ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኤርትራ ለታጣቂዎች የጦር መሣሪያ ጥይቶችን እያቀረበች ነው ሲል ከሰሰ
ኢትዮጵያ የጎረቤት አገር ኤርትራ መንግሥት በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች የተለያዩ ዓይነት የጦር መሣሪያ ጥይቶችን እየሰጠ ነው ስትል ከሳለች።
ፌዴራል ፖሊስ ረቡዕ ጥር 6/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከ56 ሺህ በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶችን በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ብሏል።
ፌዴራል ፖሊስ፤ እነዚህ የጦር መሣሪያዎች የኤርትራ መንግሥት "ከኢትዮጵያ የውስጥ ባንዳዎች እና ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር" በትግራዩ ህወሓት በኩል የተላኩ ናቸው ሲል ከስሷል።
ተያዙ የተባሉት ከ56 ሺህ በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶች ሲሆኑ፣ ሲያጓጉዟቸው የነበሩ "ሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በወልዲያ የፍተሻ ጣቢያ" ላይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አመልክቷል።
ፖሊስ "በስውር የተላኩ" ያላቸው 41,999 የክላሽ ጥይት፣ 14,000 የብሬን ጥይት እና 800 የድሽቃ ጥይት በአጠቃላይ 56,799 ጥይቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በማኅበራዊ ሚድያ ገፁ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
መግለጫው እንደሚለው የጦር መሣሪያዎቹ በፀጥታ ኃይሎች ትብብር በቁጥጥር ሥር የዋሉት ማክሰኞ ጥር 5/2018 ዓ.ም. ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን ለመመለስ ያላትን አማራጭ እንደምትጠቀም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መግለፃቸውን ተከትሎ በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት እየተካረረ መጥቷል።
ዐቢይ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ "ባሕር በር አልባ ሀገር ሆና አትቀርም" ሲሉ ይናገራሉ። ኤርትራ በአውሮፓውያኑ 1991 ነፃነቷን ማግኘቷን ተከትሎ ኢትዮጵያ ባሕር በር አልባ ሀገር ሆና ቆይታለች።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው ሰኞ ከአገራቸው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ "የብልጽግና የቀይ ባሕር ፍላጎት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የታወጀ ጦርነት ነው" ማለታቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ካለው ውጥረት ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄ "የውሃ ጦርነት ብሎ ማወጅ ለማን ነው? ለእኛ በቀጥታ የቀይ ባሕር ጉዳይ አይደለም። የናይል ጦርነት ነው እየታወጀ ያለው። ጦርነቱ ማንን የሚመለከት ነው?" ብለዋል።
ፌዴራል ፖሊስ እንደሚለው የኤርትራ መንግሥት የፋኖ ታጣቂዎችን ለማስታጠቅ የሞከረው ኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት ለመፍጠር ነው።
ኢሳያስ ለጦርነት ዝግጅት ወደ ኢትዮጵያ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እና ሌሎችም የጦር መሣሪያዎች እየገቡ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የፖሊስ መግለጫ እንደሚለው ተጠርጣሪዎቹ ላይ በተደረገው ምርመራ የጦር መሣሪያ ጥይቶቹ ከኤርትራ መንግሥት የተላኩ መሆናቸውን እና ህወሓት መቀሌ ላይ ተቀብሎ ወደ አማራ ክልል በማስገባት ለፋኖ ለማድረስ ሲንቀሳቀስ ነበር።
ጥይቶቹን ሲያጓጉዙ ተይዘዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ አደረግኩ ባለው ምርመራ "ጥይቶቹ በሻዕቢያ መንግሥት እንደተላኩ እና ጽንፈኛው ህወሓት...ከመቀለ ወደ አማራ ክልል ሸዋ ሮቢት" ለማድረስ መንገድ ላይ እንደነበሩ ተናግረዋል ብሏል።
ህወሓት በበኩሉ፤ በኤርትራ መንግሥት ተልኳል የተባለውን የጦር መሣሪያ "ጽንፈኛው ህወሓት ከትግራይ...ወደ አማራ ክልል" ለማስገባት ተንቀሳቅሷል የሚል የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርጓል። የህወሓት ቃል አቀባይ ሚካኤል አስገዶም፤ "ጭብጥ የሌለው ውሸት ነው" ሲሉ አጣጥለዋል።
ህወሓት "ወደዚህ የወረደ ሥራ የሚገባ ፓርቲ አይደለም" ሲሉ የተከላከሉት ቃል አቀባዩ፤ "በውስጣቸው የተፈጠረውን አጀንዳ ለማስቀየስ ሆነ ተብሎ የተሠራ የውሸት ዜና ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ሚካኤል ይህ ዓይነቱ ክስ "የተለመደ ነው" ብለዋል። "ወደ ግጭት እንዳይኬድ እኛ የበኩላችንን ጥረት እያደረግን ነው። የእነሱ አካሄድ ግን፤ ይመስለኛል ወደዚያ የሚመራ ነገር ነው" ሲሉም የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናትን ወንጅለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው ህወሓት ከኤርትራ መንግሥት ጋር እየተባበረ ነው የሚል ወቀሳ ሲያሰማ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የኤርትራ መንግሥት እና ህወሓት ኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት ለመፍጠር እየተባበሩ ነው ብለው ከዚህ ቀደም የወቀሱ ሲሆን፣ ሁለቱ ወገኖች ግን ይህን ክስ ያስተባብላሉ።
ፌዴራል ፖሊስ "የጠላት ኃይሎች በሀገራችን ላይ አደጋ ለማድረስ እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው የፀጥታ ኃይሉ የጀመረውን ኦፕሬሽን አጠናከሮ እንደሚቀጥል" ገልፆ ሕብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር እንዲተባበር ጥሪ አቅርቧል።