ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግሮክን በመጠቀም የሰዎች ፎቶ ወደ እርቃን ምስል የሚቀየርበት አሰራርን እንደሚያቆም ኤክስ አስታወቀ
የኢላን መስክ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ቴክኖሎጂ የሆነው ግሮክን በመጠቀም የሰዎች ፎቶ ወደ እርቃ ምስል የሚቀየርበትን አገልግሎት እንደሚያቆም አስታወቀ።
የሰዎች ትክክለኛ ፎቶ ወሲባዊ ተደርጎ መሠራቱን ተከትሎ ነው ጉዳዩ ሕግን የሚጥስ ነው የሚል ከፍተኛ ወቀሳ የደረሰበት።
"ግሮክ ከዚህ በኋላ ትክክለኛ የሰዎችን ፎቶ ወስዶ በሚያጋልጡ ልብሶች እንዳያደርግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ አድርገናል" ሲል የግሮክ ኤአይ መተግበሪያ የሆነው ኤክስ አስታውቋል።
"ይህ መመሪያ ከፍለው ለሚጠቀሙና ለሌሎችም ተጠቃሚዎች የሚሠራ ነው" ይላል መግለጫው።
የካሊፎርኒያ ግዛት አቃቤ ሕግ የሕፃናትን ፎቶ ጨምሮ የሰዎች ትክክለኛ ፎቶ ወሲባዊ ይዘት እንዲይዝ ተደርጎ በግሮክ አማካይነት እየተሠራ ነው የሚል ምርመራ መጀመሩን ተከትሎ ነው ኤክስ የቴክኖሎጂ ለውጥ ማድረጉን ያስታወቀው።
"ይህ ጉዳይ ሕገ-ወጥ በሆነባቸው ቦታዎች ሁሉ ግሮክ የሰዎችን ትክክለኛ ፎቶ በውስጥ ልብስ እና በሌሎች ተመሳሳይ የሚያጋልጡ ልብሶች ማድረግ እንዳይችል አድርገናል" ይላል የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ መግለጫ።
ኤክስ አክሎ ከዚህ በኋላ ከፍለው የሚጠቀሙ ተጠቃሚዎች ብቻ ናቸው ፎቶ 'ኤዲት' ማድረግ የሚችሉት ብሏል።
መተግበሪያው ይህን ያደረገው የኤክስን መመሪያ በሚጥስ መልኩ ግሮክን የሚጠቀሙ ሰዎችን ለማገድ እንደሆነ በመግለጫው አስታውቋል።
ኢላን መስክ ረቡዕ በኤክስ ገፁ በፃፈው መሠረት ልክ ለአዋቂዎች በሚዘጋጁ ፊልሞች ላይ እንደምናየው "የአዋቂ ሰዎችን (ትክክለኛ ያልሆኑ) ከወገብ በላይ እርቃት ማሳየት ግን ይቻላል" ብሏል።
"ይህ አሜሪካ ውስጥ የሚሠራበት አሠራር ነው። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ እንደ ሀገራቱ ሕግና መመሪያ ሁኔታዎች የሚቀያየሩ ይሆናሉ" ሲሉ አክሏል።
የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር በውስጥ ልብስ ሆነው የሚያሳይ ፎቶ በግሮክ መሠራቱን ተከትሎ ለተነሳው ተቃውሞ ኢላን መስክ "ሰዎች የንግግር ነፃነትን ማገድ ነው የሚፈልጉት" የሚል ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።
በተለይ ባለፉት ጥቂት ቀናት ተጠቃሚዎች በግሮክ አማካይነት የሰዎችን ትክክለኛ ፎቶ ወስደው እንደፈቀዱ ኤዲት ማድረጋቸውን በርካታ ሀገራት ተቃውመዋል።
የሰዎች ፎቶ እርቃናዊ በሆነ መንገድ ተበዝብዟል በማለት ማሌዢያና ኢንዶኔዥያ ግሮክን በማገድ የመጀመሪያዎቹ ሀገራት ሆነዋል።
የብሪታኒያው የሚድያ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ኦፍኮም በበኩሉ ኤክስ የዩኬን ሕግ ጥሶ እንደሆን ለማጣራት ምርመራ መጀመሩን ያስታወቀው ባለፈው ሰኞ ነው።
ሰር ኪር ስታርመር ኤክስን ቢያስጠነቀቁም መተግበሪያው ለውጥ ማድረጉን በደስታ እንደሚቀበሉ ተናግረዋል።
ኤክስ አዲሱን መመሪያውን እንዴት ነው ተግባራዊ የሚያደርገው የሚለው አሁን ጥያቄ ሆኗል። ግሮክ የሰዎች ትክክለኛ ፎቶና ሀሰተኛ ፎቶዎችን እንዴት ነው የሚለየው ሲሉ ብዙዎች ይጠይቃሉ።