ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ሶማሊያውያን ስደተኞች አሜሪካ ውስጥ እንዲኖሩ እንደማይፈልጉ ተናገሩ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሶማሊያ ስደተኞች በአሜሪካ እንደማይፈልጉ በመግለጽ ለጋዜጠኞች "ወደመጡበት መመለስ አለባቸው" እና "አገራቸው ጥሩ ያልሆነችው በምክንያት ነው" አሉ።
ማክሰኞ ዕለት በካቢኔ ስብሰባ ላይ "እውነቱን ለመናገር በአገራችን እንዲኖሩ አልፈልግም" ብለዋል። ትራምፕ "ወደ አገራችን ቆሻሻ ማስገባት ብንቀጥል አሜሪካ በተሳሳተ መንገድ ትሄዳለች" ብለዋል።
የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት በሚኒሶታ ሰፊ የሶማሌ ማኅበረሰብ ውስጥ ዘመቻ እያቀዱ ስለመሆናቸው እየተነገረ ባለበት ጊዜ ነው ትራምፕ ይህን የሚያንኳስስ አስተያየት የሰጡት።
የሚኒሶታ ግዛት ባለሥልጣናት ዕቅዱ ከምሥራቅ አፍራዊቷ አገር የመጡ የሚመስሉ የአሜሪካ ዜጎችን ያለአግባብ ጠራርጎ ሊያስወጣ እንደሚችል በመግለጽ አውግዘዋል።
በጋራ 'ትዊን ሲቲስ' የሚባሉት ሚኒያፖሊስ እና ሴንት ፖል የተባሉት በዓለም ላይ ካሉት ትላልቅ የሶማሌ ማኅበረሰቦች መገኛ መካካል ናቸው። ከተሞቹ በአሜሪካ ውስጥ ትልልቆቹ የሶማሊ ማኅበረሰብ መገኛ ናቸው።
ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ለሰዓታት በቴሌቪዥን ከተላለፈ የካቢኔ ስብሰባ በኋላ በሰጡት አስተያየት "በአገራችን እንዲኖሩ አልፈልግም። እውነቱን እነግራችኋለሁ፣ እሺ። አንድ ሰው 'እንዴ! ይህ ትክክኛ አመለካከት አይደለም' ሊል ይችላል። ግድ የለኝም። በአገራችን እንዲኖሩ አልፈልግም" ብለዋል።
"አገር ለመባል በማትበቃው ሶማሊያ፤ ምንም የላቸውም፤ ምንም የላቸውም። እርስ በእርሳቸው እየተገዳደሉ ይኖራሉ። ምንም መዋቅር የለም" ብለዋል ትራምፕ።
ከዚያም ለኮንግረስ ለመመረጥ የመጀመሪያዋ ሶማሊ-አሜሪካዊት ተወካይ የሆኑትን ዴሞክራቷን ኢልሃን ኦማርን ወደመተቸት ዞረዋል።
"ሁልጊዜ እመለከታታለሁ" ያሉት ትራምፕ፤ ኢልሃን ኦማር "ሁሉንም ሰው ትጠላለች። እና ብቁ ያልሆነች ሰው እንደሆነች አስባለሁ" ብለዋል።
ኢልሃን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ "በእኔ ላይ ያለው አባዜ አስፈሪ ነው" ብለዋል። "በጣም የሚያስፈልገውን እርዳታ እንደሚያገኝ ተስፋ አደርጋለሁ።"
የአገሪቱ የስደተኞች እና የጉምሩክ ተቋም የሆነው ኢሚግሬሽን ኤንድ ከስተምስ ኢንፎርስምነት (አይስ) በትራምፕ አስተዳደር በመንትያ ከተሞች ውስጥ ሕጋዊ ያልሆኑ የሶማሊያ ስደተኞችን ዒላማ እንዲያደርግ መመሪያ ተሰጥቶታል ሲሉ እቅዱን የሚያውቁ ሰው ማክሰኞ ዕለት ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ እንዳሉት በዚህ ሳምንት ኦፕሬሽኑ ሲጀመር በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ዒላማ እንደሚደረጉ ይጠበቃል። ስለ ኦፕሬሽኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበው ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ነው።
ስለታቀዱት ስራዎች አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑት አይስን የሚቆጣጠረው የሀገር ውስጥ ደህንነት መምሪያ ቃል አቀባይ ማንኛውም ሰው በዘር ላይ ተመስርቶ ኢላማ ይደረጋል መባሉን ክደዋል።
"በየቀኑ አይስ በመላ አገሪቱ ያሉትን ሕጎች ያስፈጽማል" ብለዋል ረዳት ፀሐፊ ትሪሲያ ማክላውሊን።
"አንድን ሰው የአይስ ዒላማ የሚያደርገው ዘራቸው ወይም ጎሳቸው ሳይሆን በሕገወጥ መንገድ በአገሪቱ ውስጥ መሆናቸው ነው" ብለዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የሚኒያፖሊስ ከንቲባ ጃኮብ ፍሬይ በአይስ የሚፈጸም ኦፕሬሽን "የፍትህ ሂደት ይጣሳል" ብለዋል።
የአካባቢው መሪዎች እንደሚሉት፣ ከሶማሊያ የመጡ ወደ 80,000 የሚጠጉ ሰዎች እዚያ ይኖራሉ፣ እና አብዛኛዎቹ የአሜሪካ ዜጎች ናቸው።
የትራምፕ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ ሁለት የብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ ጥቃት ከተፈከፈተ በኋላ በስደተኞች ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ አጠናክሮታል። በአፍጋኒስታናዊ ጥቃት የተፈጸማባቸው የብሔራዊ ዘብ አባላት የ20 ዓመቷ ሳራ ቤክስትሮም እና የ24 ዓመቷን አንድሪው ዎልፍን ሲሆኑ ሳራ ህይወቷ ሲያልፍ አንድሪው ደግሞ ከባድ ጉዳትወ ደርሶበታል።
ባለፈው ሳምንት ትራምፕ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሚኒሶታ ለሚኖሩ የሶማሊያ ነዋሪዎች የሚደረገው ጊዜያዊ ጥበቃን ለማቆም ማቀዳቸውን ገልጸዋል። ይህ ጊዜያዊ ጥበቃ በችግር ውስጥ ካሉ አገሮች ለመጡ ስደተኞች የሚደረግ ነው።