ትራምፕ በምን ዓይነት መንገድ ግሪንላንድን "ሊጠቀልሉ" ይችላሉ?

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን መጠቅለል እንደሚፈልጉ በግልጽ ተናግረዋል፤ ዋይት ሐውስም የኃይል እርምጃን ጨምሮ ሁሉም አማራጮች ጠረጴዛ ላይ መሆናቸውን አረጋግጧል።

ወታደራዊ እርምጃ የአሜሪካ መንግሥት ሊወስድ ከሚችላቸው ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አማራጮች እንደ አንዱ የሚቆጠር ነው። ነገር ግን ይህ ወታደራዊ እርምጃ አንድ የኔቶ አባል ሀገር በሌላኛው ላይ የሚፈጽመው ስለሚሆን ጉዳዩን ለኔቶ ጥምረት አስከፊ መዘዝ ይኖረዋል፤ የጥምረቱ ኅልውና ላይም አደጋ ሊደቅን ይችላል።

ትራምፕ ግሪንላንድ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ወሳኝ መሆኗን ደጋግመው ገልጸዋል። ደሴቷ "ሁሉም ቦታ በሩሲያ እና በቻይና መርከቦች ተሸፍናለች" ሲሉም ማስረጃ ሳያቀርቡ ከስሰዋል።

በዚህ ዘገባ በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በዴንማርክ ባለሙያዎች በመታገዝ ፕሬዝዳንቱ ሊከተሏቸው የሚችሏቸውን አማራጮች እና ለእያንዳንዳቸው ምን ማሳመኛ ምክንያቶች ሊቀርቡ እንደሚችሉ ዳስሰናል።

ወታደራዊ እርምጃ

የመከላከያ ተንታኞች እንደሚናገሩት፤ ግሪንላንድን በድንገተኛ ወታደራዊ ጥቃት መቆጣጠር በአንጻራዊነት ቀላል ቢሆንም እጅግ ከፍተኛ መዘዝ ያስከትላል።

ግሪንላንድ በቆዳ ስፋት ግዙፍ ብትሆንም የሕዝብ ቁጥሯ 58,000 አካባቢ ብቻ ነው። ከዚህ ውስጥ አንድ ሦስተኛው የሚኖረው በዋና ከተማዋ ኑክ ሲሆን ቀሪው ደግሞ ኑሮውን ያደረገው በምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ ነው።

ግሪንላንድ የራሷ ወታደራዊ ኃይል የላትም። በደሴቲቷ የወታደራዊ ጉዳዮችን ኃላፊነት የወሰደችው ዴንማርክ ደግሞ ያላት የአየር እና የባሕር ኃይል እንዲህ ያለውን ሰፊ ግዛት ለመጠበቅ ውስንነት አለበት።

አብዛኛው ግዛት የሚጠበቀው በውሻ የሚጎተቱ እና በረዶ ላይ የሚንሸራተቱ ጋሪዎችን በሚጠቀመው "ሲሪየስ ፓትሮል" በተባለ የዴንማርክ ልዩ ኃይል ነው።

ይሁን እንጂ ዴንማርክ በአርክቲክ እና በሰሜን አትላንቲክ አካባቢ የምታውለውን የመከላከያ ወጪ ባለፈው ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምራለች።

ግሪንላንድ ግዙፍ የቆዳ ስፋት ያለት፣ የሕዝብ ቁጥሯ አነስተኛ እንዲሁም የራሷ የጦር ኃይል የሌላት መሆኑ ለአሜሪካ ዒላማ ምቹ ያደርጋታል። አሜሪካ አሁን ራሱ በግሪንላንድ ሰሜናዊ ምዕራብ ጫፍ በሚገኘው የፒቱፊክ ጣቢያ በቋሚነት የሰፈሩ ከ100 በላይ ወታደሮች አሏት።

በሀሳብ ደረጃ ይህ ጣቢያ ለወደፊት ዘመቻዎች እንደ የሎጂስቲክስ ማዕከል ሊያገለግል እንደሚችል ይገመታል።

ወታደራዊ ሰፈሩ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተመሠረተ ነው። የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ደሴቷ ያመሩት፤ ዴንማርክ በናዚ መያዟን ተከትሎ ግሪንላንድ ላይ ሠራዊት እና የራዲዮ ጣቢያ እንዲያቋቁሙ ነበር።

የዴንማርክ የደኅንነት ባለሙያ እና የ'ሪስክ ኢንተለጀንስ' ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ሃንስ ቲቶ ሀንሰን፤ አሜሪካ በምን ዓይነት ዘመቻ ግሪንላንድን ልትይዝ እንደምትችል ያስረዳሉ።

እንደ ሀንሰን ገለጻ አሜሪካ ወረራ የምትፈጽም ከሆነ "ዋነኛ አቅም" በመሆን "የአየር እና የባሕር ኃይል ድጋፍ" የሚሰጠው በአላስካ የሚገኘው 11ኛ የአየር ወለድ ክፍለ ጦር ነው። ይህ ክፍለ ጦር በአየር ወለድ ተልዕኮዎች ወቅት ፓራሹት እና ሄሊኮፕተር መጠቀም የሚችሉ ሁለት ብርጌዶች ጭምር እንዳሉት ይገልጻሉ።

'ሲብላይን' የተሰኘውን የስጋት እና ደኅንነት መረጃ ኩባንያ የሚመሩት ብሪታኒያዊው ጀስቲን ክራምፕም ይህንን ትንተና ይጋሩታል።

አሜሪካ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር በአየር የማጓጓዝ አቅም እንዳላት የሚጠቁሙት ክራምፕ፤ "በአንድ ጉዞ ብቻ ለእያንዳንዱ ጥቂት የደሴቱ ነዋሪዎች አንድ ወታደር እንዲመደብ የሚያስችል ብዛት ያላቸው ወታደሮችን በቀላሉ በአየር ማጓጓዝ ትችላለች" ይላሉ።

ክራምፕ ይህ አካሄድ ርህራሄ የለሽ ሊሆን እንደሚችል ቢያምኑበትም፤ ነገር ግን ምንም ዓይነት ተቃውሞ ሊገጥመው ስለማይችል ያለምንም ደም መፋሰስ ሊፈጸም እንደሚችል ተናግረዋል።

በአሜሪካ ውስጥ ያሉ የቀድሞ ባለሥልጣናት እና ወታደራዊ ተንታኞች ግን ይህ ዓይነቱ እርምጃ ዋሽንግተን ከአውሮፓ አጋሮቿ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ስለሚኖረው ይሆናል ብለው እንደማያምኑ ያስረዳሉ።

የቀድሞ ወታደር፣ የሲአይኤ ልዩ ኃይል አባል እና የመከላከያ ረዳት ሚኒስትር ሚክ ሙልሮይ፤ "ይህ [እርምጃ] ሁሉንም ዓለም አቀፍ ሕግን የሚቃረን ነው። [ግሪንላንድ] ለእኛ ስጋት አይደሉም፤ የስምምነት አጋሮቻችን ናቸው" ብለዋል።

ሙልሮይ የዋይት ሐውስ አካሄድ ወደ ወታደራዊ እርምጃ የሚያነዘብል ከሆነ፤ 'ዋር ፓውርስ' የተባለውን ሕግ ከሚያነሱ የኮንግረስ አባላት ተቃውሞ ይገጥመዋል የሚል እምነት አላቸው።

ይህ ሕግ ፕሬዝዳንቱ ያለ ኮንግረስ ፈቃድ አንድ ነገር ከመፈጠሩ አስቀድሞ ለመከላከል በሚል ጦርነት የሚያውጅበትን አቅም የሚገድብ ነው።

"ኮንግረስ ውስጥ የኔቶን ጥምረት መፍረስ የሚደግፍ ምንም ዓይነት ድጋፍ ይኖራል ብዬ አላስብም" ብለዋል።

ግሪንላንድን መግዛት

ምንም እንኳ አሜሪካ ከፍተኛ ሀብት ቢኖራትም ግሪንላንድ እና ዴንማርክ ደሴቲቷ ለሽያጭ እንደማትቀርብ አስረግጠው ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ለትራምፕ አስተዳደር ተመራጩ አካሄድ ግሪንላንድን መግዛት እንደሆነ ለኮንግረስ አባላት መናገራቸውን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ሕግ አውጪዎችን እና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮችን ጠቅሶ ያወጣው ዘገባ አመልክቷል።

ሩቢዮ ይፋ ያደረጉት ይህ ሀሳብ ዋይት ሐውስ ጉዳዩን እያቀረበበት ካለው አኳኋን በእጅጉ የተለየ ነው።

ግሪንላንድ ለመሸጥ ብትስማማ እንኳ ሂደቱ እጅግ ውስብስብ ነው። ማንኛውም ክፍያ በኮንግረስ መጽደቅ አለበት። ግሪንላንድን ለመግዛት የሚደረግ ስምምነትም በሁለት ሦስተኛዎቹ የሴኔት አባላት ድጋፍ መጽቀድ ይኖርበታል።

የአውሮፓ ኅብረትም በስምምነቱ ላይ መስማማት አለበት። ባለሙያዎች እንደሚናገሩት እነዚህን ሂደቶች ማሳካት አስቸጋሪ ነው።

በሀሳብ ደረጃ ትራምፕ ግሪንላንድን ወይም ኮንግረስን ሳያካትቱ በራሳቸው ብቻ ስምምነት ለመፈጸም ሊሞክሩ ቢችሉም ባለሙያዎች ግን ይህ የመሆን ዕድሉ እጅግ አነስተኛ ነው የሚል እምነት አላቸው።

በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ሞኒካ ሀኪሚ ዴንማርክ፣ አሜሪካ እና ግሪንላንድ ግዛቱን ለማዛወር በሁኔታዎች ላይ የሚስማሙበት ሁኔታ "ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ሊታሰብ እንደሚችል" ያስረዳሉ።

"[ነገር ግን] ስምምነቱ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣም እንዲሆን ለራሳቸው ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት ሲባል የግሪንላንድ ተሳትፎ ሊኖርበት ይገባል" ሲሉ አብራርተዋል።

ግሪንላንድን ለመግዛት ምን ያህል ወጪ ሊጠይቅ እንደሚችል ግን ግልጽ አይደለም። ይህ ጉዳይ ደግሞ "አሜሪካ ትቅደም" የሚል መፈክር አንግበው ለተቀሰቀሱት ትራምፕ ሁኔታዎችን ሊያወሳስብ ይችላል።

በቢሊዮን ወይም በትሪሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካ ታክስ ከፋይ ገንዘብ በበረዶ በተሸፈነችው ደሴት ላይ ይውላል የሚለው ሀሳብ በትራምፕ ደጋፊዎች ዘንድ መጥፎ አቀባበል ሊኖረው ይችላል።

የደኅንነት ተንታኙ ክራምፕ፤ ደሴቷን የመግዛቱ ሙከራ የማይሳካ ከሆነ ትራምፕ ወታደራዊ አማራጭ የተሻለ ሆኖ ሊታያቸው እንደሚችል ያምናሉ።

በተለይም ይህ ጉዳይ እየተነሳ ያለው የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ለመያዝ የተከናወነው የተሳካ ዘመቻ ግፊት በፈጠረበት በዚህ ወቅት ወታደራዊ አማራጭን የበለጠ ሳቢ ሊያደርገው እንደሚችል ይጠቁማሉ።

ክራምፕ ስለ ትራምፕ ሲናገሩ "'እንግዲያውስ፤ ዝም ብለን እንወስዳታለን' ሊሉ ይችላሉ" ይላሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ፤ ትራምፕ "ግሪንላንድን እንዴት ልናገኝ እንደምንችል [አማራጮችን] የመረመረ ወይም የተመለከተ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አይደሉም" ሲሉ ተከላክለዋል።

ግዛቱን ለመግዛት ለዴንማርክ 100 ሚሊዮን ዶላር በወርቅ ለመክፈል በአውሮፓውያኑ 1946 ሃሳብ አቅርበው የነበሩትን ፕሬዝዳንት ሃሪ ትሩማንንም በአብነት አንስተዋል።

የግሪንላንድ ነዋሪዎችን ልብ የመግዛት ዘመቻ

የተሰበሰቡ የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት አብዛኛው የግሪንላንድ ሕዝብ ከዴንማርክ ነጻ መውጣት ይፈልጋል። ይህም ቢሆን ግን የአሜሪካ አካል መሆን እንደማይፈልጉ እነዚሁ የሕዝብ አስተያየቶች አሳይተዋል።

አሜሪካ የግሪንላንድን ነጻነት የሚደግፉ ሰዎችን በመለየት እንዲሁም የአጭር ጊዜ የፋይንስ ጥቅማ ጥቅም በመስጠት እንዲሁም ወደፊት የሚኖር ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን በማሳየት ልባቸውን ለመግዛት ልትሞክት ትችላለች።

አሁንም ቢሆን የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች የግሪንላንድ ነጻነት እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርጉትን የክትትል ሥራ ማሳደጋቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ይህ እርምጃ የትራምፕ አስተዳደርን ግብ የሚደግፉ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎችን ለመለየት ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።

የጂኦ-ስትራቴጂ ባለሙያ እና የመከላከያ ሚኒስቴር የቀድሞ አማካሪ የሆኑት ኢምራን ባዩኒ እንደሚናገሩት፤ "የተጽእኖ ዘመቻ" ማካሄድ ከወታደራዊ እርምጃ ከመውሰድ የተሻለ አማራጭ ነው። ይህ ዘመቻ ግሪንላንድ ነጻ እንድትወጣ ሊረዳ እንደሚችልም አክለዋል።

"ከዚያም ግሪንላንድ ነጻነቷን ካወጀች በኋላ የአሜሪካ መንግሥት አጋር እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። የወታደራዊ እርምጃ ወጪ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

እንዲህ ዓይነቱ አጋርነት አሜሪካ ከዚህ ቀደምም አድርጋው የምታውቀው ነው። ምሳሌ አሜሪካ የፓሲፊክ ውቅያኖስ አገራት ከሆኑት ፓላው፣ ማክሮኔዥያ እና ማርሻል አይላንድስ ጋር ተመሳሳይ ስምምነቶችን ፈጽማለች።

እነዚህ ሀገራት ለአሜሪካ መከላከያ መብት ሰጥተዋል። በምላሹም የእነዚህ ሦስት ሀገራት ዜጎች አሜሪካ ውስጥ የመኖር እና የመሥራት ዕድል ያገኛሉ።

ነገር ግን አሁንም ባሉ ስምምነቶች መሠረት ወደ ግሪንላንድ የፈለጉትን ያህል ወታደሮች የማስገባት ሥልጣን ያላቸው ትራምፕ፤ በዚህ ዓይነቱ አካሄድ ላይረኩ ይችላሉ።

ደግሞም እንዲህ ዓይነቱ አሠራር አሜሪካ በአርክቲክ በረዶ ስር በጥልቀት ተቀብረው በሚገኙት የግሪንላንድ ከፍተኛ የማዕድን ክምችቶች ላይ የባለቤትነት መብት አይሰጣትም።

የዴንማርኩ ተንታኝ ሀንሰን ከወታደራዊ እርምጃ ውጭ ግሪንላንድን "የመያዝ" ማንኛውንም ዘመቻ የግሪንላንድ ሕዝብ እስከተቃወመው ድረስ የመሳካት ዕድል የለውም።

በአሁኑ ወቅት ግሪንላንድ ውስጥ የአሜሪካ አካል ለመሆን ቅስቀሳ የሚያደርግ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲ የለም። "ግሪንላንድ በድጋሚ የአውሮፓ ኅብረት አባል የመሆን ዕድሏ ሰፊ ነው" ይላሉ ተንታኙ።

"በተጨማሪም የአሁኑ የአሜሪካ አስተዳደር የቀረው ሦስት ዓመት ብቻ ነው፤ የግሪንላንድ ሕዝብ ግን ምናልባትም 1,000 ዓመት የሚሻገር ፍላጎት አለው" ሲሉ ምልከታቸውን አጋርተዋል።