ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ እና ተቃዋሚያቸው ቦቢ ዋይን የሚፎካከሩበት የኡጋንዳ ምርጫ እየተካሄደ ነው
ኡጋንዳያውያን ለ40 ዓመታት የዘለቀ ሥልጣናቸውን ለማስቀጠል እየጣሩ ያሉትን ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ እና ተቃዋሚያቸው የቀድሞ የፖፕ ሙዚቀኛ ቦቢ ዋይን ለተፋጠጡበት ምርጫ ዛሬ ድምጻቸውን እየሰጡ ነው።
የኡጋንዳ የምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ፤ የተወሰኑ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች አሸናፊ መሆናቸውን እንዳያውጁ በአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ማስፈራሪያዎች እየደረሱባቸው እንደሆነ አስታውቀዋል።
21.6 ሚሊዮን ሰዎች ድምጽ ለመስጠት በተመዘገቡበት የኡጋንዳ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ስድስት ሰዎች በዕጩነት ቀርበዋል።ዋናው ፉክክር ያለው ግን በሙሴቬኒ እና ወደ ፖለቲከኛነት በተቀየረው የቀድሞው ሙዚቀኛ ቡቢ ዋይን መካከል ነው።
ትንታኞች ያለፉትን ተከታታይ ስድስት ምርጫዎች ያሸነፉት ሙሴቬኒ ሥልጣናቸውን የማራዘም ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
ትክክለኛ ስሙ ሮበርት ኪያጉላኒ የሆነው የ43 ዓመቱ ዋይን፤ ሙስናን ለመዋጋት እና ጠንካራ ለውጥ ለማካሄድ ቃል ገብቷል። ሙሴቬኒ በበኩላቸው በአገሪቱ መረጋጋት እና ዕድገት በማምጣት ብቸኛው መሪ መሆናቸውን በማንሳት ይከራከራሉ።
ተቃዋሚዎች ያደረጓቸው የምርጫ ዘመቻዎች መስተጓጎል የበዛባቸው ነበሩ። የፀጥታ ኃይሎች፤ የዋይን ደጋፊዎች ላይ ጥቃት እና እስር ፈጸመዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ይህንን ክስ ውደቅ ያደረጉት የአገሪቱ ፖሊስ ቃል አቀባይ ኪቱማ ሩሶኬ በበኩላቸው፤ በተለይም የዋይን ፓርቲ የሆነው 'ናሽናል ዩኒቲ ፕላትፎርም' ደጋፊዎች ረብሻ ፈጥረዋል ሲሉ መልሰው ወንጅለዋቸዋል።
የዛሬው ድምጽ መስጫ ቀን ከመድረሱ አስቀድሞ ኢንተርኔት እንዲቋረጥ ተደርጓል። የኡጋንዳ ኮሚዩኒኬሽን ኮሚሽን፤ ኢንተርኔት መቋረጡ ሐሰተኛ መረጃ፣ ማጭበርበ እና ብጥብጥ ማነሳሳትን ለመከላከል አስፈላጊ እንደሆነ ገልጿል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ግን "እጅግ አሳሳቢ" ሲሉ እርምጃውን ኮንነዋል።
የዋይን ፓርቲም ኢንተርኔት ለማቋረጥ የተሰጠውን ምክንያት ውደቅ አድርጓል። የመንግሥት ባለሥልጣናት ተቃዋሚዎች የሚያደርጉትን መሰባሰብ እና የምርጫ ማጭበርበርን የተመለከ መረጃ ልውውጥ ለማስቆም ሞክረዋል ሲል ከስሷል።
የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ ሳይመን ብያባካማ በበኩላቸው አንዳንድ ተቃዋሚዎችን አሸናፊ አድርገው እንዳይገልጹ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንደሆነ አስታውቀዋል።
ኃላፊው በስም ካልጠቀሷቸው ባለሥልጣናት ለሚደርስባቸው ማስፈራሪያ እንደማይንበረከኩም ተናግረዋል።
ሳይመን ይህንን የተናገሩት በስፋት የተሠራጨ አንድ ቪዲዮን በተመለከተ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ነው።
ቪዲዮው ላይ የፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ልዩ ረዳት የሆኑ ግለሰብ፤ ተቃዋሚው ቦቢ ዋይን ቢያሸንፍ እንኳ ምርጫ ኮሚሽን አሸናፊነቱን እንደማያውጅ ሲናገሩ ይታያሉ።
ኃላፊው "አንዳንድ ሰዎች 'እገሌን ፕሬዝዳንት አድርገህ የማታውጅ ከሆነ ታያለህ' ይላሉ። እኔ ድምጽ የመለገስ ሥራ ላይ እንዳልተሰማራሁ እነግራቸዋለሁ" ሲሉ ተናግረዋል። "ሥራ ፈት ሰዎች" ሲሉ ከጠሯቸው አካላት የሚደርስባቸው ዛቻ እንደማያሳስባቸውም አክለዋል።
"ከሁኔታዬ መረዳት እንደምትችሉት 'ፍርሃት' የሚለው ቃል በእኔ መዝገበ ቃላት ውስጥ የለም" ያሉት የምርጫ ኮሚሽን ኃላፊው፤ ሂደቱን የሚመሩት የመራጮችን ፍላጎት እና ሕጉ በመከተል ብቻ እንደሆነም ገልጸዋል።
"ሕጉ ከጠቅላላው ትክክለኛ ድምፅ ውስጥ 50 በመቶ ሲደመር አንድ ያገኘ ዕጩ የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ይሆናል። አንድ ዕጩ ምን ያህል ድምፅ እንደሚያገኝ የሚወስኑት መራጮች ናቸው። መራጮች ያሉትን ደግሞ እኔ ለአገሪቱ አውጃለሁ" ብለዋል።
በአገሪቱ ሕግ መሠረት ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በ48 ሰዓታት ውስጥ ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግም የምርጫ ቦርድ ኃላፊው ገልጸዋል።