ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሁለት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አካባቢውን "ለቅቀው እንዲወጡ" አዘዘ
በአማራ ክልል ስር የተመሠረተው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስተዳደር፤ "የፕሪቶሪያ ስምምነትን በመጣስ ወገንተኛ የሆነ የፖለቲካ አቋም" ይዘዋል ያላቸው ሁለት ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች "ዞኑን ለቅቀው እንዲወጡ" አዘዘ።
ትዕዛዙ የተላለፈባቸው 'ኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል' (NRC) እና 'ኢንተርናሽናል ሜዲካል ኮር' የተሰኙት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ የአስተዳደሩን ውሳኔ ገና እየተመለከቱት እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የሁለት ዓመቱን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ስር መተዳደር የጀመሩትን አካባቢዎች እየመራ የሚገኘው፤ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ለሁለቱ ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ የሰጠው እሁድ ጥር 2/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው።
አስተዳደሩ ውሳኔ ካስተላለፈባቸው ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኖርዌዩ 'ኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል'፤ ተፈናቃዮችን በዘላዊነት ማቋቋም ላይ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው።
በግጭት፣ በተፈጥሮ አደጋ እና በበሽታ ለተጎዱ ሰዎች የአደጋ ጊዜ ምላሽ የሚያቀርበው 'ኢንተርናሽናል ሜዲካል ኮር' ደግሞ ዋና መሥሪያ ቤቱ አሜሪካ ውስጥ ነው። ድርጅቱ ሁመራ፣ ጸገዴ እና ወልቃይት ወረዳዎች ውስጥ ሴቶች እና ህጻናት ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ እገዛ እንደሚያደርግ የተቋሙ መረጃ ያመለክታል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ባወጣው መረጃ፤ እነዚህ ድርጅቶች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት "ለሰብአዊ ድጋፍ በሚል" ቢሆንም "ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ" ቆይተዋል ሲል ከስሷል።
ድርጅቶቹ በአካባቢው "ሥራ ከጀመሩበት [ጊዜ] ጀምሮ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ሥልጠናዎች እና ልዩ ልዩ ተግባራት የአገራችን ሕጎች እና መንግሥታችን የፈረመውን የፕሪቶሪያ ስምምነትን የሚቃረኑ" ተግባራት ፈጽመዋል ብሏል።
"በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅሬታን የሚፈጥሩ እና ማኅበረሰቡ ሌሎች ሕጋዊ ድርጅቶችን ጭምር በጥርጣሬ እንዲመለከታቸው የሚያደርጉ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች" የሚሉትም አስተዳደሩ ተፈጽመዋል ካላቸው ተግባራት መካከል ተጠቅሰዋል።
እንደ አስተዳደሩ ገለጻ ተቋማቱ "ከሕገ-ወጥ ተግባራቸው እንዲታቀቡ" እንዲሁም "የፕሪቶሪያ ስምምነትን እንዲያከብሩ በተደጋጋሚ ማሳሳቢያ" ተሰጥቷቸዋል።
ይሁን እንጂ ድርጅቶቹ "ሕገ ወጥ ተግባሮችን" መፈጸም ቀጥለዋል ሲል ከስሷል። "ከተቋቋሙለት የሰብአዊ ድጋፍ ዓላማ በተቃረነ አኳኋን የፕሪቶሪያን ስምምነት በመጣስ ወገንተኛ የሆነ የፖለቲካ አቋም" ይዘዋል ሲልም ወንጅሏል።
የአስተዳደሩ መግለጫ "ወገንተኛ የሆነ የፖለቲካ አቋም" ጋር በተያያዘ ከጠቀሳቸው ተግባራት ውስጥ፤ "በብዙ የሕይወት መስዋእትነት ነጻ የወጣውን ማኅበረሰብ እንደ አፈናቃይ" መጥራት የሚለው ይገኝበታል። "አካባቢውን የትግራይ ክልል አካል በማለት" ጠርተዋልም ብሏል።
"ለአብነትም ድርጅቶቹ ቅጥር ለመፈጸምም ሆነ ሌሎች ይፋዊ (ኦፊሳሊያዊ) ግንኙነቶችን በተመለከተ አካባቢውን ምዕራብ ትግራይ በሚል [ይጠራሉ]" ሲል በመግለጫው አስፍሯል።
አካባቢዎቹን "ምዕራብ ትግራይ" ብሎ መጥራት "እንደ ኢትዮጵያ ሕጎች ሁሉ የሀገሪቱ የሕግ አካል የሆነውን የፕሪቶሪያ ስምምነትን በጉልህ የሚጥስ ተግባር" ነው ብሏል። የፌደራል መንግሥት የፕሪቶሪያ ስምምነትን የፈረመው "ጦርነትን ለመቋጨት እና አካባቢውን ሰላማዊ በማድረግ ችግሮችን ለመፍታት" እንደሆነ ገልጿል።
ይህ ስምምነት "አካባቢውን አወዛጋቢ ቦታ" በሚል እንደሰየመውም በመግለጫው አክሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው መስከረም ላይ "የኢንተርናሽናል ሜዲካል ኮር" ተሽከርካሪ፤ "የጫነው አንድ ትልቅ ታንከር ውስጥ ሦስት ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ደብቆ እያዘዋዋረ" መገኘቱን አስተዳደሩ ገልጿል። "ይህም ተግባሩ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን የሚያሳፋፋ እና በወንጀል የሚያስጠይቅ" ነው ብሏል።
ሁለቱ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ እነዚህን "ሕገ ወጥ ተግባራት መፈጸማቸው በበቂ ሁናቴ" መረጋገጡን የገለጸው አስተዳደሩ፤ ከዚህ ቀደም የተሰጣቸውን "ምክረ ሀሳብ" አልተቀበሉም ሲልም ከስሷል።
"ሕገ ወጥ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያርሙ የተሰጣቸውን ምክረ ሀሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ዞኑን ለቅቀው እንዲወጡ በጥብቅ እናሳስባለን" ሲል የዞን አስተዳደሩ ውሳኔውን አስታውቋል።
አስተዳደሩ ያቀረባቸውን ውንጀላዎችን በተመለከተ ቢቢሲ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የሁለቱ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ኃላፊዎች በአሁኑ ሰዓት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንደማይሰጡ ገልጸዋል።
የኢንተርናሽናል ሜዲካል ኮር የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ሎውረንስ ሙታህሪያ "አዲስ አበባ እና መስክ ላይ ያሉ መረጃዎችን ማረጋገጥ፣ መግለጫውን ካወጡት አካላት ጋር ግንኙነት መፍጠር እና [በመግለጫው] የሰፈረውን [ክስ] እውነተኛነት ማረጋጥ" ስለሚያስፈልግ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ አስረድተዋል።
የዞን አስተዳደሩ መግለጫ ስለማውጣቱ እንደሚያውቁ የተናገሩት የኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል ካንትሪ ዳይሬክተር አይዛክ ኦዲያምቦ ኦኮም በተመሳሳይ፤ "ሕጉን ተከትለው [ጉዳዩ] በትክክል ምን እንደሆነ ለመረዳት" ሲሉ አስተያየት እንደማይሰጡ ተናግረዋል።
ኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያከናውናቸው ተግባራትን የሚያስተጓጉል ዕገዳ ሲያጋጥመው ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
የትግራይ ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ሐምሌ 2013 ዓ.ም. የሲቪል ማኅረበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን "ከተቋቋሙለት ዓላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ" ተገኝተዋል በሚል ዕገዳ ከጣለባቸው ሦስት ድርጅቶች አንዱ ነበር።
ሁለቱ ድርጅቶች የተላለፈው ውሳኔ ከተነሳ በኋላም ኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል በዕገዳው የቀጠለ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከአምስት ወራት በኋላ በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ወደ ሥራ እንዲመለስ ተደርጓል።
የፌደራል መንግሥት በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ ላይ የወሰደው ይህ እርምጃ በወቅቱ እንደ ሂውማን ራይትስ ዎች ካሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።
ቢቢሲ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ውሳኔ በፌደራል መንግሥት ደረጃ እውቅና ያለው ስለመሆኑ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።