ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ የሶማሊያ መንግሥት ከዩኤኢ ጋር የተፈጸሙ ስምምነቶችን የሰረዘበትን ውሳኔ ውድቅ አደረጉ
ራሷን ነጻ አገር አድርጋ የምትቆጥረው ሶማሊላንድ እና ከፊል ራስ ገዟ ጁባላንድ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የተፈጸሙ የወደብ ስምምነቶችን ለማቋረጥ ያስተላለፈውን ውሳኔ ውድቅ አደረጉ።
ሶማሊላንድ የፌደራል መንግሥቱ በግዛቷ ላይ "ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ ሥልጣን" እንደሌለው የገለጸች ሲሆን፣ ፑንትላንድ ደግሞ የሞቃዲሾ ውሳኔ "ተፈጻሚ የማይሆን እና የማይጸና" እንደሆነ አስታውቃለች።
የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ካቤኒ ሰኞ ሰኞ ጥር 4/2018 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የተደረጉ ሁሉም የሁለትዮሽ ስምምነቶች እንዲቋረጡ መወሰኑን አስታውቋል።
ይህ ውሳኔ ከባሕረ ሰላጤዋ አገር ጋር የተደረጉ "የወደብ ሥራዎችን፣ የመንግሥት ተቋማትን፣ እንዲሁም የፀጥታ እና የመከላከያ ትብብርን" እንደሚመለከት ተገልጿል።
በተለይም የወደብ ጉዳይ ላይ አጽንኦት የሰጠው የፌደራል መንግሥቱ መግለጫ፤ ውሳኔው በሶማሊላንድ በሚገኘው በርበራ ወደብ፣ በፑንትላንድ ቦሳሶ ወደብ እንዲሁም የጁባላንድ ኪስማዮ ወደብ ላይም ተፈጻሚ እንደሚሆን አስታውቋል።
"የፌዴራል ተቋማትን" እና የአገሪቱ ፌደራል ሥርዓት አባል ግዛቶችን እንደሚመለከትም አክሏል።
የፌደራል መንግሥቱ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው "የሶማሊያን ሉዐላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ብሔራዊ አንድነት ለመጠበቅ አስፈላጊ" በመሆኑ እንደሆነ አስረድቷል።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች "የሶማሊያን ነፃነት እና ፖለቲካዊ መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥሉ ጠብ አጫሪ እና ሰላምን የሚያናጉ ድርጊቶችን" ፈጽማለች ሲልም ከስሷል።
የአቡ ዳቢ እርምጃዎች በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተቀባይነት ያላቸውን "የሉዐላዊነት እና ጣልቃ ያለመግባት መርሆዎችን የጣሰ" እንደሆነም ገልጿል።
ይህንን የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ ተከትሎ መግለጫ ያወጡት ሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ የሞቃዲሾን ውሳኔ እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል።
የመጀመሪያውን የአገርነት ዕውቅና ከእስራኤል ያገኘችው ሶማሊላንድ፤ የፌደራል መንግሥቱ "ከበርበራ ወደብ ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ ስምምነቶች ላይ ላይ ሥልጣን እንዳለው በመጥቀስ" ያስተላለፈውን ውሳኔ "በፅኑ እንደምትቃውም" ገልጻለች።
ሶማሊላንድ ውስጥ የሚገኘው የበርበራ ወደብ እንዲሁም የበርበራ አየር ማረፊያ እና ነጻ የንግድ ቀጣና የሚተዳደሩት ባለቤትነቱ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥት በሆነው "ዲፒ ወርልድ" በተባለው የወደብ አስተዳደር ኩባንያ ነው።
ሐርጌሳ ባወጣችው መግለጫ "ሶማሊያ፤ የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ሉዓላዊ ግዛት የማትነጠል አካል በሆነችው በርበራ ላይ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ሥልጣን፣ አስተዳደራዊ ሥልጣን ወይም ውጤታማ የሆነ ቁጥጥር የላትም" ስትል የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ ውድቅ አድርጋለች።
የሶማሊያ መንግሥት የስምምነቶቹ "ተዋዋይ ወገን ወይም ዋስ" እንዳልሆነች የገለጸችው ሶማሊላንድ፤ ከዚህም የተነሳ ውሎቹን "ለማገድ፣ ለማሻሻል ወይም በሌላ መልኩ ተጽዕኖ ለማሳደር" የሚያስችል "ምንም ዓይነት ሕጋዊ መብት" እንደሌላት አስረድቷል።
"በሶማሊላንድ ሪፐብሊክ እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መካከል የተደረጉ ሁሉም ስምምነቶች ሕጋዊ፣ ጸንተው የሚኖሩ እና ሙሉ በሙሉ አስገዳጅ ናቸው" ስትልም አቋሟን ገልጻለች።
ራስ ገዝ መሆኗን ያወጀችው ፑንትላንድም ባወጣችው መግለጫ ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቃለች። ፑንትላንድ የሞቃዲሾን ውሳኔ የተቃወመችው የራሷን እና እና የሶማሊያን ፌደራል ሕገ መንግሥቶች በመጥቀስ ነው።
በሕገ መንግሥቶቹ መሠረት "ፑንትላንድ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች እና ወዳጅ አገራት ጋር የተደረጉ የልማት እና የደኅንነት ስምምነቶችን የመጠበቅ፣ የመሰረዝ እና የመለወጥ ሥልጣን" የግዛቲቱ መንግሥት እንደሆነ አስታውቃለች።
በዚህም ምክንያት የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት "የቦሳሶ ወደብ ልማት ፕሮጀክት እንዲሁም በፑንትላንድ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ተደረገው የደኅንነት ትብብር ስምምነት" ለመሰረዝ ያስተላለፈው ውሳኔ "ተፈጻሚ የማይሆን እና የማይጸና" እንደሆነ የፑንትላንድ መንግሥት ገልጿል።
የፑንትላንድ መንግሥት በዚህ መግለጫው የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ አስተዳደር "የሶማሊያ ሕዝብን ለመከፋፈል እና ግጭት ለመፍጠር እየሠራ" ነው በማለት ከስሷል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ "ሶማሊያውያን በአገሪቱ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ እንዳይመካከሩ" እያደረጉ እንደሆነ በማንሳትም ወቅሷል።
የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር "በሕገ ወጥ መንገድ ሕገ መንግሥቱን በብቸኝነት ካሻሻሉበት" ከአውሮፓውያኑ 2023 መጀመሪያ አንስቶ ፑንትላንድ ከፌደራል መንግሥት ጋር ያላትን ግንኙነት እንዳቋረጠች ገልጿል።
ሶማሊያ ውስጥ "ስምምነት ላይ የተመሠረተ፣ የተባበረ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና በፌዴራል ሥርዓት ላይ የተገነባ የመንግሥት መዋቅር እስኪመሠረት ድረስም" በዚህ ውሳኔው እንደሚጸና አስታውቋል።
የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ያስተላለፈው ውሳኔ በፑንትላንድ መንግሥት፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የቦሳሶ ወደብ ልማትን እያከናወነ ባለው ኩባንያ መካከል ያለውን ትብብር እንደማይጎዳው በመግለጫው አስፍሯል።