ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኦሮሚያ ክልል በታጣቂዎች ታግተው የነበሩት ዐይነ ስውሩ ዐቃቤ ሕግ መለቀቃቸው ተገለጸ
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ በታጣቂዎች ታግተው የነበሩት ዐቃቤ ሕግ ሽብሩ ጉታ መለቀቃቸውን የምዕራብ ሸዋ ዞን ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
ጽሕፈት ቤቱ ዛሬ ታኅሣሥ 3/2018 ዓ.ም. በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ ሐሙስ ታኅሣሥ 2/2018 ዓ. ም. ታጋቹን "በግምት 8 ሰዓት አካባቢ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ወሊሶ ወረዳ፣ አዳሚ ጎቱ በምትባል ቀበሌ አስፋልት ዳር ትተውት ሄደዋል" ብሏል።
ታግተው የነበሩት ዐቃቤ ሕግ ከተገኙ በኋላ "በቅርብ በሚገኝ የጤና ጣቢያ ሕክምና እየተደረገላቸው" እንደሚገኝም ገልጿል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት "ድምጽ ስለሆናችሁን እናመሰግናለን" ሲልም አክሏል።
ሽብሩ ጉታ መገርሳ "በታጣቂዎች መታገታቸውን" የኦሮሚያ ዐቃቢያነ ሕግ ማኅበር ከቀናት በፊት ለቢቢሲ ገልጿል።
ሰኞ ኅዳር 29/ 2018 ዓ.ም. ዐይነ ስውር የሆኑት የኤጀርሳ ለፎ ወረዳ ዐቃቤ ሕግ "ታጥቆ ጫካ ውስጥ በሚንቀሳቀስ አካል ከሰዓት አካባቢ መታገታቸውን" አስታውቋል።
ዐቃቤ ሕግ ሽብሩ ስለመታገታቸው ማስረጃ እንዳገኘ እና ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝም ገልጾ ነበር።
የኦሮሚያ ዐቃቢያን ሕግ ማኅበር በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መረጃ መሠረት፤ ዐቃቤ ሕጉ የታገቱት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ በቾ ወረዳ፣ ቱሉ ቦሎ ከተማ እናታቸውን ከጠየቁ በኋላ፣ ለሥራ በምዕራብ ሸዋ ዞን ወደሚገኘው ዳንዲ ወረዳ፣ ጊንጪ ከተማ በመኪና ሲመለሱ ነው።
ከዕገታ የተለቀቁት ዐቃቤ ሕግ በምን ሁኔታ ላይ እንደነበሩ እና አሁን ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ የተገለጸ ነገር የለም።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ከማኅበሩ አመራሮች አንዱ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ዐቃቤ ሕግ ሽብሩ ሥራ የጀመሩት ከጥቅምት 2016 ዓ. ም. አንስቶ ነው።
"በቅንነት እና በሥነ ምግባር ፍትሕን ለማስፈን ለማኅበረሰቡ የሚሠራ ነበር። የዕለት ከዕለት ሥራውን ሕግን ተከትሎ ብቻ የሚያከናውን ነው" ሲሉም ገልጸዋቸዋል።
"ሕዝቡን በሙያዊ ሥነ ምግባር እና በገለልተኛነት ሲያገለግል የነበረ እና ዐይነ ስውር የሆነ ዐቃቤ ሕግ ድጋፍ ሊሰጠው ሲገባ፤ ታግቶ መወሰዱ ልዩ ትኩረት ሊቸረው ይገባል" በማለትም አክለዋል።
ከማኅበሩ አመራሮች አንዱ አካል ጉዳተኛው ዐቃቤ ሕግ መታገታቸው "በአገር ውስጥም በዓለም አቀፍ ሕግም ተቀባይነት የሌለው እና ከማኅበረሰቡ እሴት ጋር የሚጣረስ ነው" ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ዐቃቢያነ ሕግ ማኅበር እንዳለው፤ በተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች ስምምነት አንቀጽ 11 መሠረት፤ አደገኛ በሆኑ ወይም በታደራዊ ግጭት ባለባቸው ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን ለአካል ጉዳተኞች ከለላ መደረግ አለበት።
ዐቃቤ ሕጉ ከታገቱ በኋላ "የት እንዳሉ እና በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ" አለመታወቁን የገለጹት የማኅበሩ አመራር "ደኅንነቱ አስጊ ሁኔታ ውስጥ ነው" ብለው "ከእገታ እንዲለቀቅ" መጠየቃቸው ይታወሳል።
በኦሮሚያ ክልል ዐቃቢያነ ሕጎች እንዲሁም ነዋሪዎችም በታጣቂዎች መታገታቸው በተደጋጋሚ ተዘግቧል። ከእገታዎቹ ጋር በተያያዘ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተጠያቂ ቢደረግም በተደጋጋሚ ክሶቹን አስተባብሏል።
ከሳምንታት በፊት በምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ ጅማ አርጆ ወረዳ አራት ዐቃቤ ሕጎች በታጣቂዎች ታግተው አንደኛው ሲገደሉ፤ የተቀሩት ሦስቱ መለቀቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ከተለቀቁት ዐቃቤ ሕጎች አንደኛው ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ተገልጿል።
ታግተው ከተለቀቁት ዐቃቤ ሕጎች አንደኛው የሆኑት የሦስት ልጆች አባት ዓለማየሁ መሰለ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "የታገትነው በማይታወቁ ሰዎች ሳይሆን በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ነው" ብለዋል።
ዐቃቢያነ ሕጎቹ ላይ በታጣቂዎች ጥቃት የተፈጸመባቸው ለሥራ ወደ ጅማ ያቀኑ በነበረበት ወቅት ነው።
መንግሥት 'ሸኔ' የሚለው እና በሽብር ቡድንነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከእገታው ጋር በተያያዘ በቀረበበት ክስ ላይ ምላሽ አልሰጠም።