ትራምፕ ግሪንላንድን 'ለመጠቅለል' ይፈልጋሉ፡ይህ ጉዳይ በምን መልኩ ሊቋጭ ይችላል?

ባለፉት ሳምንታት ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአርክቲክ ውቅያኖስ የሚገኘውን እና በዓለማችን ትልቁን የግሪንላንድ ደሴት 'ለመጠቅለል' ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል ።

በመጀመሪያ የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው በ2019 ግሪንላንድን የመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ጠቆሙ። ከቀናት በፊት ደግሞ ደሴቲቱን ኢኮኖሚያዊም ሆነ ወታደራዊ ኃይልን ተጠቅመው መቆጣጠርን ከዕቅዳቸው ውጪ እንደማያደርጉ አሳውቀዋል።

የዴንማርክ እና የአውሮፓ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ግሪንላንድ ለሽያጭ አትቀርብም፤ የግዛት አንድነቷም መጠበቅ አለበት ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ሰማኒያ በመቶ የሚሆነው ክፍሏ በበረዶ የተሸፈነው ነገር ግን ከፍተኛ ጥቅም ላይ ያልዋለ የማዕድን ሃብት ባለት ደሴት ላይ ሁለት የኔቶ አጋሮች የፈጠሩት ይህ ያልተለመደ ውዝግብ እንዴት ሊጠናቀቅ ይችላል?

ይህ ፍላጎት ለ300 ዓመታት ያህል በዴንማርክ ቁጥጥር ሥር ባለችው እና 56 ሺህ ሕዝብ በሚኖርባት ግሪንላንድ የራስን በራስ የማስተዳደር ፍላጎት ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል?

የግሪንላንድ የወደፊት ዕታ ፈንታን በተመለከተ አራት ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን እንደሚከተለው እንመለከታለን።

ትራምፕ ፍላጎት ያጡና ሁሉም ነገር ባለበት ይቀጥላል

ሩሲያ እና ቻይና በቀጠናው ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ያላቸውን ስጋት ለማረቅ ዴንማርክ የግሪንላንድን ፀጥታ እንድታጠናክር ለማድረግ ትራምፕ የወሰዱት እርምጃ ብቻ ነው የሚል ግምት አለ።

ዴንማርክ ባለፈው ወር ለአርክቲክ ደሴቷ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ በጀት ይፋ አድርጋለች። ገንዘቡ ከትራምፕ ንግግር በፊት የተዘጋጀ ቢሆንም ይፋ የሆነው ግን ከንግግራቸው በኋላ ነው። የዴንማርክ መከላከያ ሚኒስትር ድጋፉን "የብረት መዝግያ" ነው ሲሉ ገልጸውታል።

"ትራምፕ ከተናገሩት ዋናው ነገር ዴንማርክ በአርክቲክ ውቅያኖስ ላይ ግዴታዋን መወጣት አለባት ወይም ደግሞ አሜሪካ ኃላፊነቱን እንድትወስድ መፍቀድ ይኖርባታል" የሚል ነው ሲሉ 'ፖሊቲከን' የተባለው ጋዜጣ ዋና የፖለቲካ ጉዳዮች ዘጋቢዋ ኤልዛቤት ስቫን ገልጸዋል።

በሮያል ዴንማርክ መከላከያ ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርክ ጃኮብሰን ደግሞ ትራምፕ "ወደ ሥልጣን ከመግባታቸው በፊት ጉልበታቸውን ማሳያ" እንደሆነ ያምናሉ።

ግሪንላንድ ደግሞ አጋጣሚውን ተጠቅማ ለነጻነት ለሚያርገውን ጉዞ አስፈላጊ የሆነውን ዓለም አቀፍ ሥልጣንን ለማግኘት እየተጠቀመችበት ነው ብለዋል።

ትራምፕ በግሪንላንድ ዙሪያ ያላቸው ፍላጎት እንደሚቀየር ፕሮፌሰር ጃኮብሰን ቢያስቡም፤ ጉዳዩ መነጋገሪያ እንዲሆን አድርገዋል ይላሉ።

የግሪንላንድ ነፃነት ጉዳይ ለበርካታ ዓመታት አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል። አንዳንዶች ክርክሩ ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ ሊሄድ ይችላል ይላሉ።

"ባለፉት ጥቂት ቀናት የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በአስተያየቶቻቸው ረጋ ያሉ መሆናቸውን አስተውያለሁ። ማለትም ነፃነት እንፈልጋለን ግን በረዥም ጊዜ የሚሆን ነው ብለዋል" ይላሉ ስቫን።

ግሪንላንድ ነፃነቷን ታገኝና ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ትፈልጋለች

በግሪንላንድ ድምጽ ከተሰጠ ነፃነት እንደምትቀዳጅ እና ይህንንም ዴንማርክ ተቀብላ ታጸድቀዋለች የሚለው የብዙዎች ሃሳብ ነው።

ግሪንላንድ ለጤና እና ለማኅበራዊ ድጋፍ ከዴንማርክ የሚያገኙትን ድጎማ ለማቆየት ዋስትና እስካልተሰጣቸው ድረስ ግሪንላንዳውያን ለነፃነታቸው ድምጽ መስጠታቸው አይቀርም።

"የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ከጠየቁ የግሪንላንድ ኢኮኖሚ እና የደኅንነት ሥርዓትን እንዴት ማዳን እንደሚቻል አሳማኝ ማስረጃ ያስፈልጋቸዋል" ሲሉ የዴንማርክ ዓለም አቀፍ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪው ኡልሪክ ጋድ ለቢቢሲ ተናግሯል።

አንደኛው ቀጣዩ እርምጃ አሜሪካ በአሁኑ ጊዜ የፓስፊክ ግዛቶች ከሆኑት ከማርሻል ደሴቶች፣ ከማይክሮኔዥያ እና ፓላው ጋር ያላት ዓይነትን ነፃ ማኅበር ማቋቋም ነው።

ዴንማርክ ከዚህ ቀደም ለግሪንላንድም ሆነ ለፋሮ ደሴቶች ይህንን ማኅበር ተቃውማ ነበር።

እንደ ዶ/ር ጋድ ገለጻ ግን የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜት ፍሬድሪክሰን ይህንን ሙሉ በሙሉ አይቃወሙትም።

የቅኝ ግዛት ኃላፊነትን በመቀበል "ዴንማርክ ስለግሪንላንድ ታሪካዊ ዳራ ያላት ዕውቀት ከ20 ዓመታት በፊት ከነበረው የተሻለ ነው" ብለዋል።

የቅርብ ጊዜ ውይይቶች "ምንም እንኳን የላላ ቢሆንም ዴንማርክን በአርክቲክ ውስጥ ማቆየት፤ ከግሪንላንድ ጋር አንድ ዓይነት ግንኙነት እንዲኖር ማድረግን [ፍሬዴሪክሰን] እንዲቀበሉ ሊያሳምን ይችላል" ሲሉ አክለዋል።

ግሪንላንድ ዴንማርክን ማስወገድ ብትችልም በቅርብ ዓመታት ውስጥ የዩናይትድ ስቴትስን ተጽዕኖ ማስወገድ እንደማትችል ግልጽ ሆኗል።

አሜሪካኖች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ደሴቲቱን ከተቆጣጠሩ በኋላ ለቅቀው ወጥተው ካለማወቃቸውም በላይ ለደኅንነታቸው አስፈላጊ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።

በአውሮፓውያኑ 1951 የተደረገው ስምምነት የዴንማርክ የደሴቲቱን መሠረታዊ ሉዓላዊነት ብትቆጣጠርም ግን ለአሜሪካ የፈለገችውን ሁሉ ሰጥታለች።

የግሪንላንድ ባለሥልጣናት የዋሽንግተንን ሚና በተመለከተ ካለፉት ሁለት የአሜሪካ አስተዳደሮች ጋር ግንኙነት ማድረጋቸውን ዶ/ር ጋድ ተናግረዋል።

"አሁን አሜሪካ መቼም እንደማትወጣ ያውቃሉ።"

ትራምፕ የኢኮኖሚያዊ ጫናውን ከፍ ያደርጋሉ

የትራምፕ የኢኮኖሚ ጫና ለዴንማርክ ትልቁ ስጋት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ። ዩናይትድ ስቴትስ በዴንማርክ ወይም በአውሮፓ ኅብረት ምርቶች ላይ ታሪፍ በከፍተኛ ሁኔታ ከጨመረች ዴንማርክ በግሪንላንድ ላይ አንድ ዓይነት ስምምነት እንድታደርግ ትገደዳለች።

ፕሮፌሰር ጃኮብሰን እንዳሉት ከሆነ የዴንማርክ መንግሥታት በአርክቲክ ደሴቷ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በሌላም አቅጣጫ ሊመጣ ይችላል በሚል እየተዘጋጁ ነበር።

ትራምፕ በሁሉም ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ እያስፈራሩ ሲሆን፣ ይህም የአውሮፓን ዕድገት በከፍተኛ ሁኔታ ሊያስተጓጉል ይችላል።

አንዳንድ የዴንማርክ እና የሌሎች የአውሮፓ ኩባንያዎች በአሜሪካ ማምረቻዎቻቸውን ለማቋቋም እያሰቡ ነው።

ታሪፍ ለመጨመር ከሚያግዙ አማራጮች አንዱ በአውሮፓውያኑ 1977 የወጣውን የዓለም አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ የኢኮኖሚ ኃይል ሕግን (አይኢኢፒኤ) ማንሳት መሆኑን የፒልስበሪ ቤንጃሚን ኮት ማርኬት ዋች ለተባለው ድረ ገጽ አመልክቷል።

በዚህ ውሳኔ ሊነኩ ከሚችሉት ዋና ዋና የዴንማርክ ኢንዱስትሪዎች አንዱ የመድኃኒት አምራቹ ዘርፍ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ እንደ የጆሮ ማዳመጫ መርጃ፣ ኢንሱሊን እና በኖቮ ኖርዲስክ የሚመረተውን ኦዜምፒክ የተባለውን የስኳር በሽታ መድኃኒት ከዴንማርክ ታገኛለች።

ትራምፕ ግሪንላንድን ሊወሩ ይችላሉ

"የኒውክሌር አማራጩ" ከእውነት የራቀ ቢመስልም፣ ግን ትራምፕ ወታደራዊ እርምጃዎችን ማስወገድ አለመቻላቸው ሊታሰብበት ይገባል።

በመሠረቱ በግሪንላንድ ውስጥ የጦር ሰፈር እና ብዙ ሠራዊት ስላላት ዩናይትድ ስቴትስ ደሴቷን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ አይሆንባትም።

ፕሮፌሰር ጃኮብሰን "አሜሪካ ቀድሞውንም ቢሆን ትቆጣጠራታለች" ከማለት ባለፈ የትራምፕን ንግግር ጥልቀት የጎደለው የሚመስል እና ዓላማው ግልጽ ያልሆነ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዋሺንግተን ማንኛውንም ወታደራዊ ኃይል ከተጠቀመች ዓለም አቀፍ ክስተት ይፈጥራል።

"ግሪንላንድን ከወረሩ ኔቶን ይወርራሉ። ስለዚህ እዚህ ጋር ሁሉም ነገር ይቆማል። አንቀጽ 5 ተግባራዊ ይደረጋል። በዚህም የኔቶ አባል አገር ሌላ የኔቶ አባል አገርን ከወረረ ኔቶ አይኖርም።"

የትራምፕ ሀሳብ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ስለታይዋን ሲናገሩ ወይም የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን ስለ ዩክሬን ሲናገሩ ያለውን ይመስላል ብለዋል ዶ/ር ጋድ።

"ይህን መሬት መውሰዳችን ሕጋዊ ነው እያለ ነው። በቁም ነገር ከወሰድነው ግን ይህ ለመላው የምዕራቡ ዓለም ኅብረት መጥፎ ምልክት ነው" ብለዋል።