ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአልሸባብ ዛቻ ስጋት ውስጥ የጣለው ከአሜሪካ የተባረረው ሶማሊያዊ
ማሃድ ሞሐሙድ ባለፈው ወር ከአሜሪካዋ ሚኒያፖሊስ ከተማ ከተባረረ በኋላ የሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ውስጥ ካለው ሙቀት፣ ትርምስ እና ውጥረት ጋር ቀስ በቀስ እየተላመደ ነው።
ሶማሊያውያን የ36 ዓመቱን ማሃድ፣ 'ጋሪአን' ብለው ይጠሩታል። ትርጉሙ "ዳኛ" ማለት ነው።
ይህንን ስሙን የሚጠቀመው በቲክቶክ ላይ ነው።
አሜሪካ እያለ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮችን ማፍራት ችሏል። አድናቂዎች ማሃድን የጎሳውን ጥቅም በመከላከሉ አወድሰውታል።
ይህ በሶማሊያውያን የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ዘንድ የተለመደ የመወራረፍ ባህል አካል ነው።
ነገር ግን ከዋይት ሐውስ ጋር ግንኙነት ያለውን የ"ራፒድ ሪስፖንስ 47" ኤክስ አካውንት ለሚቆጣጠሩት፣ ማሃድ "ሕገ ወጥ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ" ነበር።
በጥቅምት ወር በወጣው ጽሑፍ ላይ በሶማሊያ ዋና ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሆቴል "የፈረንሳይ ባለስልጣናትን በማገት ተሳትፏል" ሲል ከሶታል።
ማሃድ በወቅቱ ሞቃዲሾ ውስጥ እንዳልነበረ በመግለጽ ክሱን ውድቅ አድርጓል።በዚህ ክስ የተነሳ ጥፋተኛ ተብሎ ስላልተፈረደበት ክሱ ተቋረጠ።
የአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ኤጀንሲ (አይስ) በቁጥጥር ስር ያዋለው ተቀናቃኙ የቲክቶከር አድራሻውን ካሾለከ በኋላ እንደሆነ ተናግሯል።
"አይስ ሁለት ክሶች እንዳሉብኝ ነገሩኝ። አንደኛው ሕገወጥ በሆነ መንገድ ወደ አገሪቱ መግባት እና የፈረንሳይ ባለሥልጣንን ማገት ነው።"
ማሃድ ከእገታ ጋር ተያይዞ የቀረበበት ክስ በኤፍቢአይ (FBI) እንደተያዘ እና ጥያቄዎች ከቀረቡለት በኋላም በነፃ እንደተሰናበተ ተናግሯል።
ያ ግን ከመባረር አላዳነውም።
ከሶማሊያ ወደ አሜሪካ ያደረገው ጉዞ ከአስር ዓመት በፊት የጀመረ ሲሆን መጀመሪያ ያመራው እአአ እስከ 2021 ድረስ ወደ ኖረባት ደቡብ አፍሪካ ነበር።
ነገር ግን እዚያ ሳለ መጤ ጠል በሆኑ እና በታጠቁ ቡድኖች ጥቃት እንደደረሰበት ይናገራል።
ከዚያም ወደ ብራዚል ሄዶ በመጨረሻም ያለምንም ሰነድ የሜክሲኮን ድንበር በማቋረጥ ወደ አሜሪካ ተሻገረ።
ማሃድ "የሜክሲኮን አጥር ስዘልል ተይዤ ለአንድ ወር ታስሬ ነበር" ይላል።
"በኋላ የጥገኝነት ጥያቄዬ እየታየ ስለነበር የስራ ፈቃድ አግኝቼ ተለቀቅኩ።"
ከዚያም ወደ ሚኒያፖሊስ አመራ።
"የኡበር ሹፌር ሆኜ እሠራ ነበር። በመጨረሻ የተስፋይቱ ምድርን በመርገጤ ደስተኛ ነበርኩ። እነሱ እንደሚቀበሉኝም ተስፋ አድርጌ ነበር።"
የቲክቶክ ስራው እንዲሁ መስመር እየያዘለት መጣ። ደጋፊዎቹ የቀጥታ ስርጭቱን ሲመለከቱ ስጦታዎችን ስለሚልኩለት ቋሚ ገቢ አስገኝቶለታል። ይህ ደግሞ መንግሥትን በመከላከሉ ምክንያት በሶማሊያ የሚገኘው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን፣ አልሻባብ ዕይታ ውስጥ እንዲገባ እና ዛቻ እንዲደርስበት አድርጓል።
በአሜሪካ ያቀረበው የጥገኝነት ጥያቄ በከፊል ከዚያ ስጋት ጋር የተያያዘ ነበር።
ማሃድ በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ማለዳ ላይ የኢሚግሬሽን ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ሲያውሉት የነበረውን በዝርዝር ያስታውሳል።
ቁርስ ከበላ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ የታክሲ ስራውን ለመጀመር በማሰብ ወደ መኪናው ሄደ።
"ወዲያውኑ ሊወስዱኝ መጡ" ይላል።
እንደ ማሃድ ገለጻ፣ ሚኒያፖሊስን እና መንትያ ከተማዋን ሴንት ፖልን ወደሚያገለግለው እና በመኪና ጉዞ የ30 ደቂቃ ርቀት ላይ ወደሚገኘው የአይስ (ICE) ዋና መሥሪያ ቤት ተወሰደ።
ከዚያም በዊልማር ወደሚገኘው የካንዲዮሂ ካውንቲ እስር ቤት ተዛውሮ ስድስት ወራት በእስር እንዳሳለፈ ተናግሯል።
ከእነዚያ ወራት ውስጥ ሦስቱን ያሳለፈው የጥገኝነት ጥያቄው ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ መሆኑን እና የቀሩት ሦስቱ ደግሞ ከአገር እስኪባረር በመጠበቅ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ባለሥልጣናቱ በሶማሊያ ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ያቀረበውን አቤቱታ ውድቅ ስላደረጉ የጥገኝነት ጥያቄውን ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ።
ማሃድ ከአገር የሚባረሩ ሰዎችን የሚያጓጉዝ አውሮፕላን ማረፊያ ወደሚገኝበት አሪዞና ለአጭር ጊዜ ተዛውሮ እንደነበረ ይናገራል።
ነገር ግን በተደጋጋሚ የሎጂስቲክስ ዝግጅቶች ባለመሟላታቸው የተነሳ ጉዞው ዘግይቷል።
ማሃድ ካሳለፈባቸው እስር ቤቶች አንዱ ከአገር ለመባረር የሚጠብቁ የኬንያ፣ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ዜጎችን ጨምሮ 39 ስደተኞች ይገኙ ነበር።
በመጨረሻም የእርሱ ከአገር የመባረሪያ ጊዜ ሲደርስ ማሃድ እጆቹ እንዳይንቀሳቀሱ በሚያደርግ ጥብቅ ጃኬት እንዲለብስ ተደርጎ፣ ከሌሎች ሰባት ስደተኞች እና ጠባቂዎች ጋር በትንሽ አውሮፕላን ጉዞ ጀመረ።
ጉዞው መጀመሪያ ወደ መካከለኛው አሜሪካ ኮስታሪካ፣ ከዚያም ወደ ምዕራብ አፍሪካ ሴኔጋል፣በኋላም ወደ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ተደረገ።
እዚያም ማሃድ እጆቹ እንዳይንቀሳቀሱ ያደረገው ጃኬትን አውልቆ፣ እጁ በካቴና ከታሰረ በኋላ በሌላ አውሮፕላን ወደ ሞቃዲሾ እንደተሳፈረ ተናግሯል።
ማሃድ ለመባረር ለሦስት ወራት ሲጠብቅ በመቆየቱ፣ እጣ ፈንታውን ቀድሞ ተቀብሏል፤ ወደ አገሩ ሲመለስም ብዙም ስሜታዊ አልነበረም።
ከአስር ዓመታት መለያየት በኋላ፣ በመጨረሻ ከሦስቱ ልጆቹ ጋር እንደገና ተገናኝቷል። "ይህንን ጊዜ በምንም ነገር አልለውጥም ነበር... ለ10 ዓመታት አላየኋቸውም" ይላል ማሃድ።
ነገር ግን ከአልሻባብ የግድያ ማስፈራሪያዎችን የያዙ የጽሑፍ መልዕክቶችን ከተቀበለ በኋላ ለሕይወቱ ስለሚፈራ አሁንም በአሜሪካ መሆንን ይመርጣል።
ከቤት ውጭ ሲሆን ተጨማሪ የደህንነት ጥንቃቄዎችን ይወስዳል፤ ነገር ግን ለደህንነት ሲባል ተጨማሪ ዝርዝሮችን ወይም ያሉበትን የስጋት ዓይነቶች ማጋራት አልፈለገም።
ማሃድ ወደ ሞቃዲሾ ሲመለስ በቲክቶክ ላይ ያገኘውን ዝና ተከትሎ የአካባቢው ፖለቲከኞችን ጨምሮ በርካታ የጎሳው አባላት በደስታ ተቀብለውታል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባለው ተሳትፎ ምክንያት ከአሜሪካ የሚባረሩ ወይንም ሊባረሩ የሚችሉ ሌሎች ሶማሊያውያን የማያገኟቸውን ዕድሎችን ሊያገኝ እንደሚችል ይገነዘባል።
ባለፈው ወር ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የትውልድ አገራቸው ደህንነቱ የተጠበቀ ባልሆነበት ጊዜ ሰዎች እንዳይባረሩ የሚያደርገውን ጊዜያዊ ከለላ እንደሚያቆሙ ተናግረዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ደግሞ የሶማሊያ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዲገቡ እንደማይፈልጉ በመግለጽ ለጋዜጠኞች "ወደመጡበት መመለስ አለባቸው" እና "አገራቸው ጥሩ ያልሆነችው በምክንያት ነው" በማለት ተናግረዋል።
ሶማሊያ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ እአአ በ1991 ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ መላውን አገሪቱ የሚቆጣጠር ማዕከላዊ መንግሥት አልነበራትም።
አሁን በሞቃዲሹ ማዕከላዊ መንግሥት ቢኖርም ሶማሊያውያን ሥርዓት አልበኝነትና የሽብር አደጋን ተቋቁመው እየኖሩ ነው።
እስላማዊ ታጣቂዎች አሁንም አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል የሚቆጣጠሩ ሲሆን አልፎ አልፎም በዋና ከተማዋ ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ።
የትራምፕ አስተያየት የተሰማው በሚኒሶታ ግዛት የማኅበራዊ ድጋፍ ፕሮግራም ውስጥ ስለተፈፀመ ከፍተኛ ማጭበርበር ከተጠየቁ በኋላ ነው።
በኮቪድ-19 ወቅት ለልጆች ምግብ ለማቅረብ በሚል የሜኔሶታን መንግሥት አጭበርብረዋል የተባሉ ሰዎችን የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ከስሷል።
የቀድሞው የሜኔሶታ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መርማሪ ኬሽ ሜጋን እንዳሉት፤ በዚህ የማጭበርበር ክስ ብዙ ሶማሊያዊ ስደተኞች ስማቸው ተነስቷል። ተፈጽሟል በተባለው ማጭበርበር የሜኔሶታ ግዛት በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ማጣቱም ተገልጿል።
በርካታ የሶማሊያ ስደተኞች በዚህ ክስ ውስጥ ስማቸው ተጠቅሷል።
ፕሬዝዳንቱ ስለ ሶማሌዎች አስተያየት ከሰጡ በኋላ፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የኢሚግሬሽን ሠራተኞች በሚኒያፖሊስ እና በሴንት ፖል የስደተኞችን በር ሲያንኳኩ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ተሰራጭተዋል።
80,000 የሚጠጉት የሶማሊያ ማኅበረሰብ ለሚኖሩባት ከተማ ይህ ልጥፍ የማንቂያ ደወል ነው።
ቢቢሲ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በትንሽ የጓደኛቸው ክፍል ውስጥ በስጋት ለማሳለፍ የተገደዱ አምስት ወጣት ሶማሊያውያንን አነጋግሯል።
ባለፈው ሳምንት በስማቸው የተከራዩትን ቤት በድንገት ለቅቀው ወደ ጓደኛቸው ቤት መምጣታቸውን ይናገራሉ።
ጊዜያዊ ጥበቃ የተደረገላቸው ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን፣ አይስ አድራሻቸውን በመከታተል ሊወስዳቸው የመምጣቱ ነገር የጊዜ ጉዳይ ብቻ እንደሆነ አምነዋል።
ቦታ መቀየር የተወሰነ ጥበቃ እንደሚያስገኝላቸው ተስፋ በማድረግ መያዝ የሚችሉትን ብቻ ይዘው በሌሊት ተደብቀው ወደጓደኛቸው ቤት ሄደዋል።
አሁን ሕይወታቸው ባለበት ረግቷል። ሥራ ፈትተዋል። ምግብ መብላት ትተዋል ወይንም የሚበሉበትን ሰዓት ቀይረዋል።
ከስደተኞቹ አንዱ ሁሉም ነገር በምን ያህል በፍጥነት እንደተለዋወጠ ሲገልጽ "የምግብ እጥረት አለብን። ባለፉት አምስት ቀናት አይስ እየጠበቀን ሊሆን ይችላል ብለን ስለምንፈራ ወደ ስራ አልገባንም። ምን እንደሚደርስብን አላውቅም" ብሏል።
ማሃድ በቅርብ ወራት ውስጥ ወደ ሶማሊያ የተባረረ ብቸኛው ሰው አይሆንም። እስካሁን ድረስ ይፋዊ ቁጥሮች ባይወጡም እንደሱ ያሉ የተወሰኑ ስደተኞች አይጠፉም።
ቢቢሲ ያነጋገረው እና ማንነቱ እንዳይገለጽ የጠየቀ ሶማሊያዊ ወጣት ሞቃዲሾ ውስጥ ሕይወቱን መልሶ ለመገንባት እየተፍጨረጨረ እንደሆነ ተናግሯል።
ከገጠሪቱ ሶማሊያ የወጣው ይህ ወጣት በአገሪቱ ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ድርቅ ከብት እና ሰብሉን ማውደሙን ተከትሎ ለመኖር በጣም ተቸግሮ ነበር።
ከዚያ በኋላ በብራዚል በማድረግ በሜክሲኮ ድንበር በኩል በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ተሻገረ፤ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በቁጥጥር ስር ውሏል። ወደ ሶማሊያ ከመመለሱ በፊት ለ18 ወራት በእስር ቤት ቆይቷል።
በስልክ ሲያወራ፣ ስለወደፊቱ እርግጠኛ አለመሆኑ ገልጿል።
"ከዜሮ እንድጀምር መልሰው ላኩኝ" ይላል። "የሠራሁበት ነገር ሁሉ ብን ብሎ ጠፋ።"
ወደ አሜሪካ ለመድረስ ወደ 20,000 ዶላር ከፍሏል፤ ይህም ከጓደኞቹና ከቤተሰቡ የተበደረውን ገንዘብ ያካትታል።
ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ምንም ገንዘብ አልነበረውም እና በሶማሊያ ምንም ዓይነት ዕድል እንደሌለ ይናገራል።
"እዚህ የወደፊት ተስፋ አይታየኝም" ይላል። "ምንም የሚካሄድ ነገር የለም… ሥራ የለም።"
አሁን እንደገና ወደ ሌላ ስፍራ ለመሰደድ እያሰበ ነው።
"ሕይወትን እንደገና መጀመር አልፈልግም። አሁን ወደ ማንኛውም አገር መሰደድ ብቻ ነው የምፈልገው።"