔታ የኢራን ባለሥልጣትን አመስግነዋል።

    “. . .ሊፈጸሙ ታቅደው የነበሩት (ከ800 በላይ ስቅላቶች) በሙሉ በኢራን አመራሮች በመሰረዛቸው ያለኝን አክብሮት እገልጸለሁ፤ አመሰግናለሁ” ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ የሳምንቱን መጨረሻ ፍሎሪዳ በሚገኘው መኖሪያቸው ለማሳለፍ ሲሄዱ እስራኤል እና የአረብ አገራት ኢራንን ላይ ጥቃት እንዳይፈጽሙ አሳምነዋቸው እንደሆን ተጠይቀው ነበር።

    “ማንም አላሳመነኝም፤ ራሴን አሳምኛለሁ። ከ800 በላይ ሰዎችን ለመግደል አቅደው ነበር። ማንንም አልገደሉም። ስቅላቶቹ ተሰርዘዋል። በጣም አስደናቂ ነበር” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ከዚህ ቀደም ዶናልድ ትራምፕ የኢራን መንግሥት ተቃዋሚ ሠልፈኞችን የሚገድል ከሆነ "ጠንካራ እርምጃ" እንደሚወስዱ አስጠንቅቀው ነበር።

    በተጨማሪም ሠልፈኞቹን በማበረታታት "ድጋፍ እየመጣላችሁ" ነው ሲሉ ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።

  14. የኢራን ተቃውሞ መሪ የሆኑት ልዑል ሬዛ ፓህላቪ ትራምፕ ቃላቸውን እንደሚጠብቁ ተናገሩ

    በስደት ላይ የሚገኙት የመጨረሻው የኢራን ንጉሥ ልጅ የዓለም መንግሥታት የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክን ለመጣል ተቃዋሚዎችን እንዲደግፉ ጥሪ አቀረቡ።

    ተቃውሞውን አሜሪካ ተቀምጠው የሚመሩት ሬዛ ፓህላቪ ትራምፕ ቃላቸውን የሚጠብቁ መሪ መሆናቸውን እና ከኢራናውያን ጎን እንደሚቆሙ እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

    “እስላማዊው ሪፐብሊክ ይወድቃል፤ ሊወድቅ ይችላል የሚለው ሳይሆን መቼ“ የሚለው ነው ጥያቄው ሲሉ ተናግረዋል።

    በአሜሪካ የሚኖሩት የተቃዋሚ መሪ የሆኑት ሬዛ ፓህላቪ፣ ዓለም የኢራንን አብዮታዊ ዘብ አመራርን ዒላማ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

    ይህም "ዓላማችንን ያመቻቻል እንዲሁም ተጨማሪ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ይከላከላል" ብለዋል።

    ከሃያ ቀን በፊት በኢራን የኑሮ ውድነትን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመጽ እስካሁን ድረስ ከ2,600 በላይ ተቃዋሚዎች በኢራን የፀጥታ አካላት መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አስታውቀዋል።

    የኢራን መንግሥት ተቃውሞዎቹን በኢራን ጠላቶች የተደገፉ "ረብሻዎች" ሲል ጠርቷቸዋል።

    ፓህላቪ በኢራን የሚካሄደው ተቃውሞ መሪ ሆነው ብቅ ያሉ ሲሆን፣ ኢራናውያን ተቃውሟቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

    በኢራን የተቀሰቀሰውን መጠነ ሰፊ ተቃውሞ ተከትሎ የኢንተርኔት እና ሌሎች የመገናኛ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ የተቋረጡ ሲሆን፣ የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎችም ጠንካራ እርምጃ መውሰዳቸውን ቀጥለዋል።

    ፓህላቪ አርብ ዕለት በዋሽንግተን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢራን የደኅንነት ክፍል በዘመቻው ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆኑን እና የኢራን ባለሥልጣናት ተቃውሞውን ለማብረድ ከውጭ ሚሊሻዎች ማምጣታቸውን ተናግረዋል።

    ዓለም የኢራንን አብዮታዊ ዘብ ኃይሎች ዒላማ እንዲያደርግ እና መሠረተ ልማቶችን እንዲቆጣጠር እንዲሁም እንዲያዝ አሳስበው "ወሳኝ የሆነ ጥቃት" እንዲፈጸም ጥሪ አቅርበዋል።

    በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ኃያላን አገራት የኢኮኖሚ ጫና እንዲፈጥሩ፣ የኢራን ዲፕሎማቶችን እንዲያባርሩ፣ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እንዲጠይቁ እና በኢራን ውስጥ ግንኙነት እንዲኖር የሳተላይት ኢንተርኔት፣ ስታርሊንክ እና ሌሎች ደኅንነታቸው የተጠበቀ ግንኙነቶችን እንዲፈቅዱ ጠይቀዋል።

    “የኢራን ሕዝብ ወሳኝ እርምጃ እየወሰደ ነው። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሙሉ በሙሉ እንዲቀላቀል ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል።

    "በዓለም እርዳታ ወይም ያለ ምንም ድጋፍ ሥርዓቱ ይወድቃል። ዓለም ቃሉን ወደ ተግባር ከቀየረ ፈጥኖ ይወድቃል፤ ብዙ ሕይወትም ይድናል።"

    ከከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት አድርገዋል ስለሚሉ ዘገባዎች ለመናገር ፈቃደኛ ባይሆኑም፣ “ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቃላቸውን የሚያከብሩ ሰው እንደሆኑ እና በመጨረሻም ከኢራናውያን ሕዝብ ጋር እንደሚቆሙ አምናለሁ” ብለዋል።

  15. ተዋናይ እና የቴሌቪዥን መሰናዶ አቅራቢ ነጻነት ወርቅነህ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

    በቴአትሮች፣ በአስቂኝ ፊልሞች ላይ በመተወን እና የቴሌቭዥን መሰናዶ በመምራት የሚታወቀው ነጻነት ወርቅነህ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

    ‘ኤፍቢአይ’፣ ‘ፍሬሽማን’ እና ‘ያንቺው ሌባ’ን ጨምሮ በሌሎችም አስቂኝ ፊልሞች እንዲሁም ተውኔቶች የሚታወቀው ነጻነት ባደረበት ሕመም ማረፉ ተገልጿል።

    ነጻነት ወርቅነህ ለዓመታት ተወዳጅ በሆነው እና በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የሚተላለፈው ‘የቤተሰብ ጨዋታ’ ፕሮግራም አዘጋጅ እና አቅራቢ የነበረ ሲሆን በቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችም ዝነኛ ነበር።

    ኢቢኤስ ቴሌቭዥን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አርቲስቱ ባደረበት ሕመም በድንገት ሕይወቱ ማለፉን ገልጾ ኅልፈት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በሕልፈቱ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው “ነጻነት በተለይም በሕዳሴ ግድብ በተዘጋጀው የ2016 አዲስ ዓመት የመቀበያ ፕሮግራም የነበረውን አስተዋጽዖ ሁሌም አስታውሰዋለሁ" በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም ነጻነት የመራው እና እሳቸውም የታደሙበትን የአዲስ ዓመት ዝግጅtእ በማስታወስ "ሁላችንም አዲሱን ዓመት በደስታ እንድንቀበል አድርጎን ነበር። ለቤተሰቦቹ እና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን እመኛለሁ” ብለዋል።

    ነጻነት ባለ ትዳር እና የሦስት ልጆች አባት ነው።

    የነጻነት የእረፍት ዜና መሰማቱን ተከትሎ የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ታዋቂ ሰዎች፣ የሙያ ባልደረቦቹ እንዲሁም አድናቂዎቹ ከምሥሉ ጋር የሐዘን መግለጫዎችን እያጋሩ ነው።

  16. ኢራን በብሪክስ የባሕር ኃይል ልምምድ ላይ መሳተፏ ውዝግብ አስነሳ

    በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የብሪክስ አገራት የባሕር ኃይል ልምምድ ላይ ኢራን ተሳታፊ መሆኗ አሜሪካንን ሲያስቆጣ በደቡብ አፍሪካ መንግሥት ውስጥ ውዝግብ ፈጠረ።

    አሜሪካ የኢራን መንግሥት በተቃዋሚዎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ እየወሰደ ባለበት ጊዜ ኢራን በልምምዱ ላይ ተሳታፊ እንድትሆን ደቡብ አፍሪካ መጋበዟን በጽኑ ተችታለች።

    ሩሲያ፣ ቻይና እና ሌሎች የብሪክስ አባል አገራት ባሕር ኃይሎች በተሳተፉበት በደቡብ አፍሪካ የባሕር ክልል ውስጥ በተካሄደው ልምምድ ላይ ኢራን የተሳተፈችው የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር የፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳን ትዕዛዝ ችላ ብሎ ነው የሚል ክስም ተሰንዝሯል።

    ለዚህም ምላሽ የደቡብ አፍሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ለዚህ “ከባድ ክስ” ምላሽ ማጣራት ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።

    በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው ጠንካራ የተቃውሞ መግለጫ የደቡብ አፍሪካ መከላከያ ሚኒስቴር እና የጦር ኃይሎች ለፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ ባለመገዛት ኢራን በልምምዱ እንድትሳተፍ ማድረጋቸው “የሚያስደነግጥ እና የሚያሳስብ “ ነው ብሎታል።

    የደቡብ አፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሯ የፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ መመሪያ “ለሚመለከታቸው ሁሉ በግልጽ ተላልፎ ስምምነት ተደርሶበት እና ተግባራዊ እንዲሆን” መወሰኑን ይፋ አድርገዋል።

    ነገር ግን ኢራን ከብሪክስ አገራት የባሕር ኃይል ልምምዱ እንድትወጣ የተላላፈው ውሳኔ ተጥሶ በቻይና በተመራው እና ለአንድ ሳምንት በቆየው ልምምድ ላይ ተሳትፋለች።

    ብሪክስ በብራዚል፣ በሩሲያ፣ በሕንድ፣ በቻይና ተመሥርቶ ደቡብ አፍሪካ ዘግይት ብላ ነበር የተቀላቀለችው። በቅርቡም ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የስብስቡ አባል ሆነዋል።

  17. “ከኢራን ጋር ያለው ቅራኔ በዲፕሎማሲ ይፈታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ”- የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ

    የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ስቲቭ ዊትኮር ከኢራን ጋር ያለው ቅራኔ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ይፈታል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናገሩ።

    በእስራኤላውያን እና አሜሪካውያን ጥምር ካውንስል ላይ ንግግር ያደረጉት መልዕክተኛው፤ ኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ይወሰድ እንደሆነ ተጠይቀው “በዲፕሎማሲ ይቋጫል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ መልሰዋል።

    ከኢራን ጋር በተያያዘ እልባት ያላገኙ አራት ጉዳዮች “ኒውክሌር፣ ኒውክሌር ማበልጸግ፣ ሚሳዔል እና የውክልና ኃይሎች” መሆናቸውን አክለዋል።

    የፕሬዝዳንት ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ስቲቭ ዊትኮር ከኢራን ጋር ያለው ቅራኔ በዲፕሎማሲ የማይፈታ ከሆነ “ለኢራን የከፋ ይሆናል” ብዋል።

    ዊትኮፍ ኢራናውያንን “ጀግኖች” ብለው ያሞካሹ ሲሆን፤ አሜሪካ ከኢራናውያን ጎን እንደምትቆምም ተናግረዋል።

  18. የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከሞቃዲሾ መውጣት ጀመረች

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከሶማሊያ ጓዟን ጠቅልላ መውጣት ጀመረች።

    ሐሙስ ዕለት የዩኤኢ መንግሥት ንብረት የሆኑ ቁሳቁሶችን የጫኑ ሦስት አውሮፕላኖች ከአደን አዴ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መነሳታቸውን ምንጮችን ጠቅሶ የቢቢሲ የሶማሊኛ አገልግሎት ዘግቧል።

    ሶማሊያ ከኤምሬትስ ጋር ያላትን የደህንነት እና የመከላከያ ስምምነት ከሰረዘች በኋላ ከሞቃዲሿ ያላትን ቁሳቁስ ማውጣት ጀምራለች።

    አርብ ዕለት ተጨማሪ ቁሳቁሶችን ለማውጣት ሁለት ተጨማሪ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ሶማሊያ ከኤምሬትስ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማቋረጥ የወሰነችው ያለፈቃድ የአየር ክልሏን እና ግዛቷን በመጠቀም የየመን ተገንጣይ ቡድን መሪ የሆኑት አይዳሮስ አል-ዙባይዲን ማስወጣቷን ተከትሎ ነው።

    ኤምሬትስ ከሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት እና ከክልል መንግሥታት ጋር ባላት ስምምነት መሠረት በቦሳሶ፣ በኪስማዮ እና በበርበራ ወደቦች የልማት ሥራዎች ስታከናውን ቆይታለች።

    ነገር ግን ባለፈው ሰኞ የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ከዩኤኢ ጋር የገባውን የወደብ ማልማት እና የፀጥታ ስምምነት ሙሉ በሙሉ መሰረዙን አስታውቋል።

    ሶማሊያ ይህን ያደረገችው ዩኤኢ ሉዓላዊነቴን ጥሳለች በሚል ነው።

    በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች እንዳሉት በሶማሊያ እና በኤምሬትስ ባለሥልጣናት መካከል በሰነድ እና በፍቃድ ዙሪያ በነበሩ ሂደቶች የተነሳ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር።

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባለሥልጣናት በመጀመሪያ የሶማሊያ መንግሥት መመሪያዎችን ተቃውመው ነበር ያሉት ምንጮቹ አውሮፕላኑ ከመነሳቱ በፊት የበረራ መግለጫዎችን እና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን አቅርበው ንብረቶቻቸውን መውጣት ችለዋል ብለዋል።

  19. ሙሴቪኒ በጊዜያዊ የምርጫ ውጤት በከፍተኛ ልዩነት እየመሩ ነው

    የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ሐሙስ ዕለት በተካሄደው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጊዜያዊ ውጤት መሠረት በከፍተኛ ልዩነት እየመሩ መሆኑን የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አስታወቀ።

    አርብ ጠዋት ይፋ በተደረገው ጊዜያዊ ውጤት መሠረት ሙሴቬኒ 76 በመቶ ድምጽ በማግኘት መሪነቱን ይዘዋል። ይህ የምርጫ ውጤት የተሰበሰበው ከ45 በመቶ የአገሪቱ የምርጫ ጣቢያዎች ነው ተብሏል።

    እንደ ኤጀንሲው ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት ከሆነ የተቃዋሚው መሪ ቦቢ ዋይን 20 በመቶ ገደማ የመራጮች ድምጽን ማግኘት ችሏል።

    ኡጋንዳውያን ከተደጋጋሚ ተቃውሞ እና አመጽ በኋላ ሐሙስ ዕለት በተካሄደው ውጥረት የበዛበት ብሔራዊ ምርጫ በቀጣይ አገሪቱን ለሚያስተዳድራት ተወዳዳሪ ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

    የ81 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ የተወዳደሩት የአገሪቱን መሪነት መንበር ለሰባተኛ ጊዜ ለማሸነፍ ነው።

    የቀድሞው ድምጻዊ የ43 ዓመቱ ፖለቲከኛ ቦቢ ዋይን በምርጫው ወቅት "ከፍተኛ" ማጭበርበር እንደተፈጸመ ተናግሯል።

    ምርጫወe የተካሄደው በመላው አገሪተ ኢንተርኔት ከተቋረጠ በኋላ ነው።

    ቦቢ ዋይን ተፈፀመ ስላለው የምርጫ ማጭበርበር ምንም ዓይነት ማስረጃ ያላቀረበ ሲሆን የምርጫ ኮሚሽንም ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጠም።

    የቀድሞው የአማፂ መሪ ሙሴቪኒ የሚያሸንፉ ከሆነ የአራት አስርት ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸውን ያራዝመዋል።

    ሙሴቪኒ የጦር ጄነራል የሆኑት ልጃቸው ሙሁዚ ካይነሩጋባን ተተኪ አድርገው እንደሚመርጡ በሰፊው ይታመናል።

    ይህንን ግን ፕሬዚዳንቱ አስተባብለዋል።

    የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን የመጨረሻው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ቅዳሜ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።

  20. በኢራን ኢንተርኔት ከተቋረጠ 180 ሰዓታት አለፉ

    ኔት ብሎክስ የተሰኘውና በዓለም የኢንተርኔት ስርጭትን የሚከታተለው ድርጅት በኢራን የኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ 180 ሰዓታት ማለፉን አስታወቀ።

    ድርጅቱ በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት አገሪቱ አሁን ያጋጠማት እአአ በ2019 ከነበረው የኢንተርኔት መቆራረጥ የበለጠ መሆኑን ገልጿል።

    በኢራን ከሁለት ሳምንት በላይ የቀጠለ ሕዝባዊ አመጽ እየተካሄደ ነው።

    አመፁ የተቀሰቀሰው የኑሮ ውድነትን ምክንያት አድርጎ ቢሆንም አገሪቱን ለረዥም ዓመታት ያስተዳደረው መንግሥት ከሥልጣን እንዲወርድ የሚጠይቁ ድምጾች ተሰምተዋል።

    የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መንግሥት ተቃውሟቸውን ለመግለጽ አደባባይ በወጡ ኢራናውያን ላይ በወሰደው እርምጃ ከ2400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።

    ኔት ብሎክስ እአአ በ2019 ለአንድ ሳምንት ያህል የዘለቀውን የኢንተርኔት መቋረጥ ጠቅሶ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ምን ያህል የከፋ እንደነበር የታወቀው ኢንርኔት ዳግም ሲጀመር ነው ብሏል።