ትራምፕ ቅንጡ 747 አውሮፕላን ከኳታር "በስጦታ" ሊቀበሉ ነው

ዋይት ሐውስ ከኳታር የንጉሣዊ ቤተሰብ ጋር ለፕሬዝዳንቱ መገልገያ የሚውል ቅንጡ አውሮፕላን ለመረከብ ድርድር እያደረገ መሆኑ ተገለፀ።

ኳታር ባወጣችው መግለጫ አውሮፕላኑ በስጦታ የሚሰጥ ነው የሚለውን አስተባብላለች። ነገር ግን "ለጊዜያዊ ግልጋሎት" ጥቅም ላይ የሚለው አውሮፕላንን ለማስተላለፍ በሁለቱ አገራት መካከል ንግግር እየተደረገ መሆኑን ገልጻለች።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ እንደዘገበው አውሮፕላኑ ለትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ቤተመጻሕፍት በስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ ላይ በልግስና ይሰጣል።

ይህ ዜና የተሰማው በዚህ ሳምንት ትራምፕ ሁለተኛውን የስልጣን ዘመናቸውን ከጀመሩ ወዲህ ትልቅ የውጪ አገር ጉዞ በተባለው የመካከለኛው እሥራቅ ጉብኝታቸው ኳታርን ለመሄድ እየተዘጋጁ ባለበት ወቅት ነው።

በአሜሪካ የኳታር የሚዲያ አታሼ አሊ አል አንሳሪ ድርድሩ በኳታር እና በአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር መካከል እየተካሄደ ነው።

"ጉዳዩ በሁለቱም የሕግ ክፍሎች በኩል የሚታይ ሲሆን እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ውሳኔ ላይ አልተደረሰም" ብለዋል።

የሲቢኤስ ኒውስ ምንጮች እንደተናገሩት አውሮፕላኑ አስፈላጊው እድሳት እስኪደረግለት እና የደህንነት ባለሥልጣናት ይሁንታን እስኪያገኝ ድረስ ጥቅም ላይ አይውልም

በትራምፕ ተቺዎች ዘንድ የአውሮፕላኑ ዋጋ እና አያያዙ ሕጋዊ እና ግብረ ገባዊ ጥያቄዎችን ማንሳቱ አይቀርም።

እሁድ ዕለት የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክረተሪ ካሮላይን ሌቪት "ማንኛውም ከውጪ መንግሥት የሚሰጥ ስጦታ ሁል ጊዜ ሁሉንም የሚመለከታቸው ሕጎች ሙሉ በሙሉ ማክበሩን ካየን በኋላ ነው የምንቀበለው ። የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ግልፅነት እንዲኖር ቁርጠኛ ነው" ብላለች።

ከኳታር ጋር የሚደረገውን ንግግር በሚመለከት በትሩዝ ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ እሁድ ዕለት አውሮፕላኑን በስጦታ እንደሚረከቡት ገልፀው ያለምንም ወጪ እንዲጠቀሙበት ብቻ እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል።

"የመከላከያ ሚኒስትር ስጦታ፣ ያለምንም ክፍያ ያገኘን ሲሆን 40 ዓመት የሞላውን 747 አውሮፕላን ኤርፎርስ ዋን ለጊዜው ይተካል። ግልጽ እና ይፋ በሆነ ልውውጥ የተገኘ ነው፣ ስለዚህ ሁሌም ቀና ነገር የማይታያቸው ዲሞክራት ወንድሞች እንድንከፍል እየጠየቁን ነው፥ ከፍተኛ ዶላር፣ ለአውሮፕላኑ" ሲሉ ጽፈዋል።

ዋይት ሐውስ አሁን እየተጠቀመባቸው ያሉት አውሮፕላኖች ለፕሬዝዳንት አገልግሎት ተብለው የተበጁ ሁለት ቦይንግ 747-200B አውሮፕላኖችን ሲሆን፣ ልዩ የመገናኛ መሳሪያዎች እና የቢሮ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች፣ የስብሰባ አዳራሽ መያዛቸውን የአሜሪካ አየር ኃይል መረጃ ያሳያል።

አውሮፕላኖቹ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1990 እና 1991 ጀምሮ አገልግሎት ላይ ውለዋል።

ኤርፎርስ ዋን አውሮፕላኖች አብዛኛውን ጊዜ ወደ ቀጣይ ፕሬዝዳንቶች ይተላለፋሉ።

በብሔራዊ ቤተ መዛግብት መረጃ መሠረት የሬገን ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መጽሐፍት ብቻ ኤር ፎርስ 1 አውሮፕላን ያለው ሲሆን ከመሰጠቱ በፊት ሰባት ፕሬዚዳንቶችን አገልግሏል።

ኤቢሲ ኒውስ እንደዘገበው ኳታር ዘመናዊ የሆነውን ቦይንግ 747-8 አውሮፕላን "የቤተ መንግሥት ሰዎች የሚጠቀሙበትን" በስጦታ ለመስጠት ተዘጋጅታለች።

ቦይንግ ለዋይት ሐውስ አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለማቅረብ ውል ተፈራርሞ የነበረ ቢሆንም ትራምፕ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ኩባንያው ከተያዘለት ጊዜ ዘግይቷል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

የትራምፕ አስተዳደር በመጀመሪያ የአስተዳደር ዘመኑ ከቦይንግ ጋር ሁለት ልዩ 747-8 አውሮፕላኖች ለማግኘት ተነጋግሮ ነበር።

ቦይንግ አውሮፕላኖቹ እአአ እስከ 2027 ወይም 2028 ድረስ ዝግጁ እንደማይሆኑ አስታውቋል።

ትራምፕ በየካቲት ወር "በጭራሽ፤ በቦይንግ ደስተኛ አይደለሁም። ለማስረከብ ረዥም ጊዜ ወሰደባቸው። ታውቃላችሁ፣ ኤር ፎርስ ዋን፣ ኮንትራቱን የሰጠናቸው ከረዥም ጊዜ በፊት ነበር" ብለዋል።

"አውሮፕላን እንገዛለን፤ ወይ እናገኛለን አለበዘዚያም የሆነ ነገር።"

ትራምፕ በመጀመርያው የሥልጣን ዘመናቸው ከኳታር ጋር መልካም የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ነበራቸው።

ኳታር በ2019 በርካታ የአሜሪካ አውሮፕላኖችን እነደምትገዛ አስታውቃ ነበር።

ኳታር ከዚህ በፊት የግል አውሮፕላኖችን ለሌሎች አገራት በስጦታ ሰጥታ ታውቃለች።

ከዚህ በፊት በ2018 ቅንጡ አውሮፕላን ለቱርክ በስጦታ ሰጥታ ታውቃለች።