ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች "አንዳቸው የሌላኛቸውን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ" ያላቸው አጋርነት አጸኑ
ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች "አንዳቸው የሌላኛቸውን ሰላም እና ደኅንነት" እንዲሁም "የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ" ያላቸውን ስራቴጂክ አጋርነት በድጋሚ አረጋገጡ።
የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ባቀጡት መግለጫ "ቀጣናዊ መረጋጋትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት" ያላቸውን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል።
ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶቹ ማክሰኞ ታኅሣሥ 28/2018 ዓ.ም. የጋራ መግለጫውን ያወጡት፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሼህ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሥራ ጉብኝት ተከትሎ ነው።
የአቡዳቢው ሚኒስትር ዲኤታ፤ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ ተገናኝተው "ቀጣናዊ ሰላም እና ደኅንነት" ላይ ሁለቱ አገራት ያላቸውን "የጋራ ፍላጎት" በተመለከተ "ምልከታቸውን እንደተለዋወጡ" ተገልጿል።
ምሽት ላይ የወጣው የጋራ መግለጫም ይህንኑ የሰላም እና ደኅኅንነት ጉዳይ አንስቷል። "ሁለቱም ወገኖች አንዳቸው የሌላኛቸውን ሰላም እና ደኅንነት፣ የግዛት አንድነት እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ለመደገፍ እና ለማስተዋወቅ ያላቸውን ሁለንተናዊ እና ስትራቴጂካዊ አጋርነት በድጋሚ አረጋግጠዋል" ይላል መግለጫው።
ዶ/ር ጌዲዮን እና ሼህ ሻክቡት ከሁለትዮሽ ጉዳዮችም በተጨማሪ "በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰላም እና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ የተመዘገቡ ቁልፍ ለውጦችን" እንደገመገሙ መግለጫው ያስረዳል።
"ሁለቱም ወገኖች መረጋጋትን ለማምጣት እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ያላቸውን ቁርጠኝነ" መግለጻቸውን ባሰፈረው መግለጫ ላይ፤ የሱዳን የእርስ በስር ጦርነት ጉዳይ በአጽንኦት ተነስቷል።
ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ጦርነት እየታመሰች ባለችው ሱዳን የሚገኙ ተፋላሚ ኃይሎች "በንጹሃን ላይ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች" አውግዘዋል። "ሁለቱም ተፋላሚ አካላት ለንጹሃን እና ለሰብአዊ ድጋፍ ሠራተኞች ጥበቃ" እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ጦርነቱን የሚቋጭበትን መንገድ በተመለከተም፤ "የእርስ በርስ ጦርነቱን የማቆም ቀዳሚ ኃላፊነት የተፋላሚ ወገኖች መሆኑን ሁለቱም ወገኖች አስምረውበታል" የሚለው መግለጫው ላይ ሰፍሯል።
"በአስቸኳይ ወደ ዘላቂ ተኩስ አቁምነት የሚያድግ የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስለማድረግ አስፈላጊነት" በመግለጫቸው ያነሱት ሁለቱ አገራት፤ "በመላው ሱዳን አስቸኳይ፣ ፈጣን እና ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲኖር" ጠይቀዋል።
"በሲቪል የሚመራ ገለልተኛ መንግሥትን ለመመሥረት መንገድ የሚጠርግ አካታች እና ግልጽ የሽግግር ሂደት" መኖሩ አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
የተባበሩት መንግሥታ የሱዳን ጦርነት እየተቀጣጠለ ለመምጣቱ አንዱ ምክንያት "የውጭ ድጋፍ" መሆኑን ቢያነሳም፤ የትኛውንም አካል በስም አይጠቅስም። የባሕረ ሰላጤዋ አገር የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከዚህ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ስሟ ይነሳል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ የተለያዩ አካላት አቡ ዳቢ፤ ከሱዳን ጦር ጋር እየተዋጋ ላለው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሳሪያ እንደምታቀርብ በማንሳት ይከስሳሉ። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ግን ይህንን ክስ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋል።
የኤምሬቶች እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በጋራ ያወጡት መግለጫም "ሁለቱም ወገኖች ሰላምን ለማስፈን፣ ቀጣናዊ መረጋጋትን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እና የቆየ ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ለማጠናከር" የጋራ ቁርጠኝነት እንዳላቸው ጠቅሷል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣት ወዲህ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ትብብር በብዙ መልኩ የጠነከረው ኤምሬቶች፤ እንደ የሰላም እና ደኅንነት እንዲሁም ኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት ባሉ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አበባ አጋር ነች።