አሜሪካ እና ቻይና ለሦስት ወር ታሪፎቻቸውን ለመቀነስ ተስማሙ

አሜሪካ እና ቻይና አንዳቸው በሌላኛቸው ምርቶች ላይ የጣሉትን ታሪፍ ለ90 ቀናት ለመቀነስ ከስምምነት ደረሱ።

የአሜሪካ ግምጃ ቤት ዋና ፀኃፊ ስኮት ቤሴንት ለ90 ቀናት ሁለቱም አገራት የጣሉትን ታሪፍ በ115 በመቶ ዝቅ ለማድረግ መስማማታቸውን ተናግረዋል።

ሁለቱ ኃያላን አገራት እዚህ ስምምነት ላይ መድረሳቸው የተገለፀው በሳምንቱ መጨረሻ በስዊትዘርላንድስ በዝግ ንግግር ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ ነው።

ይህ ንግግር ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ከጣሉ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የተደረገ ውይይት ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ 145 በመቶ ታሪፍ ሲጥሉ ቤጂንግ በምላሹ ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ 125 በመቶ ታሪፍ ጥላለች።

ይኹን አንጂ አሁን አሜሪካ በቻይና ምርቶች ላይ የጣለችው ታሪፍ ለ90 ቀናት ወደ 30 በመቶ ዝቅ ስታደርግ ቻይና በአሜሪካ ምርቶች ላይ የጣለችው ታሪፍ ደግሞ እንዲሁ ለተመሳሳይ ቀናት ወደ 10 በመቶ ይቀንሳል።

አሜሪካ ሕገወጥ የሆነውን የፌንታኒል ኦፒየድ ዕጽ ለመቆጣጠር በሚል ያካተቻቸው እርምጃዎች እንዳሉ መሆናቸው ተገልጿል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት የቻይና መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ባሳየው ፈቃደኝነት መደነቃቸውን ተናግረዋል።

አሜሪካ እና ቻይና የገቡበት የንግድ ጦርነት በፋይናንስ ገበያው እና በዓለም ላይ ግሽበትን ያስከትላል የሚል ፍርሃት ቀስቅሶ ነበር።

የአሜሪካ ግምጃ ቤት ዋና ጸሐፊ ስኮት ቤሴት ውይይቱን "ገንቢ እና ውጤታማ" ሲሉ የገለፁት ሲሆን የቻይናው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሂ ሊፌንግ በበኩላቸው ንግግሮቹ "በጥልቀት" እና "በመግባባት" የተካሄዱ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በጄኔቭ ሲደረግ የቆየው የሁለት ቀን ንግግር መጠናቀቁን ተከትሎ የአሜሪካ የንግድ ተወካይ አምባሳደር ጃሚየሰን ግሪር "ከቻይናውያን አጋሮቻችን ጋር የደረስንበት ስምምነት" አሜሪካ ያለባትን 1.2 ትሪሊየን የንግድ ጉድለት ይቀንሳል ብለዋል።

ቤሴንት አሜሪካ እና ቻይና በመካከላቸውን የተፈጠረውን የንግድ ጦርነት በማቀዛቀዝ ረገድ "ወሳኝ የሆነ እርምጃ" ላይ መድረሳቸውን ሲናገሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሂ ደግሞ ንግግሩ "ለሁለቱ አገራት ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ነገር ግን ለዓለም አቀፉ ምጣኔ ኃብት መረጋጋት እና እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሂ ሁለቱ ተደራዳሪ ወገኖች በዋና ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውን እንዲሁም የምጣኔ ኃብት እና ንግድ ምክክር መንገዶችን የሚያሳልጥ ቡድን ለመመስረት መስማማታቸውን ተናግረዋል።

የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ተቆጣጣሪ የሆኑት ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ ንግግሩን "ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የሚደረግ ጉዞ" ሲኡ አድንቀውታል።

በመግለጫቸው "ሁለቱም አገራት ውጥረቶችን የሚቀንሱ፣ የሚታየውን ሁኔታ የሚያድሱ እና በባለብዙ ወገን የግብይት ስርዓት ላይ ያላቸውን እምነት በማጠናከር ተግባራዊ መፍትሄዎችን በማዘጋጀት ግስጋሴያቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስባለሁ" ብለዋል።

ውይይቱ በጄኔቭ እንደተጀመረ ቅዳሜ ዕለት ትራምፕ በሁለቱ አገራት ግንኙነት ላይ የተደረገውን ንግግር ግንኙነታቸውን "ዳግም ማስጀመር" ሲሉ አድንቀውታል።

አርብ ዕለት ውይይቱ ከመጀመሩ በፊት የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት ዋሽንግተን ብቻዋን ታሪፍ እንደማትቀንስ ገልፀው፣ ቻይና የራሷን ድርሻ መወጣት አለባት ብለዋል።

ሁለቱም ወገኖች ከስብሰባው በፊት የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎችን የሰጡ ሲሆን ቤጂንግ ዩናይትድ ስቴትስ ታሪፎችን ማቃለል አለባት ስትል፣ ቤሴንት ግን ትኩረቱ "ውጥረት ማርገብ" ላይ እንደሆነ እና ይህ "ትልቅ የንግድ ስምምነት" እንዳልሆነ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረው ነበር።

የቻይና መንግሥት ሚዲያ እንደዘገበው ቤጂንግ ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር የወሰነችው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚጠብቀውን፣ የአገሪቱን ጥቅም እና የአሜሪካን ነጋዴዎች ጥሪን ሙሉ በሙሉ በማጤን ነው።

በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለው የንግድ ጦርነት የተካረረው ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ወር ከቻእና የሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሆነታሪፍ መጣላቸውን ተከትሎ ነው።