ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች በዱባይ ቤት መግዛትን እየመረጡ ያሉት ለምንድን ነው?

በሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች የተንቆጠቆጠችው የባሕረ ሰላጤዋ ዱባይ ባለፉት ዓመታት ያሳየችውን ፈጣን ዕድገት በቃኝ ያለች አትመስልም። አሁንም እንደ አዲስ ግዙፍ ሕንጻዎችን በመገንባት ተወጥራለች።

ታላቁን የአረብ ባሕር ተንተርሳ የተመሠረተችው ዱባይ አብዛኛዎቹ ሕንጻዎቿ ከባሕር ዳርቻዎች ላይ የቆሙ ናቸው። አሁን አሁን ግን ሕንጻዎቹ ወደ ባሕር ዳርቻ መሄድ አይጠበቅባቸውም። ምስጋና ለቴክኖሌጅ ይሁንና ባሕሩ በተፈለገው ቦታ ሁሉ ይፈጠራል።

ዱባይ ከሰባቱ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ግዛቶች መካከል በቆዳ ስፋቷ ሁለተኛ ናት። በቱሪዝም፣ በንግድ እና በሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ማዕከልነት ደግሞ ከኤምሬትስ ግዛቶች ቀዳሚዋ ነች።

ዱባይ የሪል ስቴት ኢንቨስትመንቷን በሁሉም አቅጣጫዎች አስፋፍታለች። ደቡባዊ የግዛቷ ክፍል ወይም ደግሞ ደረቅ መሬት ያለበት አካባቢ ደግሞ ከፍተኛው የሪል ኢስቴት ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ይመስላል።

ይህ የዱባይ ክፍል የአረብ ባሕር የማይደርስበት፣ የአገሬው ሰው በሰፊው ያልሰፈረበት፣ እንዲሁ ምድረ በዳ የሚመስል አካባቢ ነው። ዱባይ ከማዕከላዊ ከተማዋ ወደ አገሪቱ [የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ] መዲና አቡ ዳቢ እየሰፋች ትገኛለች።

በዚሁ ስፍራ 20 የሚደርሱ የሪል ስቴት አልሚዎች ይሳተፋሉ። እያንዳንዱ አልሚ ከአንዲት መለስተኛ ከተማ ስፋት ጋር የሚስተካከል መሬት አጥሮ ዘመናዊ የሕንጻ ጫካ ይገነባል።

የመንገድ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች እጅግ የተሳለጡ ናቸው። የአረብ ባሕር ከመነሻው በቀላሉ ተጠልፎ በተፈለገበት ቦታ ሁሉ እየተርመሰመሰ ለእነዚህ አዳዲስ መንደሮች ተጨማሪ ውበት ያጎናጽፋል።

አብዛኛዎቹ አልሚዎች የቤቶቻቸውን ሞዴሎች የሚያሳዩባቸው ሰፋፊ ቅጥር ግቢዎች አሏቸው። በአንደኛው የሪል ስቴት አልሚ የሞዴል ቤቶች ማሳያ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተገኝተናል።

በዚህ ግቢ ውስጥ አልሚው የሚገነባቸው የሪል ስቴት ቤቶች በአነስተኛ የመስታውት ፍሬም ውስጥ ሞዴላቸው ተቀምጧል። በጊዜያዊነት የተሠሩ የሚመስሉ ግን ውሳጣቸው እጅግ ዘመናዊ በሆኑ ቁሶች የተገነቡ ቤቶቹም በዚሁ ግቢ ውስጥ ይገኛሉ።

ከአንዳንዶቹ ዘመናዊ የሪል ስቴት ቤቶች ጋር ለማስረከብ ያዘጋጇቸው ቅንጡ ተሽከርካሪዎችንም እዚሁ ግቢ ውስጥ እንደተጨማሪ የገበያ መሳቢያነት በማሰብ አስቀምጠዋቸዋል። በግቢው ውስጥ የኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ሰንደቅ ዓላማዎች ከፍ ብለው ተሰቅለው ይታያሉ።

ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከመላው ዓለም የተሰባበሰቡ የሪል ስቴት አሻሻጮች በእዚህ ቅጥር ግቢ ውስጥ ይርመሰመሳሉ።

የሪል ስቴት አሻሻጮቹ እነዚህን ሞዴል ቤቶች እና የሚገኙባቸውን አካባቢዎች ለገዢዎች ሲያስረዱ ደንቀፍ ሳይሉ በሚገርም ፍሰት በሚያማልል ሁኔታ ነው።

በብዙ ቋንቋዎች እየተግባቡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የዓለም ቤት ፈላጊዎች በአንድ ቦታ ላይ ይስተናገዳሉ። ይህ ግቢ አብዛኛው የዱባይ ሪል ስቴት ገዢ ቀጣይ ቤቱን ለመግዛት የሚወስንበት ቦታ ነው።

አሻሻጮቹ [ደላሎቹ] በአገሪቱ መንግሥት ፈቃድ የተሰጣቸው፣ ከአልሚ ድርጅቶች ጋርም የንግድ ስምምነት ያላቸው ናቸው። ብሩክ ተከስተ ከታዋቂ ኢትዮጵያውያን የሪል ስቴት አሻሻጮች አንዱ ነው።

ብሩክ 10 ሠራተኞችን በሥሩ በመቅጠር 'ብሩክ ሪል ስቴት' የሚል ድርጅት አቋቁሞ ከአንድ ዓመት በላይ በዚህ ሥራ ላይ ቆይቷል። በዋናነት ለኢትዮጵያውያን እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ገዢዎችም ቤቶችን ያሻሽጣል።

በሥራ ቆይታውም ከ100 ለሚልቁ ኢትዮጵያውያን በዱባይ ቤት ማሻሻጡን ይናገራል። እንደ ብሩክ ገለጻ ሰዎች በዱባይ ቤት የሚገዙባቸው ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው።

“የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ ዋነኛው ምክንያታቸው ነው” የሚለው ብሩክ፣ በሌላ በኩል ብዙ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን “ለኢንቨስትመንት አማራጭነት ቤቶቸን ይገዛሉ” ይላል።

በተለይ ቤቱን በማከራየት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንደ ሁነኛ አማራጭ ቆጥረው ቤት የሚገዙ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውንመ ብሩክ ይገልጻል።

ከዚሀ ቀደመ ሮይተርስ ያረበው አንድ ጥናታዊ ዘገባም ይህንን ያረጋግጣል። በአብዛኛው በዱባይ የሪል ስቴት ገበያ ላይ የሚሳተፉ ባለሃብቶች በአገራቸው የሰላም ስጋት ያለባቸው ዜጎች መሆናቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

ለአብነት ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ብዙ ዜጎቿ የዱባይን ሪል ስቴት ገበያ አጥለቅልቀውታል። በዚህም ምክንያት በፈረንጆቹ 2023 መጀመሪያ አካባቢ የዱባይን ሪል ስቴት በመግዛት ሩሲያውያን ከመላው ዓለም ቀዳሚዎች ነበሩ።

እንደ ሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የተጋነነ ባይሆንም የአፍሪካ ኢንቨስተሮችም በዱባይ ሪል ስቴት ገበያ ላይ ንቁ ተሳታፊ ናቸው። ኢትዮጵያዊው አህመድ ዝናብ ላለፉት ሦስት ዓመታት በዱባይ የሪል ስቴት ገበያ በአሻሻጭነት ቆይቷል።

አህመድ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከመላው ዓለም የሚመጡ ቤት ፈላጊዎችን ከሻጮች ጋር ያገናኛል። እስካሁን ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን ‘ራምዚ’ ብሎ ባቋቋመው ድርጅት በኩል ቤት መግዛታቸውንም ይናገራል።

በባሕረ ሰላጤዋ ባለጸጋ አገር ያሉ አመቺ ሁኔታዎችን በመጠቀም በርከታ ኢትዮጵያውያንም ቤቶችን ዱባይ ውስጥ ይገዛሉ። እንደ አህመድ ገለጻ ከሆነ በዱባይ ኢትዮጵያውያን ሪል ስቴት ቤት ገዥዎች ከአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነጻጸሩ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣሉ።

እነዚህ ኢትዮጵያውያን ብዙዎቹ ቤት የሚገዙት ለመኖሪያ አይደለም። በአንጻሩ “የገዙትን ቤት በማከራየት ገንዘብ ለማግኘት ነው” ይላል አህመድ። ደንበኞቹም በአብዛኛው ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ የሚመጡ ናቸው።

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ የሪል ስቴት አሻሻጭ ዳግማዊ ኤፍሬም እንደሚለው ደግሞ “የአገሪቱ [የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ] መንግሥት የሚሰጠው ማበረታቻ እና የሪል ስቴት አልሚዎች በተራዘመ ክፍያ ቤቶችን ያለ ወለድ መሸጣቸው” የዱባይ ሪል ስቴትን ተመራጭ ያደረጉት ምክንያቶች ናቸው።

በዚህም ገዥዎች ከመላው ዓለም ወደ ዱባይ ይጎርፋሉ። “ዱባይ ላይ የሪል ስቴት ቤት ከሚገዙ ባለሃብቶች መካከል 85% የሚሆኑት የሌላ አገር ዜጎች ናቸው” የሚለው ዳግማዊ፣ “የኪራይ እና የቤት ሽያጭ ዋጋ በየዕለቱ ስለሚጨምር” ባለሃብቶች እንደአዋጭ ኢንቨስትመንት ቆጥረው ይሳተፋሉ ይላል።

ሰዎች ዱባይ ላይ ቤት በመግዛታቸው የሚያገኟቸው ሌሎች ማበረታቻዎችም ተጨማሪ የኢንቨስትመንት መሳቢያ መንገዶች ናቸው።

ዱባይ ላይ ቤት የገዛ ባለሃብት በአገሪቱ ተጨማሪ ቢዝነስ ለመጀመር፣ የባንክ ሂሳቦችን በመክፈት የውጭ ምንዛሬ ለማጠራቀም እና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የሚያስችሉ ማበረታቻዎችን ያገኛል።

እነዚህ ማበረታቻዎች ደግሞ በተለይ የውጭ ምንዛሬ በቀላሉ ከማይገኝባቸው እንደ ኢትዮጵያ ካሉ አገራት የሚመጡ ባለሃብቶች ልዩ ትኩረት ይሰጡታል።

ቢቢሲ ዱባይ ውስጥ በቅርብ ጊዜ ቤት የገዙ ኢትዮጵያውያንን በማግኘት ለማናገር ቢሞከርም ባልጠቀሱት ምክንያት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋለ።

ነገረ ግን የሪል ስቴት አሻሻጮች እንደሚሉት ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው በኢትዮጵያ፣ በአሜሪካ እና በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቤቶችን የገዙ ሲሆን፣ ለመግዛትም በሂደት ላይ የሚገኙ እንዳሉ ቢቢሲ ተረድቷል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥት የዘረጋው የተሳለጠ እና ያጠረ የቢሮክራሲ ሥርዓትም ለሪል ስቴት ኢንቨስትመንቱ መፋጠን አስተዋጽዖ እንዳለው ብሩክ ይናገራል።

“ሰዎች ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን ሳያባክኑ ባሉበት ቦታ ሆነው ሁሉንም ሂደት በመጨረስ በአጠረ ጊዜ ቤታቸውን መረከብ የሚችሉበትን መንገድ መንግሥት ዘርግቷል።”

ይህም መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች ሳይሰላቹ እና በጊዜ ሂደት ሃሳባቸውን ሳይቀይሩ ቤት በመግዛት ውሳኔያቸው ላይ እንዲጸኑ ያደርጋል።

ዱባይ ለናጠጡ ከበርቴዎች ቅንጡ መኖሪያ ቤቶችን በማቅረብም ከዓለም ቀዳሚ እየሆነች ነው። ‘ጁሜራህ’ ተብሎ በሚጠራው የዱባይ አካባቢ በሰው ሰራሽ ሐይቅ ላይ በዘንባባ ቅርጽ የሚገነቡት ትልልቅ የሪል ስቴት መንደሮች በዋጋቸው ዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌላቸው ቅንጡ ቤቶች ሆነዋል።

ጁሜራህን ጨምሮ ዱባይ የምታቀርባቸው ቅንጡ ቤቶች ባለፈው ዓመት 10 ሚሊዮን ዶላር እና ከዚያ በላይ በመሸጥ ዱባይን ከቀሪው ዓለም ቀዳሚ አድርገዋታል።

በባለፈው ዓመት ሽያጭ በዱባይ 431 ቤቶች እያንዳንዳቸው 10 ሚሊዮን ዶላር [ከ560 ሚሊዮን ብር በላይ] እና ከዚያ በላይ በሆነ ዋጋ ተሽጠዋል። በዚህ ዋጋ ይህንን ያህል ቤቶች በመሸጥ ዱባይን የሚስተካከል አልተገኘም።

በዚሁ ጁሜራህ ተብሎ በሚጠራው ሰው ሰራሽ ደሴት ላይ ቅንጡ ቪላዎች ባለፈው መጋቢት ወር በ76 እና 82 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መሸጣቸውን የዘ ኢኮኖሚስት ዘገባ አስነብቧል።

በቅርቡ ደግሞ በተመሳሳይ ሥፍራ 114 ሚሊዮን ዶላር [ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ] የተሸጠ ቪላ የሪል ስቴት ንግድ ተዋንያንን አጃኢብ አሰኝቷል።

በጁሜራህ አንድ ግለሰብ ባዶ ቦታ ብቻ በ34 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መግዛቱም እንዲሁ አነጋጋሪ ሆኗል።

የዱባይ ሪል ስቴት ገበያ በዚህ ዓመት የ15 በመቶ ጭማሪ ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አል አረቢያ የበይነ መረብ ሚዲያ አስነብቧል።

ባለንበት የፈረንጆቹ 2024 የመጀመሪያው ሦስት ወራት ብቻ ዱባይ ውስጥ በሪል ስቴት ዘርፍ ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ግብይት ተደርጓል።

አሁን እስካለንበት ወር ጊዜ ድረስ ደግሞ የሪል ስቴት ግብይቱ ከ27 ቢሊዮን ዶላር ሊበልጥ እንደሚችል ባለሙያዎችን አነጋግሮ ድረ ገጹ አትቷል።

የሪል ስቴት ገበያው በዋጋ እንዲንር እና የቤት ፈላጊዎች ቁጥር እንዲጨምር ያደረገው የአገሪቱ መንግሥት ያስቀመጠው የሕዝብ ቁጥርን መጨመር ዕቅድ እንደሆነ ይታመናል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥት በ2040 የዱባይን የሕዝብ ቁጥር በ2022 ከነበረበት 3.7 ሚሊዮን ወደ 7.8 ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ ግብ አስቀምጧል።

ይህንን ተከትሎ የሚከሰተውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት ቢያንስ እስከ 2028 ድረስ በዓመት 70 ሺህ ቤቶችን መገንባት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።