ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትራምፕ አስተዳደር ለሶማሊያዊያን ጊዜያዊ ሕጋዊ ጥበቃ እንደማይሰጥ አስታወቀ
የትራምፕ አስተዳደር ለሶማሊያዊያን ጊዜያዊ ሕጋዊ ጥበቃ እንደማይሰጥ አስታወቀ። ይህም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቀላሉ ከአሜሪካ ለማባረር ሁኔታዎችን ያመቻቻል ተብሏል።
"በሶማሊያ ያለው ሁኔታ ስለተሻሻለ ከዚህ በኋላ የሕጉን መስፈርቶች ስለማያሟላ ነው" ውሳኔው የተወሰነው ሲሉ የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትሯ ክሪስቲ ኖም ተናግረዋል።
በእንግሊዝኛው ቲፒኤስ እየተባለ የሚጠራው ማዕቀፍ አሜሪካዊያን ባለሥልጣናት ደኅንነታቸው የተጠበቁ አይደሉም ወደተባሉ ሀገራት ስደተኞችን እንዳይመልሱ ያግዳል።
ከሚመጣው መጋቢት ጀምሮ 2500 የሚሆኑ ሶማሊያዊያን የሥራ ፈቃዳቸውን እና ሕጋዊ እውቅናቸውን የሚያጡ ሲሆን ይህም ከሀገር እንዲባረሩ ሊያደርጋቸው ይችላል።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሶማሊያዊያን ስደተኞችን እንደማይፈልጉ በግልፅ ተናግረዋል። በሚኒያፖሊስ የሚገኙ ስደተኞች ተይዘው ከሀገር እንዲወጡም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
"ጊዜያዊ ማለት ጊዜያዊ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ በላኩት መግለጫ የተናጉሩት ክሪስቲ "ከዚህም ባለፈ ሶማሊያዊያን ዩናይትድ ስቴትስ እንዲቆዩ ማድረግ ከብሔራዊ ጥቅማችን ጋር የሚጋጭ ነው። አሁን ቅድሚያ የምንሰጠው ለአሜሪካዊያን ነው" ብለዋል።
የአሜሪካ ኮንግረስ ጊዜያዊ ሕጋዊ ጥበቃን ያስተዋወቀው በአውሮፓውያኑ 1990 ነበር። ሕጉ በጦርነት እና ተፈጥሯዊ ክስተት ከላሸቁ ሀገራት ለሚመጡ ስደተኞች ጥላ ይሰጣል። ቲፒኤስ ያላቸው ስደተኞች አሜሪካ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ መሥራትና መኖር ይችላሉ።
የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴር ለቢቢሲ እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት 2471 ሶማሊያዊያን ቲፒኤስ ሲኖራቸው 1383 ደግሞ አመልክተው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
ክሪስቲ ባለፈው ወር በርካታ ሶማሊያዊያን ዳያስፖራዎች በሚኖሩባት ሚኒሶት ግዛት ከሕፃናት ማቆያ ኢንዱስትሪ ጋር በተያያዘ የመንግሥት በጀት ተመዝብሯል ብለው ለዚህ ተጠያቂዎች ሶማሊያዊያን ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል።
ባለፈው ሳምንት ጆናታን ሮስ የተባለ የአይስ ፖሊስ አሜሪካዊቷ ሪኔ ጎልድን በሚኒያፖሊስ ከተማ ተኩሶ መግደሉ ቁጣ ቀስቅሷል። ይህን ተከትሎ በሚኒሶታ ግዛት በምትገኘው ሚኒያፖሊስ እና በሌሎች የአሜሪካ ከተሞች ተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል።
የትራምፕ አስተዳደር የስደተኞች ቁጥጥር መኮንኑ ራሱን ለመከላከል የወሰደው እርምጃ ነው ይላል። የአካባቢው ባለጅልጣናት ግን ግለሰቧ ምንም ዓይነት አደጋ አልደቀነችም በማለት ይከራከራሉ።
ትራምፕ በተለይ ባለፉት ወራት ሶማሊያዊያን ስደተኞች "ወደመጡበት ቦታ ይመለሱ" በማለት ከሀገራቸው እንዲወጡ ሲጠይቁ ቆይተዋል። አልፎም "ሀገራቸው መልካም ሁኔታ ላይ ያልሆነችው ለዚህ ነው" ብለዋል።
የአሜሪካ መንግሥት መግለጫውን ከማውጣቱ በፊት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው "ታላቁ የሚኒሶታ ሕዝብ ወይ ፍርሀት አይግባህ፤ ቀና የምትልበት ቅን ይመጣል" ሲሉ ፅፈዋል።
ቲፒኤስ ለሶማሊያዊያን የተፈቀደው በአውሮፓውያኑ 1991 በትልቁ ቡሽ ፕሬዝደንትነት ዘመን ነበር። ነገር ግን በሶማሊያ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በዲሞክራት እና ሪፐብሊካን ፕሬዝደንቶች እየታደሰ እስከዛሬ ቆይቷል።
ፕሬዝደንት ባይደን ለሶማሊያዊያን ለ18 ወራት የሚቆይ ቲፒኤስ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህ ቀነ-ገደብ በሚቀጥለው መጋቢት ያበቃል።
ትራምፕ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለቬንዙዌላ፣ ሄይቲ፣ አፍጋኒስታን እና ኔፓል ስደተኞች የሚሰጠውን ቲፒኤስ መሰረዙ ይታወሳል።