በቡርኪና ፋሶው መሪ ኢብራሂም ትራኦሬ ላይ ሊፈጸም የነበረ የግድያ ሴራ መክሸፉ ተሰማ

የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መሪ የሆኑትን ካፕቴይን ኢብራሂ ምትራኦሬን ለመግደል የተቀናበረ ሴራ መክሸፉን የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር መንግሥት አስታወቀ።

የአገሪቱ የደኅንነት ሚኒስቴር እንደገለጸው መሪውን ለመግደል የረቀቀ የተባለ ሴራ የተቀናበረው ከሦስት ዓመት በፊት በትራኦሬ ከመሪነት በተገለበጡት ወታደራዊው መኮንን በሌተናንት ኮሎኔል ፖል ሄንሪ ዳሚባ ነው።

"የደኅንነት መሥሪያ ቤታችን ይህንን ሴራ በመጨረሻው ሰዓት ላይ ደርሶበታል። ሴረኞቹ የአገሪቱን መሪ ለመግደል እና ሲቪል ባለሥልጣናትን ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ ተቋማትን ለመምታት ዕቅድ ነበራቸው" ሲሉ የደኅንነት ሚኒስትሩ ማሐማዱ ሳና ተናግረዋል።

አክለው ሴራው በጎረቤት አገር አይቮሪ ኮስት አማካኝነት ተደግፏል ሲሉ ከስሰዋል።

ይህንን ክስ በተመለከተ ከኮሎኔል ዳሚባም ሆነ ከአይቮሪ ኮስት አስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።

በርካቶች ከቶማስ ሳንካራ ጋር የሚያመሳስሏቸው የቡርኪና ፋሶው መሪ ካፕቴይን ትራኦሬ ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ሁለት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደርጎባቸዋል።

በተጨማሪም በአገሪቱ ውስጥ እየተጠናከሩ በመምጣት ሚሊዮኖችን ከቤታቸው ያፈናቀሉት እስላማዊ ታጣቂ ኃይሎች ከባድ ፈተና ሆነውባቸዋል።

የ37 ዓመቱ ጎልማሳ በእነዚህ ሁሉ ተደራራቢ ፈተናዎች ውስጥ ቢሆኑም በአገራቸው እና ከአገራቸው ውጪ ዝናን አትፈርዋል።

ምንም እኳን በአምባገነንነት ቢከሰሱም በአፍሪካ አንድነት ላይ ባላቸው አቋም እና በምዕራባውያን ላይ በሚያቀርቡት ትችት ተወዳጅ ናቸው።

የደኅንነት ሚኒስትሩ እንደሚሉት ባለሥልጣናት ሴራ ጠንሳሾቹ ዕቅዳቸውን ሲያወጡ የሚያሳይ ቪድዮ አግኝተዋል።

በቪድዮው ላይ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት 5 ሰዓት ገደማ ከቅርብ ርቀት አሊያም በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ፈንጂ በማጥመር ፕሬዝደንቱን ለመግደል ሐሳብ እንዳላቸው ሲወያዩ ነበር ይላሉ።

ቀጥሎ ደግሞ ሌሎች ወታደራዊ እና የሲቪል መሪዎችን ለመግደለም አሲረዋል ሲሉ ይወነጅላሉ።

ሳና እንደሚሉት ዳሚባ ወታደሮች እና ሲቪሎችን አጣምረው ከአይቮሪ ኮስት የመጣ 70 ሚሊዮን የቡርኪና ፋሶ ፍራንክ (125 ሺህ ዶላር) የውጭ ፈንድ ከማግኘታቸው በተጨማሪ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ከመግባታቸው በፊት የሀገሪቱን የድሮን መተኮሻ ጣቢያ ለመምታት ዕቅድ ነበራቸው።

"ምርመራችንን ቀጥለናል። በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር አውለናል። እኒህ ግለሰቦች ችሎት ፊት ይቀርባሉ" ሲሉ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

ሳና አሁን ሁኔታው ተረጋግቷል ብለው ዜጎች "በመታለል አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዳይገቡ" አሳስበዋል።

ምን ያክል ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የሚታወቅ ነገር የለም።

ሀገር ቤት እና ውጭ ያሉ ተቺዎች የትራኦሬ መንግሥት አምባገነናዊ፣ የተቃውሞ ድምፆችን የሚያፍን እንዲሁም ወታደራዊ መሪዎች በጅምላ የሚያስር እና ሚድያ ላይ ገደብ የጣለ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

የቡርኪና ፋሶ ጁንታ የውጭ ሀገር በአይቮሪ ኮስት በኩል እየመጣብኝ ነው ብሎ ክስ ሲያሰማ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የኃይል መጎሻሸም በቀጣናው ተጨማሪ ውጥረት ያመጣል የሚል ስጋት አለ።

ኮሎኔል ዳምቢያ በምርጫ የተመረጠ መንግሥት ፈንግለው በአውሮፓውያኑ 2022 ከጥር እስከ መስከረም ድረስ ቡርኪና ፋሶን መርተዋል።

ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ወደ ጎረቤት ሀገር ቶጎ ሸሽተው በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው ለተተኪው መንግሥት ስኬት እመኛለሁ ብለው መፃፋቸው ይታወሳል።