ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዓለም ላይ በርካታ ሰዎች በሽብር ጥቃት የሚገደሉበት የአፍሪካ የሳህል አካባቢ
"የዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት ማዕከል" በመባል በሚታወቀው የአፍሪካ ሳህል ቀጣና፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ላይ "ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ከሚደርሱ ሞቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት" በዚህ በሳህል አካባቢ መመዝገባቸውን ግሎባል ቴረሪዝም ኢንዴክስ (ጂቲአይ) አመልክቷል።
በዚህ አዲስ ዘገባ ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት 2024 "ከሽብርተኝነት ጋር የተዛመዱ 51 በመቶ ሞቶች" በሳህል ቀጣና የተከሰቱ መሆናቸውን ገልጿል።
ይህም ማለት በዓለም ላይ ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ከደረሱት 7,555 ሞቶች ውስጥ 3,885 የተመዘገቡት በዚሁ የአፍሪካ ቀጣና ነው።
እንደ ጂቲአይ ዘገባ ከሆነ በአውሮፓውያኑ 2015 የዓለም አሃዝ ከፍተኛ ደረጃ ደረሶ ከነበረበት 11,000 ቢቀንስም፣ የሳህል አሃዝ ግን ከ2019 ጀምሮ በአስር እጥፍ ገደማ ጨምሯል።
በቀጣናው የሚንቀሳቀሱ አክራሪ እና አማፂ ቡድኖችም "ትኩረታቸውን መቀየራቸውን ቀጥለዋል።"
መረጃው ታትሞ የወጣው የዓለም አቀፍ ሰላም እና ግጭቶችን በሚያጠናው 'ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ ኢንስቲትዩት' ነው።
ተቋሙ ሽብርተኝነትን "መንግሥታዊ ባልሆነ አካል በማስፈራራት ወይንም በማስገደድ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም ማኅበራዊ ዓላማን ለማሳካት የሚፈፀም ድርጊት" ሲል ይበይነዋል።
ጂቲአይ ቡርኪናፋሶ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ካሜሩን፣ ጊኒ፣ ጋምቢያ፣ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ቻድ እና ሞሪታኒያ በሳህል ቀጣና ውስጥ ያሉ አገራት መሆናቸውን በሪፖርቱ ላይ አስቀምጧል።
ሳህል በዓለም ላይ ከፍተኛ የወሊድ መጠን የሚመዘገብበት አካባቢ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ሁለት ሦስተኛ የሚጠጋው የቀጣናው ሕዝቡ ከ25 ዓመት በታች ነው።
ከምዕራቡ ዓለም በተለየ በቀጣናው "ሽብርተኝነትን በተናጠል የሚያከናውኑ አካላት እየጨመሩ" ሲሆን፣ ታጣቂ ጂሃዲስት ቡድኖች በፍጥነት እየተስፋፉ ነው ይላል ዘገባው።
አብዛኞቹ ጥቃቶች የሚፈጸሙት በሁለት ድርጅቶች ነው።
የሳህል እስላማዊ መንግሥት ቡድን ተባባሪ እና የአልቃይዳ ክንፍ በሆነው ጃማአት ኑስራት አል-ኢስላም ዋል ሙስሊም (JNIM) ነው።
የአፍሪካ የፀጥታ ዘርፍ ኔትወርክ ሊቀመንበር ኒያጋሌ ባጋዮኮ "አዲስ የሕግ ትዕዛዞችን ለማስተዋወቅ እየሞከሩ ነው" ይላሉ። "በተለይ የሸሪዓ ሕግን መሠረት በማድረግ ፍትህን ለማስፈን እየሞከሩ ነው።"
እንዲሁም "እርስ በርስ እየተፎካከሩ" መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በ2020 እና በ2021 በማሊ ከተፈፀመው መፈንቅለ መንግሥታት ወዲህ አይኤስ-ሳህል በአገሪቱ የሚቆጣጠረው ግዛት መጠን፣ በተለይም በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ከቡርኪናፋሶ እና ኒጀር ጋር በሚዋሰኑ የድንበሮች አካባቢዎች አቅራቢያ በእጥፍ ጨምሯል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን መሠረት ጄኤንአይኤም (JNIM) እንዲሁ ተደራሽነቱን ማስፋፋቱን ቀጥሏል።
የጂቲአይ ዘገባ እንደሚያመለክተው ሁለቱም ቡድኖች ሕፃናት ወታደሮችን ጨምሮ ተጨማሪ ተዋጊዎችን መልምለዋል።
በፈረንሳይኛ ተናጋሪ የአፍሪካ አገራት የቀጠናው ፖለቲካ ተንታኝ እና አማካሪ የሆነችው ቤቨርሊ ኦቼንግ "በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሰዎች ወደ ታጣቂ ቡድን ለመቀላቀል በሚወስኑበት ጊዜ ምርጫ አልባ ይሆናሉ" ብላለች።
"እነዚህ በጣም ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦች ናቸው።"
የጂቲአይ ዘገባ እንዴት የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ደካማ አስተዳደር "የሽብርተኝነት ዋና አንቀሳቃሽ" በመሆን ለአማፂ ቡድኖች ዕድገት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ እንደሆነ ያብራራል።
የሳህል ቀጣና አንዳንድ ጊዜ የአፍሪካ "መፈንቅለ መንግሥት ማዕከል" እየተባለ ይጠራል።
ከ2020 ጀምሮ በክልሉ ስድስት የተሳኩ መፈንቅለ መንግሥታት ተካሂደዋል።
እነሱም ሁለቱ በማሊ፣ ሁለት በቡርኪናፋሶ፣ አንድ በጊኒ እና አንድ በኒጀር ናቸው። እነዚህ አገራት አሁን የሚተዳደሩት በወታደራዊ መንግሥታት ነው።
በለንደን የኤስኦኤስ ዩኒቨርሲቲ የቀጠናው ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ፎላሃንሚ አይና "የሳህል አካባቢ አገረ መንግሥታት ብልሽት አጋጥሟአዋል" ይላሉ።
"የፖለቲካ መሪዎች ሕዝቡን ማዕከል ላደረገ አስተዳደር ቅድሚያ ባለመሰጠታቸው፣ ለዓመታት በዘለቀው ቸልተኝነት እና በአካባቢው ያሉ ቅሬታዎች እየተባባሱ በመምጣታቸው ሽብር ቡድኖች እነዚህን እንዲጠቀሙ በር ከፍቷል።"
ከዚህ ቀደም የሲቪል መንግሥታት ከአማፂ ቡድኖች የሚመጡትን የፀጥታ ስጋቶች መዋጋት አልቻሉም የሚል አመለካከት ነበር።
"ነገር ግን እነዚህ ወታደራዊ መንግሥታት ሥልጣን ቢይዙም መሬት ላይ ያለውን እውነታ አልቀየሩትም። እንዲያውም የፀጥታ ችግሩ ተባብሷል" ይላሉ ዶክተር አይና።
"ወታደራዊ መንግሥታቱ ፈታኝ ለሆነው የሕዝብ አስተዳደር ዝግጁ አይደሉም።"
እንደ ጂቲአይ ሪፖርት በ2024 ቡርኪናፋሶ "በተከታታይ ለሁለት ዓመት በሽብር በጣም የተጠቃች አገር ሆና ቆይታለች።"
ሪፖርቱ መውጣት ከጀመረ አንስቶ ካሉት 14 ዓመታት በተለየ በሽብር ጥቃት ተጠቂ በመሆን ቀዳሚ የሆኑት ኢራቅ ወይም አፍጋኒስታን ሳይሆኑ ቡርኪናፋሶ ሆናለች።
ጂሃዲስት ቡድኖች በሳህል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተለያዩ ሕገወጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የተደገፈ ነው።
ሰዎችን በማገት ገንዘብ በመቀበል፣ የከብት ዝርፊያ፣ የማዕድን ሽያጭ እና በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ላይ መሰማራታቸውን የጂቲአይ ዘገባ ያመለክታል።
ሳህል ከደቡብ አሜሪካ ወደ አውሮፓ ኮኬይን የሚያመላልሱ የዕፅ አዘዋዋሪዎች ቁልፍ መንገድ ሆኗል ሲል ሪፖርቱ ጠቅሶ "በሳህል የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ከሽብርተኝነት ጋር ተያይዞ ከሚገኝ እጅግ በጣም ብዙ ገንዘብን ይወክላል" ብሏል።
አንዳንድ ቡድኖች በቀጥታ የተደራጁ ወንጀሎችን ከመፈጸም ይርቃሉ። ነገር ግን "ግብር በመጣል ገንዘብ ለማግኘት ወይም በክፍያ የደኅንነት እና የጥበቃ አገልግሎት መስጠትን" እንደሚመርጡ ይጠቁማል።
"ይህ ስልት ገቢን ከማስገኘት ባለፈ እነዚህ ቡድኖች ከአካባቢው ማኅበረሰቦች ጋር እንዲዋሃዱ እና ተጽኖአቸውን እንዲያጠናክሩ ይረዳል።"
አማፂ ቡድኖች የሳህልን የበለፀገ የተፈጥሮ ሀብት ለመቆጣጠር እየተሽቀዳደሙ ነው።
ኒጀር በዓለም ሰባተኛዋ የዩራኒየም አምራች ነች፤ እንዲሁም ቁጥጥር የማይደረግበት በባህላዊ መንገድ የሚወጣ ወርቅ ማምረቻ በየአካባቢው ስለሚገኝ እንደ አይኤስ-ሳህል እና ጄኤንአይኤም ያሉ ቡድኖች ለገንዘብ ማግኛ ይጠቀሙባቸዋል።
በቅርቡ የተካሄዱትን የመፈንቅለ መንግሥታት ማዕበልን ተከትሎ የሳህል መንግሥታት ታጣቂዎችን ለመመከት ከፈረንሳይ እና ከአሜሪካ ይልቅ ወደ ቻይና እና ሩሲያ ፊታቸውን አዙረዋል።
"በአሁኑ ወቅት ሩሲያ አፍሪካ ኮርፕስ [የቀድሞው ዋግነር] ተብሎ በሚጠራው ወታደራዊ ቡድን የበለጠ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገች መሆኑን እያየን ነው" ትለለች ቤቨርሊ ኦቼንግ።
"የእነሱ ሥራ በክልሉ የሚስተዋለውን ሽምቅ ውጊያ ለመቋቋም እንዲችሉ የአካባቢውን አገራት ጦር ማሠልጠን እና መደገፍ ቢሆንም እስካሁን ውጤታማ አልሆነም።"
በዚህም ምክንያት የጂቲአይ ዘገባ በአሁኑ ጊዜ "የሽብር ማዕከል" እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ወደ ጎረቤት አገራት በከፍተኛ ቁጥር የመዛመት አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ለዚህም ማሳያው ቶጎ በ2024 አስር የሽብር ጥቃቶችን እና 52 ሞቶችን መዝግባለች።
እነዚህ ጥቃቶች በአብዛኛው አገሪቱ ከቡርኪናፋሶ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ የተከሰቱ ነበሩ።
ኦቼንግ "በአካባቢው ያሉ ታጣቂ ቡድኖች እንደ ቤኒን ወይም ቶጎ ወይም ወደ ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ የባሕር ዳርቻ ግዛቶች መስፋፋታቸው እርግጥ ይመስላል" ትላለች።