የአሜሪካ ድጋፍ በመቋረጡ ሚሊዮኖች በኤችአይቪ ይያዛሉ ተብሎ ተሰግቷል

ጉጉ* ጆሃንስበርግ መሃል ከተማ ከሚገኘው እና በዩኤስኤአይዲ የገንዘብ ድጋፍ ከሚደረግለት ክሊኒክ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ትወስድ ነበር።

ነገር ግን ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ የምትሰጠውን ድጋፍ ማቋረጣቸውን ጥር ወር ላይ ይፋ ሲያደርጉ፣ እሷ እና ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ደቡብ አፍሪካውያን በድንገት የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው አጣብቂኝ ውስጥ ወደቀ።

ጉጉ ዕድለኛ ነበረች። መድኃኒት የምትወስድበት ክሊኒክ ከመዘጋቱ በፊት አሳውቋታል። "መድኃኒቶቻቸውን በጅምላ ማግኘት ከቻሉት ሰዎች አንዱ ነበርኩ። ብዙ ጊዜ የሦስት ወር መድኃኒቴን ነበር የምወስደው። ክሊኒኩ ከመዘጋቱ በፊት ግን የዘጠኝ ወር መድኃኒት ሰጡኝ።"

መስከረም ወር ላይ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶቿን ትጨርሳለች። እና ተጨማሪ የምታገኝ ከሆነ ለመጠየቅ አካባቢዋ ወደ ሚገኘው የሕዝብ ሆስፒታል ለመሄድ አቅዳለች።

ከዚህ በፊት በወሲብ ንግድ ላይ ተሰማርታ የነበረችው የ54 ዓመቷ ጉጉ፣ ኤችኤችአይቪ በደሟ መኖሩን ያወቀችው ሥራውን ካቆመች በኋላ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት በመውሰድ ላይ ነች።

በአሁኑ ጊዜ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ የፕሮጀክት አስተባባሪ ሆና ትሠራለች።

"ነፍሰ ጡር ሴቶች ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ይወስዳሉ፤ ይህ የሚወልዱት ልጅ በቫይረሱ እንዳይያዝ ይረዳቸዋል፤ እናቶች መድኃኒታቸውን በአግባቡ እየወሰዱ መሆኑን ለማረጋገጥ የቤት ለቤት ጉብኝት እናደርጋለን። ለወርሃዊ ምርመራ በሚሄዱበት ጊዜም ልጆቻቸውን እንንከባከብላቸዋል።"

በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ በርካታ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶቻቸውን የሚያገኙት በአሜሪካ መንግሥት ከሚደገፉ የግል ክሊኒኮች ነው።

ነገር ግን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ተመልሰው ከመጡ በኋላ አብዛኛውን የውጭ ዕርዳታን በማቋረጣቸው ብዙዎቹ ተቋማት ተዘግተዋል።

ሐሙስ ዕለት ይፋ የሆነ አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው ኤችአይቪ/ኤድስን በመዋጋት ላይ ኃላፊነት ያለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሜሪካን ብቻ ለይቶ ባይጠቅስም በርካታ ለጋሽ አገራት ከፍተኛ ቅነሳ ማድረጋቸው በዓለም ዙሪያ ድንጋጤን ፈጥሯል።

እንዲሁም በሽታውን በመዋጋት ረገድ የተገኘውን "አስደናቂ መሻሻል" የመቀልበስ አደጋ እንዳለው አሳስቧል።

ዩኤንኤድስ "ከ2010 ጀምሮ አዳዲስ የኤችአይቪ ኢንፌክሽን ቁጥር በ40 በመቶ ቀንሷል። ከ2000 ጀምሮ ደግሞ 4.4 ሚሊዮን ሕጻናት በኤችአይቪ ቫይረስ እንዳይያዙ መከላከል ተችሏል። ከ26 ሚሊዮን በላይ ሕይወት ማትረፍ ተችሏል" ብሏል።

ዓለም እርምጃ ካልወሰደ ግን በ2029 ተጨማሪ 6 ሚሊዮን አዳዲስ የኤችአይቪ ኢንፌክሽኖች እና አራት ሚሊዮን ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ሊገኝ እንደሚችል እና ከኤድስ ጋር የተገናኙ ሞቶች ሊኖሩ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ ከሆነ አሜሪካ ለኤችአይቪ የምታደርገውን ድጋፍ የምታቋርጠው በታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም ስኬታማ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ እርምጃ ተብሎ በሚታወቀው ዘርፍ የተገኙ አንዳንድ ግኝቶችን ሊቀይር ይችላል።

መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የላንሴት የሕክምና ጆርናል ላይ ባለፈው ወር ሳይንቲስቶች ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የዩኤስኤአይዲ የገንዘብ ድጋፍ የኤድስ ሞትን በ65 በመቶ ወይም በ25.5 ሚሊየን ቀንሶታል።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዋከር ቡሽ እአአ በ2003 ኤችአይቪ/ኤድስን ለመዋጋት ትልቅ ፕሮግራም ሲያስተዋውቁ ለአሜሪካ "ስልታዊ እና ሞራላዊ ጥቅም" እንደሚያገለግል ተናግረው ነበር።

በዩናይትድ ስቴትስ 43ኛ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋከር ቡሽ የተጀመረው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የኤድስ አጣዳፊ ድጋፍ መርሃ ግብር በምኅጻረ ቃሉ ፔፕፋር፣ በዓለም አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከል ላይ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ አፍስሷል።

ይህም በዓለም ላይ አንድን በሽታ ለመከላከል በአንድ አገር ወጪ የተደረገ ትልቁ ገንዘብ ነው።

በደቡብ አፍሪካ ወደ 7.7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሲሆን፣ ይህም በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር መሆኑን ዩኤንኤድስ ገልጿል።

ከእነዚህ መካከል 5.9 ሚሊዮን ያህሉ የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና ያገኙ ሲሆን፣ ይህም ከ2010 ጀምሮ በኤድስ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች በ66 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የፔፕፋር የገንዘብ ድጋፍ ለኤችአይቪ/ኤድስ መርሃ ግብሩ 17 በመቶ ያህል አስተዋፅዖ አድርጓል ብሏል።

ገንዘቡ ለታካሚዎች በቀላሉ ሕክምና ለማግኘት እንዲያስችላቸው በሚል የተንቀሳቃሽ ክሊኒኮችን ከማቋቋም ጀምሮ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ይውል ነበር።

የትራምፕ አስተዳደር የሚያደርገውን ድጋፍ መቀነሱ የኢንፌክሽኑ መጠን እንደገና ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

የጆሃንስበርግ ዊትስ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቻንስለር ፕሮፌሰር ሊን ሞሪስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በኤችአይቪ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመርን፣ የቲቢ ሕሙማንን እና በሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የተጠቁ ሰዎችን ማየት የምንጀምር ይመስለኛል" ብለዋል።

"እናም በመሠረቱ እውነተኛ የስኬት ታሪክ የነበረውን ተገላቢጦሽ ማየት እንጀምራለን። ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን ከአሁኑ ለመቅረፍ እየሠራን ነው።"

ጉጉ የኤች አይቪ ሕክምና የሕይወት እና የሞት ጉዳይ እንደሆነ ትናገራለች። በተለይ በወሲብ ንግድ ላይ ለተሰማሩ እና የበለጠ ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሕክምናው አጠያያቂ አይደለም።

የእርዳታው መቀነስ የኤችአይቪ ክትባት እና የኤድስ መድኃኒት ለማግኘት በሚደረገው ምርምር ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል።

ደቡብ አፍሪካ በኤችአይቪ ላይ በሚደረጉ ዓለም አቀፍ ምርምሮች ቀዳሚ ከሆኑት አገራት መካከል አንዷ ናት።

ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱት እና በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ አብዛኛዎቹ መድኃኒቶች በደቡብ አፍሪካ ተፈትሸዋል።

ይህ ከቫይረሱ ነጻ የሆኑ ሰዎች እንዳይያዙ የሚከላከለው ፕሬፕን (pre-exposure prophylaxis) ያካትታል።

ሌላው በዚህ ዓመት የተሠራጨው ውጤታማ የሆነው የበሽታው መከላከያ መድኃኒት ሌናካፓቪር (Lenacapavir) ነው።

ይህ መድኃኒት በዓመት ሁለት ጊዜ የሚወሰድ ሲሆን፣ ከኤችአይቪ የሚከላከል ክትባት ሲሆን በደቡብ አፍሪካም ተሞክሯል።

በዊትስ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ካምፓስ ውስጥ በሚገኝ ቤተ ሙከራ ውስጥ፣ ጥቂት የሳይንስ ሊቃውንት ቡድን አሁንም ለኤችአይቪ ክትባት ለማግኘት ምርምር እያካሄዱ ነው።

በስምንት የአፍሪካ አገራት የቫይረሱን ክትባት ለማዘጋጀት የሚሠራው የብሪሊየንት ኮንሰርቲየም ቡድን አካል ናቸው።

በዊትስ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አብዱላህ ኢሊ "ያ ምን ያህል እንደሚሠራ ለማየት የክትባት ሙከራ እያዘጋጀን ነበር፤ ከዚያም በሰዎች ላይ እንሞክራለን" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ዕቅዱ በአፍሪካውያን ምሁራን የተደረጉ ምርምሮችን በአፍሪካ ውስጥ ለመሞከር ነው። ምክንያቱም ይህ ምርምር ማኅበረሰባችንን እና መላውን የሰው ልጅ የሚጠቅም እንዲሆን ስለምንፈልግ ነው።"

ነገር ግን የአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ሥራቸውን ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል።

"አቁሙ የሚለው ትዕዛዝ ሲመጣ ሁሉንም ነገር ማቆም ነበረብን። ሥራችንን እንድንቀጥል አንዳንዶቻችን ብቻ ነን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት የቻልነው። ለወራት ወደኋላ እንድንመለስ አድርጎናል፤ ምናልባትም አንድ ዓመትም ሊሆን ይችላል" ብለዋል ፕሮፌሰር ኢሊ።

ቤተ ሙከራው በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ክሊኒክ ውስጥ ሙከራ ለማካሄድ ታቅደው የነበሩ ምርምሮችን ለማካሄድ የገንዘብ ድጋፍ የለውም።

"ይህ ለደቡብ አፍሪካ እና ለአህጉሪቱ በጣም ትልቅ ኪሳራ ነው፤ ይህ ማለት ከአፍሪካ የሚወጣ ማንኛውም ምርምር በአውሮፓ ወይም በአሜሪካ መሞከር አለበት ማለት ነው" ብለዋል ፕሮፌሰር ኤሊ።

የደቡብ አፍሪካ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር አሮን ሞቶአሌዲ ለምርምር የሚሆን አንዳንድ አማራጭ የገንዘብ ድጋፍ መገኘቱን ረቡዕ ዕለት አስታውቀዋል።

የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እንዲሁም ዌልኮም ትረስት እያንዳንዳቸው 1 ሚሊየን ራንድ (የደቡብ አፍሪካ ገንዘብ) ወዲያውኑ ለመለገስ የተስማሙ ሲሆን፣ መንግሥት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ 400 ሚሊዮን ራንድ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ይህም አጠቃላይ ድጋፉን ወደ 600 ሚሊዮን ራንድ ያደርሰዋል፤ ይህም በተመራማሪዎች ከተጠየቀው 4.6 ቢሊዮን ራንድ በታች ነው።

ጉጉ በእርጅና ዘመኗ የኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት ይገኛል የሚል ተስፋ ነበራት፤ አሁን ግን ያ ተስፋዋ ጥሏት ጠፍቷል።

"የዘጠኝ ዓመት ልጄን እጠብቃለሁ፤ እሱን ለመንከባከብ የምችለውን ያህል መኖር እፈልጋለሁ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

"ይህ የአሁን ጊዜ ችግር ብቻ አይደለም። የሚቀጥለው ትውልድ ሴቶች እና ወጣቶችን እንዴት እንደሚጎዳ ማሰብ አለብን።"

____

*ስሟን ለደኅንነቷ ስንል ቀይረነዋል።