ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ስማርት መነጽር ያደረገ ሰው በድብቅ በቀረጸኝ ቪዲዮ ምክንያት የኢንተርኔት መሳለቂያ ሆንኩ"
ጥቅም ላይ ከዋሉ የረቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል አንዱ ተደርገው የሚቆጠሩት 'ስማርት' መነጽሮች፤ በዓለም ገበያ ላይ ተስፋፍተዋል። ነገር ግን እነዚህ ምርቶች ሴቶችን ለመጉዳት፣ ለማዋረድ እና የግል ነጻነታቸውን ለመጋፋት እየዋሉ ነው የሚሉ ስጋቶች ይነሳሉ።
ኡና ካሜራ የተገጠለት ስማርት መነጽር ባደረገ ሰው ሳታውቅ እና ሳትፈቅድ እንደተቀረጸች ትናገራለች።
ቪዲዮው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተለጥፎ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ዕይታን አግኝቷል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ አስተያየቶች ተሰጥተውበታል። ከአስተያየቶቹ ውስጥ አብዛኛዎቹ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው እና አዋራጅ ናቸው።
ኡና "ይህ እየደረሰብኝ እንደሆነ ምንም አላውቅም ነበር። ቪዲዮው እንዲለጠፍ አልፈቀድኩም፣ በድብቅ እንድቀረጽም ፈቃድ አልሰጠሁም" ትላለች።
"በጣም አስደንጋጭ ነበር፤ ሰው ወደሚገኝባቸው ቦታዎች መውጣትን እንድፈራ አድርጎኛል" ስትል ለቢቢሲ የደረሰባትን አስረድታለች።
ኡና እንደምትናገረው፤ ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ብራይተን በሚገኝ የባሕር ዳርቻ ላይ ፀሐይ እየሞቀች ሳለ ነበር የፀሐይ መነጽር ያደረገ ሰው ወደ እርሷ የመጣው።
ስሟን፣ የመጣችበትን ቦታ እና ስልክ ቁጥሯን ጠየቃት። እሷም በትህትና ፍቅረኛ እንዳላት በመንገር ጥያቄውን ውድቅ አደረገች።
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ቲክቶክ ላይ አንድ ቪዲዮ ተላከላት። ቪዲዮው ግለሰቡ እና እርሷ ያደረጉትን ንግግር የሚያሳይ ነበር። የተቀረጸውም ከሰውየው ዕይታ አንጻር እንደሆነ ያስታውቃል። ሰውየው አድርጎት የነበረው መነጻር እየቀረጻት እንደነበር የተረዳችው የዚያን ጊዜ ነው።
ስማርት መነጽሮች እንደ ስማርት ስልክ ሁሉ ካርታዎችን መጠቀም፣ ሙዚቃ ማዳመጥ እና ቪዲዮ መቅረጽ ያስችላሉ።
ቪዲዮውን የተመለከቱት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ "የድንጋጤ ስሜት" እንደተሰማት ኡና ትናገራለች። ብራይተን ውስጥ እንደምትኖር በግልጽ ከሚያሳውቀው ቪዲዮ ስር የተሰጡት አስተያየቶች በስድብ የተሞሉ ነበሩ።
"ከቁጥጥሬ ውጪ ነበር፤ ትልቁ አስፈሪው ነገርም ይኸው ነገር ነበር" ትላለች።
ድርጊቱን ለአካባቢው ፖሊስ አሳወቀች። ፖሊስ ግን ሕዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ ሰዎችን መቅረጽ ወንጀል ባለመሆኑ ምንም ሊያደርግ እንደማይችል ነገራት።
"እንዲህ ዓይነት ነገር የማውቃቸው ሴቶች ላይ በሙሉ ያጋጥማቸዋል" ትላለች መንገድ ላይ ከማያውቁት ሰው የእንተዋወቅ ጥያቄ መቀበል የተለመደ ነገር መሆኑን ስታስረዳ። ነገር ግን ከሰዎቹ ጋር የሚደረጉት ንግግሮች ይቀረጻሉ ብሎ ማሰቡ "አስከፊ እና አስደንጋጭ" ነገር መሆኑን ትናገራለች።
ቢቢሲ ቪዲዮው የተለጠፈበትን የቲክቶክ አካውንት ባለቤት ለማግኘት ቢሞክርም ምላሽ አላገኘም። ኡናን የቀረጻት ሰው በቲክቶክ ገጹ ላይ ከመቶ በላይ ተመሳሳይ ቪዲዮዎችን ለጥፏል። እንዲህ ዓይነት ቪዲዮችን የሚቀርጸው ግን እርሱ ብቻ አይደለም።
ኬት የተባለች ሌላ ሴትም በተመሳሳይ ስማርት መነጽር ባደረገ ሰው ተቀርጻለች። ጂም ውስጥ እያለች አንድ ሰው ቀርቦ ስልኳን የጠየቃት ሲሆን፣ እሷን ፈቃደኛ አለመሆኗን ገልጻለች።
በማግስቱ ይህ ንግግራቸው ቲክቶክ ላይ ተላከላት። ቪዲዮው በተለጠፈ በስድስት ሰዓት ውስጥ 50,000 ዕይታዎችን አገኘ። ቪዲዮው ሥር የተሰጡት አብዛኛዎቹ አስተያየቶች የኬትን መልክ እና ባህሪ የሚያንጓጥጡ እና አጸያፊ ነበሩ።
"ጭንቀት ውስጥ ነኝ። ሰዎች የሚታየው ነገር በሙሉ ያለፈቃዴ መደረጉን ሳያውቁ ኦንላይን ላይ ያፌዙብኛል" ትላለች። ኬት በቀረጻት ሰው እጅግ እንደተናደደች ተናግራለች።
"ይህ ሁሉ የሚደረገው ኦንላይን ላይ ዕይታ ለማግኘት ነው። ከዚያም በርካታ መጥፎ አስተያየቶች ይሰጡብሻል። እነዚህም በራስ መተመንሽን፣ ለራስሽ ያለሽንም ግምት ይጎዳሉ" ስትል ተጽዕኖውን ገልጻለች።
ኬት ቀደም ሲል ሁለት ጊዜ ፆታ ጥቃት እንደደረሰባት ለቢቢሲ ተናግራለች።
"አንዳንድ ጊዜ የአእምሮ ጤንነትሽ ደህና እየሆነ እንደሆነ ይሰማሻል፤ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች መልሰው ይፈጠራሉ" ብላለች።
ቲክቶክ ላይ ሪፖርት ከተደረገለት በኋላ የኡና እና የኬትን ቪዲዮዎች የለጠፉትን አካውንቶች ዘግቷል።
ስማርት መነጽሮች ያለፈቃድ ሰዎችን ለመቅረጽ ጥቅም ላይ መዋላቸው "አሳዛኝ" ነግር ግን "የሚጠበቅ ነገር" እንደሆነ ይናገራሉ።
"እንደዚህ ዓይነት መነጽሮች በአጥቂዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ወይም ሴቶች ደኅንነት እንዳይሰማቸው እና እንዲዋረዱ ለሚያደርጉ ጎጂ ወሲባዊ ድርጊቶች መገልገያ እንደሚሆኑ ግልጽ ነበር" ይላሉ።
ጎግል ግላስ (Google Glass) የተባለው የመጀመሪያው ስማርት መነጽር በ1,000 ፓውንድ ለዩናይትድ ኪንግደም ገበያ የቀረበው በአውሮፓውያኑ 2014 ነበር።
የሰዎች ግላዊ ነጻነት ላይ በሚፈጥረው ስጋት የተነሳ ግን ከሰባት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ግን በ2015 ሽያጩ ቆመ። አንዳንድ መጠጥ እና ምግብ ቤቶችም ሰዎች ቅጥሮቻቸው ውስጥ መነጽሩን እንዳያደርጉ አግደው ነበር።
አሁን ደግሞ ጎግል በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የታገዙ መነጽሮችን በዚህ ዓመት ለገበያ ለማቅረብ አቅዷል።
በጊዜ ሂደት ስማርት መነጽሮች መደበኛዎቹን መነጽሮች እንዲመስሉ ተደርገው እየተሠሩ ነው። ይህ አሠራር ሰዎች ቴክኖሎጂውን ለመለየት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው እንደሚያደርግ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።
የዋትስአፕ፣ የፌስቡክ እና የኢንስታግራም ባለቤት የሆነው ሜታ ስማርት መነጽሮችን መሸጥ የጀመረው በ2021 ነበር። ከየካቲት 2014 ጀምሮም ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ መነጽሮችን ሸጧል።
ኩባንያው የሚያመርታቸው መነጽሮች ቀረጻ ሲጀመር የሚበራ "ኤልኢዲ መብራት" እንዳላቸው ይናገራል። "ስለዚህ መገጽሩ እየቀረጸ መሆኑ ለሌሎች ግልጽ ይሆናል" ይላል። እንዲሁም "ሰዎች መብራቱን እንዳይሸፍኑት የሚከላከል ቴክኖሎጂ" እንዳለውም ገልጿል።
ይሁን እንጂ እንዴት የመነጽሩን መብራት አጥፍቶ በድብቅ ለመቅረጽ እንደሚቻል የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ጽሁፎች በይነ መረብ ላይ በብዛት ይገኛሉ። ቢቢሲ ኢንተርኔተር ላይ የሚገኙትን ዘዴዎች በመጠቀም መብራቱ ሳይበራ መቅረጽ እንደሚቻል አረጋግጧል።
ኡናም ሆነች ኬት በተቀረጹበት ወቅት መነጽሩ ላይ ምንም ዓይነት መብራት እንዳልተመለከቱ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ይህንን ግኝቱን ለሜታ አቅርቧል። ሜታ "በተገልጋዮች አስተያየት እና እየተደረገ ባለው ምርምር መሠረት የኤአይ መነጽራችንን ለማሻሻል የሚያስችሉ ዕድሎችን ሳናቋርጥ እንመለከታለን" የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
'ስማርት መነጽሮች ጠቃሚ ናቸው'
ግላዊ ተብለው የሚቆጠሩ ነገሮችን እስካልቀረጹ ድረስ፤ በአጠቃላይ በሕዝብ ቦታዎች ሰዎችን መቅረጽ ሕጋዊ ተግባር ነው። ነገር ግን ግላዊ ተብለው የሚታሰቡ ድርጊቶችን መቅረጽ በትንኮሳ ወይም ሰዎች ላይ በማድባት (stalking) ወንጀል ሊያስጠይቅ ይችላል።
በኬንት ዩኒቨርሲቲ የሳይበር ደኅንነት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ጄሰን ነርስ፤ "አንዱ ችግር ሕግ ከቴክኖሎጂው ጀርባ ሆኖ የሚጎተት መሆኑ ነው" ይላሉ።
"ስማርት መነጽሮች ጠቃሚ መሆናቸውን አምናለሁ" ሲሉ ምልከታቸውን ተናግረዋል። ለአካል ጉዳተኞች፣ ለቱሪዝም እና ለአጠቃላይ ምቾት እንደሚረዱ የሚያምኑት ተመራማሪው፤ "ለክፉ ዓላማ የሚጠቀሙባቸው ሰዎች ሊኖሩን አይገባም" ብለዋል።
"ጥቃት ፈጻሚዎች" ጉዳት የሚያደርሱ ከሆነ በሕግ እንደሚጠየቁ "እጅግ ግልጽ በሆነ መንገድ ልናሳውቅ ይገባል" ሲሉ ምክረ ሀሳባቸውን ጠቁመዋል።
ስማርት መነጽሮችን ለመለየት አስቸጋሪ እየሆኑ መምጣታቸው፤ "ብዙ ሰዎች ሊያደርጉት የሚገባውን ጥንቃቄ እንዳይፈጽሙ ሊያደርጋቸው ይችላል" ሲሉ ነርስ ያስጠነቅቃሉ።
ሜታ በበኩሉ፣ ልክ እንደማንኛውም የመቅጃ መሳሪያ ሁሉ ስማርት መነጽሮችን የሚጠቀሙ ሰዎች እንደ "ትንኮሳ፣ የግል ነጻነትን መጋፋት ወይም ምሥጢራዊ መረጃዎችን መቅዳት ባሉ ጎጂ ተግባራትን" መፈጸም እንደሌለባቸው ገልጿል።
ጎግል መነጽሮቹ ስለደቀኑት ስጋት ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።