ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በስፋት የሚሠራጩት የቡርኪናፋሶውን መሪ የሚመለከቱ መረጃዎች ምንጫቸው ከየት ነው?
ቢዮንሴ ወታደራዊ ልብስ ለብሳ ብረት ለበስ መኪና ስታሽከረክር ከአንድ ሕንጻ ጭስ ሲወጣ ይታያል። በሙዚቃ ቪዲዮው ላይ የቡርኪናፋሶው ወታደራዊ መሪ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ ሽጉጥ ሲተኩሱ ይታያሉ። "የጭቆና ሰንሰለትን ለመሰበር ለሕዝቡ በሚያደረግው ትግል ፈጣሪ ኢብራሂም ትራኦሬን ጠብቅ" ይላል የዘፈኑ ግጥም።
ነገር ግን በቪዲዮው ላይ የሚታዩት ቢዮንሴ ወይም ኢብራሂም ትራኦሬ ራሳቸው አይደሉም። ቪዲዮው በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) አማካኝነት የእውነት እንዲመስል ተደርጎ በዲፕፌክ የተዘጋጀ ነው።
የቡርኪናፋሶውን መሪ የአፍሪካ አንድነት ጀግና አድርገው የሚያቀርቡ አብዛኞቹ ሐሰተኛ መረጃን የያዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተፈጠሩ ቪዲዮዎች ካለፈው ሚያዝያ ወዲህ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን አጥለቅልቀዋል።
ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ትራኦሬን ለአፍሪካ መሪዎች ምሳሌ አድርጎ በናይጄሪያ፣ በጋና፣ እና በኬንያ የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ማቅረብ በስፋት እየተከናወነ ያለ ልምድ ሆኗል።
አንዳንድ ራሳቸውን "የአፍሪካ አንድነት" አቀንቃኞች አድርገው የሚያቀርቡ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈታሪዎችም የራሳቸውን መንግሥታን ከትራኦሬ ጋር በማነጻጸር ያርባሉ።
የፈጠራ ወይስ እውነተኛ
ከሦስት ዓመት በፊት በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጡት የ37 ዓመቱ ወታደራዊ መሪ ኢብራሂም ትራኦሬ ራሳቸውን የፀረ ኢምፔሪያልዝም እንቅስቃሴ መሪ በማድረግ የምዕራባውያንን በተለይ ደግሞ የፈረንሳይን ጣልቃ ገብነት በመተቸት ከሩሲያ ጋር ወዳጅነትን ፈጥረዋል።
ትራኦሬ ሥልጣን ከያዙ በኋላ በአገሪቱ የዲሞክራሲ መብቶች አያያዝ ያሽቆለቆሉ ሲሆን፣ ጋዜጠኞች እና የመንግሥት ተቺዎች ታስረው የሠራዊቱ አባል እንዲሆኑ ይገደዳሉ። ሂዩማን ራይትስ ዋች በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት ደግሞ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የመንግሥት ኃይሎች ቢያንስ 100 ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን አመልክቷል።
ትራኦሬ ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ላይ በብዛት መታየታቸው እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ "ቀለል ያለ መሪ" ተደርገው የሚቀርቡበት መንገድ ጠንካራ አውንታዊ ገጽታን በዓለም ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ ጭምር በመፍጠር በርካታ ደጋፊዎችን በዋና ከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ለመሳብ ችሏል።
በዚህም የተነሳ አንዳንዶች በአውሮፓውያኑ 1987 የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ የተገደሉትን የቀድሞውን የአገሪቱ ወታደራዊ መሪ ቶማስ ሳንካራ በኢብራሂም ትራኦሬ በኩል "ድጋሚ የተወለዱ" አድርገው እስከ መመልከት ደርሰዋል።
ታዛቢዎች በርካታ አፍሪካውያን ወጣቶች በመንግሥታቶቻቸው ነባር የፖለቲካ አካሄድ በመሰላቸታቸው እና የአፍሪካ አገራት ከምዕባውያን ጋር ባላቸው ትስስር ላይ ጥያቄ ማንሳትን ጨምሮ የኢብራሂም ትራኦሬን አንዳንድ አቋሞችን ይደግፋሉ።
ትራኦሬ አንደበተ ርቱዕነታቸው እና መገናኛ ብዙኃንን በብልሃት መጠቀማቸው ሌሎች መሪዎችም እንደ እሳቸው እንዲሆኑ የመፈለግ ነገርን ፈጥሯል።
ትራኦሬ በአፍሪካ ውስጥ ጠንካራ ድጋፍ ያላቸው ቢሆንም "በሰው ሠራሽ አስተውሎት አማካኝነት የሚፈጠሩት ይዘቶች ግን ይህ ድጋፍ ተፈጥሯዊ አለመሆኑን ያመለክታል" የሚሉት በአህጉሪቱ ውስጥ የመረጃ መዛባትን የሚመረምረው ኮድ ፎር አፍሪካ የተባለው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት የምርመራ ተንታኝ የሆኑት ኢሉድ አክዌ ናቸው።
አንዳንዶቹ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ተተረኩ ቪዲዮዎችን ሙያዊ የዜና ዘገባ መስለው ለመቅረብ ይሞክራሉ፤ ነገር ግን ስለ ትራኦሬ እና ስለ መንግሥታቸው አሳሳች መረጃዎችን ይዘዋል።
የትራኦሬ ጠባቂ መሪውን "ለመግደል አምስት ሚሊዮን ዶላር" ተሰጥቶት እንደነበር የሚገልጽ አንድ ቪዲዮ 1 ሚሊዮን ተመልካችን አግኝቷል።
ኢብራሂም ትራኦሬ በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ተደጋጋሚ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እንደተደረገባቸው ቢዘገብም ይህንን የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ማስረጃ ግን አልተገኘም።
ትራኦሮ በአውሮፕላን ሲጓዙ መቀመጫቸውን ለሌላ ፈንሳያዊ ነጋዴ እንዲለቁ ስለመጠየቃቸው የሚተርክ አንድ ቪዲዮ 4.5 ሚሊዮን ዕይታን አግኝቷል። ቪዲዮው በግለጽ ታሪኩ ልቦለዳዊ መሆኑን ቢገልጽም ሌሎች የዩቲዩብ ቻናሎች ግን እውነተኛ ታሪክ አስመስለው እያሠራጩት ነው።
በአሜሪካ ኦሃዮ ዩኒቨርስቲ የኮሚዩኒኬሽን ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት የቡርኪናፋሶ ዜጋው ዶ/ር ላሳኔ ኡድራጎ "አንዳንዶቹ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ምኞት ብቻ ናቸው። አንዳንዶቹ እውነት ቢሆኑም በግነት የተሸፈኑ ናቸው" ይላሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሴሌና ጎሜዝን እና ሪሃናን የመሳሰሉ ታዋቂ ዘፋኞችን ከትራኦሬ ጋር በማቅረብ በዲፕፌክ የተዘጋጁ የሙዚቃ ቪዲዮዎችን መጠቀም አዲስ ዘዴ ሆኖ ብቅ ብሏል። በአንድ ሳምንት ውስጥም እንዲህ ዓይነት ከ40 የሚበልጡ ቪዲዮች በዩቲዩብ ላይ ተጭነዋል።
ቢቢሲ 1.8 ሚሊዮን ዕይታን ያገኘውን ትራኦሬን ከታዋቂው ዘፋኝ አር ኬሊ ጋር አድርጎ የሚያሳይ ቪዲዮን የሠራውን ናይጄሪያዊ የዲፕፌክ ቪዲዮ አዘጋጅን አነጋግሯል።
"ይህንን እንድሠራ ያደረገኝ ብቸኛው ምክንያት 'ኢብራሂም ትራኦሬ' ያላቸው ተፈላጊነት ነው" ሲል ራሱን የቡርኪናፋሶው መሪ አድናቂ የሚለው የ33 ዓመቱ ኦጉጂ ናምዲ ኬኔት ተናግሯል።
ጨምሮም ቪዲዮው ከዩቲዩብ ሁለት ሺህ ዶላር እንዳስገኘለት እና "ሙሉ ለሙሉ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተዘጋጀ ነው። ሰዎችም ይህንን ማወቅ አለባቸው፤ ማንንም ማታለል አልፈንግም" ብሏል።
ትራኦሬ፣ ሩሲያ እና ምዕራባውያን
የአፍሪካ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ስለትራኦሬ ታሪክ መናገር የጀመሩት ከሁለት ዓመት በፊት ለአፍሪካ ሩሲያ ስብሰባ ወደ ሩሲያዋ ሴንት ፒተርስበርግ በሄዱበት ጊዜ ነው።
በወቅቱ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር የተነሷቸው ፎቶዎች እንዲሁም ያደረጉት ንግግር የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ በበይነ መረብ ላይ በስፋት በመሠራጨታቸው የመሪው ዝና በአህጉሪቱ ውስጥ ናኘ።
ከዚያም በአሜሪካ ምክር ቤት ውስጥ ትራኦሬን የተመለከተ ክስ በቀረበበት ጊዜ ከፍተኛ ድጋፍ እና ፕሮፓጋንዳ በስፋት መሠራጨት ጀመረ።
የአሜሪካ የአፍሪካ ወታደራዊ ዕዝ አዛዥ ጄነራል ማይክል ላንግሌይ በአሜሪካ ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ በሰጡበት ጊዜ ትራኦሬ የአገሪቱን የወርቅ ክምችት አገዛዛቸውን ለመጠበቅ እየተጠቀሙበት ነው ብለው ከስሰው ነበር።
ይህም አሜሪካ የቡርኪናፋሶውን መሪ ለማስወገድ አቅዳለች የሚሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክቶች በአፍሪካ ውስጥ በስፋት መሠራጨት ጀመሩ። ነገር ግን በርካቶቹ መልዕክቶች ሐሰተኛ መረጃን ያያዙ ነበሩ።
አንድ ሚሊዮን ያህል ተከታይ ያለው የኤክስ ገጽ የአሜሪካው ጄነራል "የቡርኪናፋሶው ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ትራኦሬ፣ ለሕዝቡ ጠላት ነው" በማለት ለምከር ቤቱ ተናግረዋል ሲል ጽፎ ነበር።
ነገር ግን ቢቢሲ የተመለከተው የጄነራሉ ንግግር የጽሁፍ ቅጂ ከአገሪቱ ወርቅ የሚገኘውን ገንዘብ "ወታደራዊው ቡድን አገዛዙን ለመጠበቅ እያዋለ ነው" የሚል ነበር።
ከኮድ ፎር አፍሪካ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከጄነራል ላንግሌይ ንግግር በኋላ 165 የፌስቡክ አካውንቶች የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትራኦሬን ከአሜሪካ ጥቃት ለመጠበቅ ልዩ ኃይላቸውን መላካቸውን የመገልጽ ተመሳሳይ ሐሰተኛ መረጃን በማሠራጨት በ10 ቀናት ውስጥ ወደ 11 ሚሊዮን የሚጠጋ ዕይታን አግኝተዋል።
እውነታው ግን የሩሲያ ወታደሮች በአሜሪካው ጄነራል ከቀረበው ክስ ጋር በማይገናኝ ሁኔታ ቀድሞውንም ለፀረ ሽብር ዘመቻ ቡርኪናፋሶ ውስጥ ይገኙ ነበር።
በኤክስ ላይ ተሠራጨ ሌላ ቪዲዮ ደግሞ በርካታ ሕዝብ የተሰበሰበበት ምሥልን በማሳየት "ፈረንሳይ ውስጥ ኢብራሂም ትራኦሬን በመደገፍ እና ለቡርኪናፋሶ ሉዓላዊነት የተሰለፈውን ሕዝብ ተመልከቱ" የሚል ጽሁፍ ሰፍሮበታል።
ነገር ግን በቪዲዮው ላይ በተደረገው ማጣራት ሰዎቹ የተሰበሰቡት ፈረንሳይ ውስጥ ሳይሆን በሰርቢያ ዋና ከተማ ቤልግሬድ ሲሆን ዓላማውም ከቡርኪናፋሶ ጋር የሚያያዝ አልነበረም።
የተጋራው ቪዲዮ 3,000 ላይኮችን ያገኘ ሲሆን፣ በማኅበራዊ መድረኩም ላይ ሐሰተኛ መሆኑ አልታወቀም።
ይህንኑ ቪዲዮ በደቡብ አፍሪካ ያሉ የትራኦሬ ደጋፊዎች ያደረጉት ሰልፍ ነው በማለት ጋናዊው ጦማሪ ሱሌይማን ሞሐመድ በፌስቡክ ገጹ ላይ አጋርቶታል። ቢቢሲ ለጦማሪው ትክክል እንዳልሆነ ቢነግረውም እውነታውን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም።
"እኛ ስለመሪዎቻችን የምንናገረውን ሰዎች ውሸት ለማስመሰል ሲሞክሩ በጣም ነው የሚያስቀው" በማለት ቪዲዮው ትክክለኛ ነው ሲል ተከራክሯል።
እራሱን የአፍሪካ አንድነት አቀንቃኝ የሆነው ሞሐመድ "አፍሪካውያን ለዘመናት ሲፈልጉት የነበረ ዓይነት መሪ በመሆኑ" ትራኦሬን እንደሚያደንቃቸው ተናግሯል።