ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መሪ ኢብራሂም ትራኦሬ ለምን በዓለም ዙሪያ የብዙዎቹን ቀልብ መግዛት ቻለ?
የ37 ዓመቱ ባለግርማ ሞገስ የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መሪ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ አገሩን ከምዕራባውያን ኢምፔሪያሊዝም እና የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መዳፍ ውስጥ ለማላቀቅ የቆረጠ የፓን አፍሪካኒስት መሪን ሰብዕና በጥበብ ገንብቷል።
መልዕክቱ በመላው አፍሪካና ከዚያም አልፎ ሲያስተጋባ፤ አድናቂዎቹ እንደ አንዳንድ ጊዜ "የአፍሪካ ቼ ጉቬራ" እየተባለ የሚጠራው ቡርኪናፋሶው የማርክሲስት አብዮተኛ ቶማስ ሳንካራ - እና ሌሎች የአፍሪካ ጀግኖች ፈለግ ሲከተል እያዩት ነው።
"የትራኦሬ ተጽዕኖ በጣም ትልቅ ነው፤ እንደ ኬንያ (በምስራቅ አፍሪካ) ባሉ አገራት ፖለቲከኞች እና ደራሲያን እንኳን ሳይቀር 'ሰውየው እሱ ነው' ሲሉ ሰምቻለሁ" ሲሉ የኮንትሮል ሪስክስ አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ ቤቨርሊ ኦቺንግ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተመራማሪዋ አክለውም "የትራኦሬ መልዕክቶች አሁን የምንኖርበትን ዘመን ያንጸባርቃሉ። ብዙ አፍሪካውያን ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያለውን ግንኙነት መጠየቅ እና ለምንድን ነው በዚህ በሀብታም ባለጸጋ አህጉር ውስጥ ድህነት የበዛበት የሚሉ ጥያቄዎችን" እያነሱ መሆኑን ይናገራሉ።
እ.ኤ.አ. በ 2022 በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ የትራኦሬ አገዛዝ የቀድሞ የቡርኪናፋሶን ቅኝ ገዢ ፈረንሳይን ምትክ ከሩሲያ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት እንድትመሠርት አድርጓል።
ይህም የሩስያ ፓራሚሊተሪ ብርጌድ ማሰማራትን ጨምሮ፣ የግራ ዘመም ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ አድርጓል።
ይህ በመንግሥት ባለቤትነት የተያዘ የማዕድን ኩባንያ ማቋቋምን ያካትታል፤ የውጭ ኩባንያዎች በአካባቢያቸው ስራዎች ላይ 15 በመቶ ድርሻ እንዲሰጡት እና ክህሎቶችን ለቡርኪናፋሷዊ ሰዎች ማስተላለፍን ይጠይቃል።
ደንቡ በቡርኪናፋሶ የወርቅ ኢንደስትሪ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ በሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ፈቃድ ለተሰጠው የሩስያ ማዕድን አውጪ ኖርድጎልድ ላይም ተፈፃሚ ሆኗል።
ቡርኪናፋሶ ከማዕድን ሀብቷ ተጠቃሚ እንድትሆን ትራኦሬ "አብዮት" ብሎ የሰየመው አካል፣ ወታደራዊው ጁንታ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ማጣሪያ በመገንባት ብሔራዊ የወርቅ ክምችት በማቋቋም ላይ ነው።
ነገር ግን፣ የምዕራቡ ዓለም ኩባንያዎች አስቸጋሪ ጊዜ እያጋጠማቸው ይመስላል፣ የአውስትራሊያ ዋና መሥሪያ ቤት የሆነው ሳራማ ሪሶርስ በ2024 መገባደጃ ላይ የአሰሳ ፈቃድ መነሳቱን ተከትሎ በቡርኪናፋሶ ላይ የግልግል ክስ መስርቶ ነበር።
ወታደራዊው ጁንታ መንግሥት ከዚህ ቀደም በለንደን በተመዘገበ ኩባንያ ባለቤትነት የተያዙ ሁለት የወርቅ ማዕድን ማምረቻዎችን ወደ መንግሥት ባለቤትን ያዘዋወረ ሲሆን፣ ባለፈው ወር ተጨማሪ በውጭ አገር ኩባንያዎች የተያዙ የማዕድን ማምረቻዎችን ለመቆጣጠር ማቀዱን ተናግሯል።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የደህንነት ጥናቶች ተቋም ተመራማሪ ሄኖክ ራንዲ አይኪንስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የትራኦሬ ሥር ነቀል ለውጥ በአፍሪካ ያለውን ተወዳጅነት ከፍ አድርጎታል።
ሚስተር አይኪንስ "እሱ አሁን ተወዳጅ እንኳን ባይሆን በአፍሪካ በጣም ታዋቂ ፕሬዝዳንት ነው" ብለዋል።
የእሱ ተወዳጅነት አብዮታዊ ምስሉን ለማጠናከር የታቀዱ ብዙ አሳሳች ልጥፎችን ጨምሮ የትራኦሬ እውቅና በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ነው የተፋፋመው።
እንደ አር ኬሊ፣ ሪሃና፣ ጀስቲን ቢበር እና ቢዮንሴ ያሉ የሙዚቃ ኮከቦች በሰው ሰራሽ አስተውሎት የመነጩ ቪዲዮዎች በዘፈን ሲያሞጋግሱት ታይተዋል፤ ምንም እንኳን ምንም ያደረጉት ነገር የለም።
ተመራማሪዋ ኦቺንግ እንደተናገሩት ትራኦሬ እ.ኤ.አ. በ2023 በሩስያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የአፍሪካውያን መሪዎች "ኢምፔሪያሊስቶች ገመዱን በሳቡት ቁጥር የሚጨፍሩ አሻንጉሊቶችን መምሰል ያቁሙ" በማለት የአፍሪካውያንን ቀልብ ስቧል።
ይህ ንግግር የትራኦሬ የፓን አፍሪካኒዝምን ምስል በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና በተጫወተው የሩስያ መገናኛ ብዙኃን በሰፊው ተሰራጭቷል።
ለንግግራቸው ምስጋና ይግባውና በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ በመገፋቱ፣ በጉባኤው ላይ ያቀረበው ተማጽኖ በአፍሪካ አሜሪካውያን እና ጥቁር ብሪታንያውያን ዘንድ ጨምሮ በመላው ዓለም ተስፋፍቷል ሲሉ ተመራማዊዋ ጠቁመዋል።
"በዘረኝነትን፣ ቅኝ ግዛትን እና ባርነት ያለፈ ማንኛውም ሰው ከመልእክቶቹ ጋር ሊዛመድ ይችላል" የሚሉት ተመራማሪዋ፤ ምንም እንኳን ስማቸውን አምታቶ ትራኦሬን እንደ ቡርኪናፋሶ በመጥቀሱ ስላቅ አስተናግዶ ቢሰርዘውም አፍሪካ አሜሪካዊው ራፐር ሜክ ሚል ባለፈው አመት መጨረሻ ላይ "ጉልበቱን እና ልቡን" ምን ያህል እንደወደደው በመግለጽ በኤክስ ገጹ ያጋራውን ልጥፍ ይጠቅሳሉ።
ነገር ግን የፈረንሣዩ ፕሬዝዳንት ቀልብ ትራኦሬን አይወደውም።
ፕሬዝዳንቱ ትራኦሬን "በራስ ፓን አፍሪካውያን ነን በሚሉ እና በኒዮ ኢምፔሪያሊስቶች መካከል ያለው ቅጥ አልባ ጥምረት" አካል እንደሆነ ገልፀውታል።
ሻምበል ትራኦሬ ዝናው ቢናኝም ለ10 ዓመታት የዘለቀውን እና የጎሳ መከፋፋል እንዲባባስ እና በአንድ ወቅት ሰላማዊ ወደነበሩት እንደ ቤኒን ወዳሉ ጎረቤቶች እየተዛመተ ያለውን የእስላማዊ አመፅን ለማስቆም የገባውን ቃል አልፈጸመም።
የሱ ጁንታ ተቃዋሚዎችን፣ ሚዲያዎችን እና የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖችን ጨምሮ ተቃዋሚዎችን አፍኗል።
የሕክምና ባለሙያ እና ባለስልጣኖችን ጨምሮ ተቺዎቹን ከጂሃዲስቶች ጋር በሚደረገው ጦርነት ወደ ጦር ግንባር በመላክ እንዲቀጡ አድርጓል።
የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሪናልዶ ዴፓኝ ትራኦሬ እንዲህ ያለውን ድጋፍ ያገኙበት ምክንያቱ "ወጣት ሕዝብ ባለበት አገር ውስጥ ያለ ወጣት ነው" ይላሉ።
በቡርኪናፋሶ አማካይ ዕድሜ 17.7 ዓመት ነው።
"እሱ ሚዲያ አዋቂ ነው፣ እናም ራሱን እንደ ቶማስ ሳንካራ በመሳል ያለፈውን ጊዜ ታዋቂነቱን ለመገንባት ተጠቅሞበታል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"እና እሱ የፖለቲካውን ጥበብ ያውቃል - በጦርነት የተጎዳን ሕዝብ እንዴት የተሻለ የወደፊት ጊዜ እንዳለ እንዲሰማው ማድረግ በዚያ ጨዋታ ላይ በጣም ጥሩ ነው።"
ሳንካራ በ1983 በ33 አመቱ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ላይ ሲወጣ "አባት አገር ወይም ሞት እናሸንፋለን!" በሚል መሪ ቃል ሕዝቡን አሰባስቦ ነበር።
ነገር ግን ትራኦሬ ስልጣን እስኪጨብጥ ድረስ ቡርኪናፋሶን ወደ ፈረንሳይ የፖለቲካ ምህዋር እንድትመለስ ባደረገ በሌላ መፈንቀል መንግሥት ከአራት ዓመት በኋላ ሳንካራ ተገደለ።
ቀደም ሲል በኮፊ አናን ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ማዕከል የሰሩት የጋና የፀጥታ ተንታኝ ፕሮፌሰር ክዌሲ አኒንግ የወታደራዊ መሪው ተወዳጅነት በአህጉሪቱ በተለይም በምዕራብ አፍሪካ እየተከሰተ ያለውን የፖለቲካ ለውጥ ያሳያል ብለዋል።
እ.ኤ.አ. በ 2024 በአፍሮባሮሜትር በ 39 አገሮች ውስጥ የተደረገ ጥናት ለዲሞክራሲ ያለው ድጋፍ ቀንሷል ፣ ምንም እንኳን በጣም ታዋቂው የመንግሥት መዋቅር ቢሆንም።
ፕሮፌሰር አኒንግ "ዲሞክራሲ ለወጣቶች ተስፋ መስጠት ተስኖታል፣ ስራ ወይም የተሻለ ትምህርትና ጤና አላመጣም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ትራኦሬ "አማራጭ እያቀረበ እና የሁለት ታሪካዊ ዘመናትን መንፈስ እንደገና እየያዘ ነው" ሲሉ አክለዋል።
በጥር ወር የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ማሃማ ቃለ መሃል በፈጸሙበት ወቅት ትዕይንቱን የሰረቀው ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሰው፤ በሰገባው ሸጉጥ የታጠቀው ትራኦሬ ነበር።
ፕሮፌሰር አኒንግ "21 የአገር መሪዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ትራኦሬ ወደ ውስጥ ሲገባ ቦታው ሌላ ሆነ። የጋናው ፕሬዝዳንት ጠባቂዎች እንኳን እሱን ተከትለው ይሮጡ ነበር" ብለዋል።
ትራኦሬ በእግራቸው ለመራመድ ለሚታገሉ ነገር ግን ምርጫ በማጭበርበር ስልጣን የሙጥኝ ላሉት የአህጉሪቱ መሪዎች በጣም ተቃራኒ ምስል አቅርቧል።
"ትራኦሬ ቄንጠኛ እና በራስ የመተማመን መንፈስ ያለው በጣም የበራ ፊት እና ትንሽ ፈገግታ ያለው ነው። ደግሞ ኃይለኛ ተናጋሪ ነው እናም ራሱን እንደ የሕዝብ ሰው ያሳያል።"
ከሩሲያ ጋር የተቆራኘው ጁንታ በኢኮኖሚው ዘርፍ መጠነኛ መሻሻል ማሳየቱን በሚያመላክት መልኩ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ በአጠቃላይ ጥሩ ግምገማ ሰጥተው ነበር።
በሚያዝያ መጀመሪያ ላይ ባወጣው መግለጫ አይኤምኤፍ ምንም እንኳን "አስቸጋሪ ሰብዓዊ እና ደኅንነት" አካባቢ ቢሆንም በ2025 ኢኮኖሚው "ጠንካራ" ሆኖ ይቀጥላል ብሎ እንደሚጠበቅ እና አገዛዙ የአገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ፣ የደመወዝ ክፍያን በመያዝ እና በትምህርት፣ በጤና እና በማኅበራዊ ጥበቃ ላይ የሚወጣውን ወጪ በማሳደግ "የሚያስመሰግን እድገት" አድርጓል ብሏል።
የዓለም ባንክን በተመለከተ፣ የዋጋ ግሽበት በ2023 ከ 0.7 በመቶ በ2024 ወደ 4.2 በመቶ ከፍ ብሏል፣ ነገር ግን በቀን ከ2.15 ዶላር በታች የሚኖሩ ሰዎችን የሚያመለክተው እጅግ የከፋ የድህነት መጠን በግብርና እና በአገልግሎት ዘርፍ በታየው "በጠንካራ እድገት" ምክንያት በሁለት መቶኛ ነጥብ ወደ 24.9 በመቶ ዝቅ ብሏል።
በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት እነዚህ ሪፖርቶች ቢወጡም ከፈረንሳይ እና ከአሜሪካ ጋር ያለው ግንኙነት ቀዝቃዛ ሆኖ ቆይቷል።
የአሜሪካው የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ማይክል ላንግሌይ፣ ትራኦሬ የቡርኪናፋሶን የወርቅ ክምችት ከአገሪቱ ጥቅም ይልቅ ለጁንታዎቹ ጥበቃ እየተጠቀመበት ነው የሚለው ንግግር የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ነው።
ይህ የሩሲያ ኃይሎች በቡርኪናፋሶ የወርቅ ኢንደስትሪ ውስጥ ድርሻ እንዲኖራቸው ትሬኦሬን እየደገፉ ነው የሚለውን የአሜሪካን እና አንዳንድ የአፍሪካ አጋሮቿን የረዥም ጊዜ ዕይታ የሚያመለክት ይመስላል።
የጄኔራል ላንግሌይ በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በአሜሪካ ሴኔት ኮሚቴ ችሎት ላይ የሰጡት አስተያየት ጀግናቸው እየተተቸ እንደሆነ በሚሰማቸው የካፒቴኑ ደጋፊዎች መካከል ቁጣን አስነስቷል።
ብዙም ሳይቆይ የቡርኪናቤይ ጁንታ የመፈንቅለ መንግሥት ሴራ ማክሸፉን እና የሴራው ጠንሳሾች በጎረቤት አገር ኮትዲቯር መሆናቸውን ገልጿል።
በጊዜው ጄኔራል ላንግሌይ ኮትዲቯርን መጎብኘታቸው ነገሩን አባብሶት ነበር።
ኮትዲቯር በምንም ዓይነት ሴራ ውስጥ እንዳልተሳተፈች ስትገልጽ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ኮማንድ ዕዝ በበኩሉ የጄኔራል ላንግሌይ ጉብኝት "አክራሪነትን" ጨምሮ "የጋራ የጸጥታ ችግሮችን" ለመፍታት ያተኮረ ነበር ብሏል።
ሆኖም ወታደራዊው ጁንታ አጋጣሚውን በመጠቀም "ኢምፔሪያሊስቶች" እና "ላኪዎቻቸው" ሻምበል ትራኦሬን ከስልጣን ለማውረድ እየሞከሩ ነው በሚል ስጋት በቡርኪናፋሶ ዋና ከተማ ትልቁን ሰልፍ አዘጋጅቷል።
"ኮሊን ፓውል ስለዋሸ፣ ኢራቅ ወድማለች። ባራክ ኦባማ ዋሽተዋል፣ ጋዳፊ ተገድለዋል፣ በዚህ ጊዜ ግን ውሸታቸው በእኛ ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም" ሲል አንድ ተቃዋሚ ሙዚቀኛ ኦሲቢ ጆሃን ለአሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግሯል።
በተመሳሳይ ቀን ለንደንን ጨምሮ ለትራኦሬ የድጋፍ ሰልፎች ተካሂደዋል።
በመቀጠልም "ለአዲሲቷ ቡርኪናፋሶ እና አዲስ አፍሪካ" ራዕያቸውን ለተካፈሉት ያለውን አድናቆት በፈረንሳይኛ እና በእንግሊዘኛ ልጥፎች በማኅበራዊ ሚዲያ አጋርቷል።
በተጨማሪም "በአንድነት፣ ኢምፔሪያሊዝምን እና የእጅ አዙር-ቅኝ አገዛዝን እናሸንፋለን፣ የተከበረች እና ሉዓላዊት አፍሪካ" በማለት ተናግሯል።
ለወጣቱ ሻምበል ነገሮች እንዴት ይቋጫሉ ብሎ መናገር ባይቻልም እሱ፣ ከማሊ እና ኒጀር ወታደራዊ መሪዎች ጋር፣ በእርግጠኝነት ምዕራብ አፍሪቃን አነቃንቋል እና ሌሎች ግዛቶችም የፈረንሳይ ወታደሮችን ለቀው እንዲወጡ በማዘዝ የእነሱን አርአያነት ተከትለዋል ።
ሦስቱ ወታደራዊ አገዛዝ ጎረቤቶችም ከአካባቢው የንግድ እና የጸጥታ ቡድን ኢኮዋስ በመውጣት የራሳቸውን ጥምረት ፈጥረው ወደ አገራቸው በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የ0.5 በመቶ ቀረጥ እንደሚጥሉ በማወጅ የየራሳቸውን ጥምረት ፈጥረዋል።
ሚስተር አይኪንስ ትራኦሬ ከሌሎች ሊማር እንደሚችል ጠቁመው ራውልግስ በ32 ዓመቱ በጋና ስልጣን ሲይዝ "ትንሹ ኢየሱስ" በመባል ይታወቅ ነበር።
ነገር ግን ከ 19 አመታት በኋላ የተደበላለቀ ቅርስ ትቷል። "ዘላቂ" ዲሞክራሲ ለመፍጠር ቢረዱም ሙስናን ማስቆም አልቻለም።
"ለዘላቂ ውርስ" ሚስተር አይኪንስ እንዳሉት ትራኦሬ ሰላምን በማስፈን እና ጠንካራ የመንግሥት ተቋማትን በመገንባት መልካም አስተዳደርን ለማምጣት ስልጣንን "ግላዊ" ከማድረግ እና ተቃዋሚዎችን ከማፈን ይልቅ ትኩረት መስጠት አለበት ብለዋል ።