በምዕራብ ወለጋ 11 የቴሌኮም ሠራተኞች ታግተው ከፍተኛ የማስለቀቂያ ገንዘብ ተጠየቀባቸው

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ ሥራ ላይ የነበሩ አስራ አንድ የኢትዮ ቴሌኮም እና የዜድቲኢ ሠራተኞችን አግተው መውሰዳቸው ተነገረ።

ባለፈው ሳምንት በተለያዩ ቀናት በታጣቂዎቹ የታገቱት ሠራተኞችን ለመልቀቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መጠየቁም ተገልጿል።

ታጣቂዎቹ የመጀመሪያውን ዕገታ የፈጸሙት ባለፈው ሳምንት አርብ ጥር 1/2018 ዓ.ም. ቂልጡ ካራ በተባለ ወረዳ ውስጥ የሞባይል ኔትዎርክ ማስፋፊያ ሥራ እያከናወኑ በነበሩ የመንግሥታዊው የቴሌኮም ተቋም እና የቻይናው ኩባንያ ባልደረቦች ላይ ነው።

በዕገታው ከተያዙት ውስጥ አምስቱ የዜድቲኢ ባልደረቦች ሲሆኑ፣ ሁለቱ ደግሞ የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞች መሆናቸው ታውቋል።

ሰባቱ ባለሙያዎች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ተይዘው መወሰዳቸውን ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የኢትዮ ቴሌኮም ምንጭ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

"አርብ ረፋድ አራት ሰዓት ላይ በሥራ ላይ እያሉ ነው የታገቱት። ሠራተኞቹ እቃዎቻቸውን እና መኪናቸውን ትተው ተወስደዋል። የት እንደተወሰዱ ምንም መረጃ የለንም" ሲሉ ምንጩ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በቀጣዩ ቀን ቅዳሜ ጥር 2/2018 ዓ.ም. ደግሞ ሌሎች አራት ሠራተኞች እዚያው ምዕራብ ወለጋ ቦጂ ዲርመጂ ወረዳ ውስጥ በታጣቂዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

ከአጋቾቹ መካከል የተወሰኑት የተያዙትን አራት ሰዎች ለመልቀቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር እንዲከፈላቸው ዜድቲኢን መጠየቃቸው ተነግሯል።

በቅዳሜው ዕገታ በታጣቂዎቹ ከተያዙት አራት የቴሌኮም ኩባንያዎቹ ሠራተኞች መካከል ሦስቱ የዜድቲኢ ሠራተኞች ሲሆኑ አንዱ የኢትዮቴሌኮም ሠራተኛ መሆኑ ታውቋል።

"በቂልጡ ካራ ወረዳ ያሉት ሁሉም ሠራተኞች ተይዘዋል። ያገቷቸው ታጣቂዎች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል" ሲሉ ምንጩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ስለተከሰተው እገታ እና መንግሥት ሠራተኞቹን ለማስለቀቅ እየወሰደ ስላለው እርምጃ የወረዳውን አስተዳደር አስተያየት በስልክ ለመጠየቅ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

በተጨማሪም ዕገታው በተፈጸመበት አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሪዎችን ስለ እገታው ለመጠየቅ የተደረገው ጥረት ምላሽ አላገኘም።

ታጣቂዎቹ ዕገታውን የፈጸሙት፤ ኢትዮ ቴሌኮም በአካባቢው ያለውን 5% እስከ 12% የሚደረስ የ4ጂ የቴሌኮም ሽፋን ወደ 82% በመቶ ለማሳደግ እየሠራ ባለበት ሰዓት እንደሆነ ባለሥልጣኑ ገልጸዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ከቻይናው ኩባንያ ጋር በመሆን በአካባቢው ያለውን የኔትወርክ ሽፋን ለማስፋት ከፍተኛ ገንዘብ መድቦ ባለፉት ሁለት ወራት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በተቋማት እና በንብረት ላይ በተለያዩ ጊዜያት ጥቃቶችን ከመፈጸማቸው በተጨማሪ ዕገታዎችን በመፈጸም ማስለቀቂያ ገንዘብ እንደሚፈጽሙ በተለያዩ ጊዜያት ተዘግቧል።

የቡድኑ አመራሮች ግን ዕገታውን የሚፈጽሙት አባላቱ ሳይሆኑ ሌሎች ታጣቂዎች ናቸው ሲሉ በተደጋጋሚ ያስተባብላሉ።