ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሱዳን ጦርነት ከተደፈሩት መካከል የአንድ ዓመት ሕፃናት እንደሚገኙበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ
ማስጠንቀቂያ፡- ይህ ጽሑፍ አንዳንድ ሰዎችን ሊረብሹ የሚችሉ የጾታ ጥቃት ዝርዝሮችን ይዟል።
በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የታጠቁ ሰዎች ሕጻናትን እየደፈሩ እና ጾታዊ ጥቃት እያደረሱ ነው ሲል የመንግሥታቱ ድርጅት የሕፃናት ኤጀንሲ (ዩኒሴፍ) ገለጸ።
በጅምላ የተፈጸመ ጾታዊ ጥቃት በአገሪቱ ወደ ሁለት ዓመት በሚጠጋው ግጭት ወቅት እንደ የጦር መሳሪያነት እያገለገለ እንደሆነ በሰፊው ተመዝግቧል።
የዩኒሴፍ በሱዳን በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት ሲያወጣ ግን ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ሪፖርቱ ከጥቃት ሰለባዎቹ ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ወንድ ልጆች መሆናቸውን ጠቅሶ፣ በተለምዶ እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎችን ማሳወቅ እና የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ በመጠየቅ ረገድ ክፍተት በመኖሩ ታዳጊዎቹ "ልዩ ፈተናዎች" እንዳጋጠማቸው ገልጿል።
ዩኒሴፍ እንዳለው ምንም እንኳን እ.ኤ.አ. ከ2024 መጀመሪያ ጀምሮ በሕፃናቱ ላይ 221 የአስገድዶ መድፈር ክሶች ሪፖርት ቢደረጉም ትክክለኛው ቁጥሩ ግን ከዚህ የበለጠ ሊሆን ይችላል።
ሱዳን ወግ አጥባቂ አገር በመሆኗ ከጥቃት የተረፉት በእነሱ እና በቤተሰቦቻቸው ላይ የደረሰውን አስገድዶ መድፈር ለመናገር በታጣቂ ቡድኖች ሊደርስባቸው የሚችለውን ቅጣት በመፍራት ዝም ማለት ይመርጣሉ።
የዩኒሴፍ ዘገባ በአገሪቱ እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት በልጆች ላይ የሚደርሰውን እንግልት የሚያሳይ መረጃ ያቀርባል።
በሪፖርቱ ላይ ከተጎጂዎቹ መካከል16ቱ ከአምስት ዓመት በታች መሆናቸውን እና አራት ጨቅላዎች እንደሚገኙበት ይፋ ሆኗል።።
ዩኒሴፍ በሕፃናቱ ላይ ለደረሰው ወንጀል ተጠያቂው ማን እንደሆነ ባይገልጽም፣ ሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምርመራዎች ግን አብዛኞቹ የአስገድዶ መድፈሮች የተፈጸሙት በአማፂ ኃይሉ ተዋጊዎች መሆኑን ጠቅሰው፣ ሰላማዊ ሰዎችን ለማሸበር እና እንቅስቃሴያቸውን የሚቃወሙትን ዝም ለማሰኘት የጾታ ጥቃትን እንደ ስልት መጠቀማቸውን ይፋ አድርገው ነበር።
ከሱዳን ጦር ኃይሎች ጋር እየተዋጋ ያለው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) ግን ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳልፈፀመ በመግለጽ አስተባብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምርመራ ሰብሳቢ መሐመድ ቻንዴ ኦትማን በጥቅምት ወር የቀድሞ ዘገባ ይፋ በሆነበት ወቅት "በሱዳን የመዘገብነውን ከፍተኛ የፆታዊ ጥቃት መጠን በጣም አስደንጋጭ ነው" ብለው ነበር።
በዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የቀረበው መረጃ እንደሚያሳየው፣የአርኤስኤፍ ጠንካራ ይዞታ በሆነው ዳርፉር ተጎጂዎች ብዙ ጊዜ ዒላማ ይደረጉ የነበረው፣ የአረብ ዝርያ ስለሌላቸው እና ጥቁር በመሆናቸው ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሱዳን የሚሰጠው ሰብዓዊ ምላሽ ቀድሞውንም የገንዘብ እጥረት አለበት። በቅርቡ የአሜሪካ ዕርዳታ መቀነስ ተጎጂዎችን ለመርዳት የሚደረገውን ጥረት አጣብቂኝ ውስጥ ጥሎታል።
በዩኒሴፍ ዘገባ ላይ የሰፈሩት ዝርዝሮች በሱዳን ያለውን አስከፊው ሁኔታ አጉልተው ያሳያሉ።
ከሌሎች ሴቶች ጋር በታጠቁ ኃይሎች ተይዛ ለቀናት ያሳለፈችው ኦምኒያ (ስሟ ተቀይሯል) "ሌሊት ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ አንድ ሰው በሩን ሲከፍት፣ ጅራፍ ይዞ ነበር። ከሴቶች አንዷን መርጦ ወደ ሌላ ክፍል ወሰዳት።ትንሿ ልጅ ስታለቅስ እና ስትጮህ ይሰማኛል። እየደፈሯት ነበር" ስትል ሁኔታውን ታስታውሳለች።
" በደፈሯት ቁጥር ይቺ ልጅ በደም ተሸፍና ትመለሳለች።ገና ትንሽ ልጅ ነች። እነዚህን ሴት ልጆች ጎህ ሲቀድ ብቻ ነው የሚለቅቋቸው።ብዙዎቹ ራሳቸውን ስተው ይመለሳሉ። እያንዳንዳቸው እያለቀሱ ውል የጠፋው ነገር ያወራሉ።እዚያ ባሳለፍኩባቸው 19 ቀናት ውስጥ ሕይወቴን ለማጥፋት ወደምፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ።" ትላለች።
በጦርነት የደቀቀችው ሱዳን የጤና አገልግሎቶችንም ሆነ ሠራተኞችን ለማግኘት ፈታኝ ከሆኑ ቦታዎች መካከል አንዷ ነች።
በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ሴቶች እና ሕፃናት የበለጠ ለጥቃት እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ ለትምህርት ከደረሱ አራቱ ልጃገረዶች መካከል ሦስቱ ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው።
የትራምፕ አስተዳደር ለሱዳን ወሳኝ የሆነውን እርዳታን አቋርጧል
የእነዚህ ወንጀሎች አስከፊ ውጤት ተጎጂዎች የሕክምና ዕርዳታ ለማግኘት የሚጠጉባቸው ቦታዎች ጥቂት መሆናቸው ነው።
ብዙ የሕክምና ተቋማት በጦርነቱ ወድመዋል፣ተዘርፈዋል ወይም በተፋላሚ ወገኖች ተይዘዋል።
በቅርቡ አሜሪካ ያደረገችው የእርዳታ ቅነሳም ልጆችን ለመከላከል ያሉትን ውስን አገልግሎቶች አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።
ዩኒሴፍ በአካባቢያቸው ያሉ ቀውሶችን ለመቋቋም የአደጋ ጊዜ ምላሽ በመስጠት የሚታወቁትን የመብት ተሟጋቾች አደረጃጀት በመጠቀም ለሕፃናት ደኅንነታቸው የተጠበቁ አገልግሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል።
እነዚህ የመብት ተሟጋቾች በአሜሪካ እርዳታ ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ የነበሩ ሲሆን አብዛኞቹ ለመዝጋት መገደዳቸውን አስተባባሪ ኮሚቴው ገልጿል።
የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በሴቶች የሚመሩ የአገር ውስጥ ድርጅቶች ከፆታዊ ጥቃት የተረፉ ሰዎችን ለመርዳት ወሳኝ ናቸው ብሏል።
ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው " ሺ ሊድስ" በመባል የሚታወቀው ቡድን ከአሜሪካ የሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ሲቆም ለመዘጋት መገደዱን ቢቢሲ ተረድቷል።
ለእነዚህ ድርጅቶች የሚመደበው በአስር ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ትልቅ ወጪ አለመሆኑን የሚገልጹት ሱዳናዊቷ የመብት ተሟጋች ሱለይማ ኤልካሊፍ፣ የሚሰጣቸው አነስተኛ ገንዘብ የማኅበራዊ ሰራተኞች በወር ወደ 35 የሚጠጉ ተረጂዎችን እንዲያገኙ አስችሏል ይላሉ።
በታጣቂዎች የተደፈሩት "በደረሰባቸው ጥንቃት እንኳን ለማዘን ዕድል የላቸውም " ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጦርነት- ምግብ ለማግኘት፣ ለመሸሽ፣ ጉዳትን ለመቋቋም ምንም ቦታ አይተዉም ሲሉም ያክላሉ።