"የባሕር በር ካላገኘን ጦርነት ይኖራል" ያሉት የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት እና የኬንያ ስጋት

የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባል አገራት የሆኑት ኬንያ እና ኡጋንዳ በባሕር በር ዙሪያ በቀረበ ጠንካራ አስተያያት ምክንያት በከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው መካከል የቃላት ምልልስ ውስጥ ገብተዋል።

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሩ ሙሴቪኒ ከአንድ ሳምንት በፊት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ አገራቸው በኬንያ በኩል "የሕንድ ውቅያኖስ ይገባታል" ብለው በይፋ መናገራቸው በአካባቢው ምን ያስከትል ይሆን የሚል ስጋት ቀስቅሷል።

የፕሬዝዳንቱን ጠንከር ያለ ጥያቄን እና ፈርጣማ አቋምን ተከትሎ አንዳንዶች በምሥራቅ አፍሪካ አገራቱ መካከል ወደፊት ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል እያሉ ነው።

ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ይህንን የተናገሩት ቅዳሜ ጥቅምት 29/2018 ዓ.ም. በሰጡት እና በአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈው ቃለ መጠይቃቸው ላይ ነው።

ቃለ ምልልሱ የተካሄደው የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ በነበረበት በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በምትገኘው ምባሌ ከተማ ነበር።

ፕሬዝዳንቱ በቃለ መጠይቃቸው ላይ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የመከላከያ እና የምጣኔ ሃብት ጥንካሬ ውህደትን ባብራሩበት ወቅት የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይን አንስተዋል።

ሙሴቬኒ አራቱ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በኢኮኖሚያቸው ስፋት መሠረት ወታደራዊ እና የጠፈር ምርምርን ጨምሮ የቴክኖሎጂ እድገት እንዳላቸው ተናግረዋል።

"አፍሪካ እንዴት ራሷን መከላከል ትችላለች? የምጣኔ ሃብት ውህደት ኢኮኖሚውን ያግዛል" ሲሉ ተናግረዋል።

"ለዚህ ነው ለሰዎች የምነግራቸው። ለምን አንድ መሆን እንዳለብን አታዩም? ምክንያቱም... ኡጋንዳ የባሕር ኃይል ማደራጀት ከፈለገች እንዴት ልትገነባ ትችላለች? እኛ ባሕር የለንም" ሲሉ ወደ ዋናው ጥያቄያቸው ተንደርድረዋል።

ኬንያ የኡጋንዳ ቁልፍ የንግድ እና የአቅርቦት አጋር ብትሆንም በጋራ የነዳጅ ማስተላለፊያ፣ መንገድ ለመገንባት እንዲሁም የባቡር መስመር ለመዘርጋት ተይዘው የነበሩ የፕሮጀክት ዕቅዶች እስካሁን ድረስ ተግባራዊ አልሆኑም።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን በተመለከተ ሲናገሩ "ማብቂያ የሌለው ንግግር ከኬንያ ጋር አድርገናል...በባቡሩ መስመር፣ በነዳጅ ማስተላለፊያ ግንባታ፤ ምክንያቱም አገራችን በተፈጥሮ የባሕር በር የላትም። ነገር ግን ውቅያኖሱ ለእኔም ይገባኛል። ምክንያቱም የእኔ ውቅያኖስ የት አለ? ያ ውቅያኖስ ይገባኛል። ወደፊት ጦርነት ይኖረናል። ወደፊት ወደ ጦርነት መግባታችን አይቀርም።"

ይህ የሙሴቬኔ አስተያየት በኬንያ ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች እና በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ላይ የውይይት እና የዘገባ ምንጭ ከመሆን አልፎ ቁጣንም እያስተናገደ ነው።

በኬንያ የወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ኮሪር ሲንጎይ በሰጡት ምላሽ አገራቸው በዓለም አቀፍ ሕግ እንዲሁም የግዛት መብትን እና የተፈጥሮ ሃብትን ለሚመለከቱ የሕግ ማዕቀፎች እንደምትገዛ በመጥቀስ የኡጋንዳ መሪ ሃሳብ ከሕግ ውጪ መሆኑን አመለክተዋል።

ኡጋንዳ የባሕር በር የሌላት አገር ስትሆን ፕሬዝዳንቷ ዩዌሪ ሙሴቪኒ የባሕር ኃይል ስለመገንባት ያላቸውን ፍላጎት እንዲሁም የሕንድ ውቅያኖስን ያለምንም ገደብ የመጠቀም ፍላጎታቸውን ሲናገሩ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ አዲስ ስጋትን ፈጥሯል።

ሙሴቬኒ ኡጋንዳ በባሕር ዳርቻ ከሚገኙ ጎረቤቶች ኬንያ እና ታንዛኒያ ጋር ወጥ በሆነ መልኩ የባሕር ላይ መብት እንዳላት በመግለጽ ያ የማይቻል ከሆነ ወታደራዊ እርምጃዎችን ሊኖሩ አንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።

"የእኔ ባሕር የሕንድ ውቅያኖስ ነው" ያሉት ሙሴቪኒ፣ አገሪቱ ያላትን የወደብ ማግኘት ጥያቄ ፍለጋ ከዲፕሎማሲ ይልቅ የብሔራዊ መብት ጉዳይ አድርገው አቅርበዋል።

እንዲሁም ውቅያኖሶች እና ወደቦች መላውን አህጉር ማገልገል አለባቸው በማለት አንዳንድ የባሕር በር ያላቸው አገራትን "በራስ ወዳድነት አስተሳሰብ" ተችተዋል።

ሙሴቪኒ እና ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከ2024 ጀምሮ ከምዕረብ ኬንያ ኤልዶሬት ተነስቶ የኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ የሚደርስ የነዳጅ ማስተላለፊያ ለመዘርጋት ንግግሮች አድርገዋል።

በመጋቢት 2024 ኬንያ የኡጋንዳው ብሔራዊ ነዳጅ ድርጅት የኬንያ ነዳጅ ማስተላለፊያን በመጠቀም በሞምባሳ ወደብ በቀጥታ የተጣራ ፔትሮሎየም እንዲያስገባ ፈቃድ ሰጥታለች።

የዚህ ውሳኔ ዓላማ የነበረው በኡጋንዳ ያለውን የነዳጅ ዋጋ ዝቅተኛ ማድረግ ነበር።

ዘ ስታር የተሰኘው የኬንያ ጋዜጣ "ይህ ኬንያ የኡጋንዳ የንግድ መስመርን ተቆጣጥራ መቆየቷ የፈጠረው የከረመ ብሶት ነው" ሲል ዘግቧል።

"በኬንያ የኡጋንዳ የንግድ መስመሮችን በመቆጣጠር ላይ ያለውን ጥልቅ ብስጭት የሚያንፀባርቁ ናቸው" ብሏል።

አክሎም "የክልላዊ ውህደት ጥሪዎችን ሲያቀርቡ የነበሩት ፕሬዝዳንቱ [ሙሴቬኒ]፣ ድምፀታቸው መቀየሩ ትዕግስት ማጣታቸውን እና በኬንያ ላይ የከረመ ስጋቶችን እንዳላቸው ያሳያል" ብሏል።

በተጨማሪም "አስተያየታቸው ከኤልዶሬት እእስከ ካምፓላ ያለ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ እና እንደ ሚጊንጎ ደሴት ባሉ የቆዩ ውዝግቦች ላይ ውጥረት መኖሩን ያሳያል።"

ሌሎች የኬንያ ጋዜጦችም ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር የመጣው ኬንያ የኡጋንዳን የንግድ መስመር ተቆጣጥራ መቆየቷ የፈጠረው የከረመ ብሶት ነው ሲሉ ዘግበዋል።

ኡጋንዳ የባሕር በር የሌላት አገር ስትሆን ፕሬዝዳንቷ የባሕር በር ስለማግኘት የሰጡት አስተያየት በባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ወደፊት ከኬንያ ጋር ጦርነት ልትገባ ትችላለች የሚል ፍራቻ ቀስቅሷል።

"የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በኬንያ ላይ ያነጣጠረ በመሰለ የተሸፈነ ስጋት ውስጥ ወደፊት ወደ ሕንድ ውቅያኖስ መግባትን ለማረጋገጥ በምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ውስጥ ስለሚደረጉ ጦርነቶች አስጠንቅቀዋል" ሲል ዘ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል።

ኡጋንዳ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ስታቀርብ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ በአምባገነኑ በኤዲ አሚን ዳዳ የሥልጣን ዘመን ተመሳሳይ ጥያቄዎች እና ዛቻዎች ኬንያ ላይ ተሰንዝረው ነበር።

በአውሮፓውያኑ የካቲት 1976 ኢዲ አሚን የኬንያን ሠፊ ክፍል በኃይል ጠቅልሎ ለመያዝ ዝተው፣ ከናይሮቢ በ32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ስፍራንም ይገባኛል ሲል ተናግረው ነበር።

በተለያዩ ጊዜያት በሁለቱ አገራት መካከል በባሕር በር የማግኘት ሰበብ የሚነሱ ውጥረቶች ግን ወደ ወታደራዊ እርምጃ አልተሸጋገሩም።

ናይሮቢ ለካምፓላ የንግድ ፍላጎት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው በሚል ወደ ሕንድ ውቅያኖስ የሚያደርሳትን አጭር መንገድ ኪሱሙን በቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ ከሞምባሳ ወደብ ጋር የሚያገናኘው የባቡር ሀዲድ መስመር ዝርጋታ አማራጭ ሰጥታለች።

ኡጋንዳ ግን ሌላ አማራጭ መስመሮችን የፈለገች ሲሆን፣ ከሆይማ ታንዛኒያ ወደ ሚገኘው ታንጋ ወደብ የነዳጅ መስመር ዝርጋታን በመጠየቀወ ይህም ውጥረትን ፈጥሮ ቆይቷል።

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ ሙሁዚ ካይኔሩጋባ በ2022 ጎረቤት አገር ኬንያን እወራለሁ የሚል ሃሳብ መሰነዘራቸውን ተከትሎ አባታቸው ሙሴቬኒ ጣልቃ ገብተው ይቅርታ መጠየቃቸው የሚዘነጋ አይደለም።

ኡጋንዳ ከታንዛኒያ ጋር በተናጠል 4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የድፍድፍ ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር እየገነባች ነው።

ይህ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር 1443 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን ከዳሬሰላም ወደብ የሚነሳ ነው።

ሥልጣን ላይ ከወጡ አርባ ዓመት ሊሞላቸው የተቃረቡት የ81 ዓመቱ አዛውንት ሙሴቪኒ በቀጣይ ዓመት ለሌላ ዙር የሥልጣን ዘመን ለምርጫ ይቀርባሉ።

በዚህ ጊዜ ይህንን የባሕር በር ጉዳይ ማንሳታቸው የሕዝብ ትኩረት እና ድጋፍን ለማግኘት የታለመ ነው የሚሉ ታዛቢዎች ቢኖሩም፣ አገራቸው ከኬንያ ጋር ባላት መልካም ግንኙነት ላይ አስጊ ጥላን አጥልቶበታል።