የፕሬዝዳንት ሙሴቪኒን ሥልጣን እና የቤተሰባቸውን የበላይነት የሚያስጠብቀው የኡጋንዳ ልዩ ኃይል

የኡጋንዳ ልዩ ኃይል ዕዝ አባላት ግዙፍ መሣሪያ ይዘው፣ የፊት ጭምብል አጥልቀው በአገሪቱ ጎዳናዎች ላይ ይዘዋወራሉ።
ይህ ዕዝ የኡጋንዳ ልዩ ወታደራዊ ክንፍ ነው። የ81 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒን እና ቤተሰቦቻቸውን መጠበቅ ዋነኛ ተልዕኳቸው እንደሆነ ይታመናል።
በአውሮፓውያኑ 1986 ሥልጣን የያዙት ሙሴቪኒ አሁንም ኡጋንዳን መምራት ቀጥለዋል። አራት ጊዜ ምርጫ አሸንፈዋል። ምርጫዎቹ ተጭበርብረዋል የሚሉ ክሶች በተደጋጋሚ ይሰማሉ።
ኡጋንዳ ነፃነቷን ያገኘችው በአውሮፓውያኑ 1962 ነው። የአገሪቱ የመሪነት ሥልጣን በአማጽያን እና በወታደሮች እጅ ቆይቷል።
ሙሴቪኒ በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመትም በመንበራቸው ላይ ለመቆየት በምርጫ እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል። የአገሪቱ ልዩ ኃይሎች ዕዝ (Special Forces Command ወይም SFC) ተቃዋሚዎች የምርጫ ቅስቀሳ እንዳያደርጉ ሊያግድ እንደሚችል ተሰግቷል።
የኡጋንዳ ልዩ ኃይል ዕዝ በ2021 የምርጫ ቅስቀሳ እንዳይከናወን አስተጓጉሎ ነበር።
ዕዙ ለዓመታት የተመራው በሙሴቪኒ ልጅ ጄነራል ሙሆዚ ካኒሩግባ ነው።
ወታደራዊ ኃይሉ የመንግሥት ተቺዎችን በማፈን፣ተቃዋሚዎች እና የመብት ተሟጋቾችን በመግደል ጭምር ይከሰሳል። ነገር ግን ልዩ ዕዙ ክሱን ያስተባብላል።
አንድ የቢቢሲ ወታደራዊ ምንጭ ዕዙ "በመከላከያው ውስጥ ያለ ስውር ሠራዊት ነው። ትዕዛዝ የሚቀበለውም ከፕሬዝዳንቱ እና ከልጃቸው ብቻ ነው። ሠራዊቱ ገናና እየሆነ መምጣቱ ከፍተኛ ጄነራሎችን እያስቆጣ ነው" ብለዋል።
የ51 ዓመቱ የሙሴቪኒ ልጅ ጄነራል ሙሆዚ ካኒሩግባ የአገሪቱ ጦር አዛዥ ነው። እንደ አባቱ ፕሬዝዳንት እንደሚሆን ይናገራል።
ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ ጄነራሎችን 'ቂላቂል' በማለት መወረፉ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር።
ንግግሩ ወታደሮችን እና ፖለቲከኞችን ያስቀየመ ቢሆንም የኡጋንዳ መንግሥት "የማኅበራዊ ሚዲያ ስላቅ" ነው ሲል ነገሩን ለማጣጣል ሞክሯል።
የፕሬዝዳንቱ ልጅ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እሰጣ ገባ ውስጥ በመግባት ይታወቃል።
ከዓመታት በፊት ኬንያን እወራለሁ ማለቱ አነጋጋሪ ሆኖ የነበረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የውስጥ ጉዳዮች ላይ አስተያየት በመዘንዘር ውዝግብ በመፍጠር ይታወቃል።
ልዩ ወታደራዊ ዕዙ ጠንካራ እየሆነ ከመምጣቱ የተነሳ የአገሪቱን መከላከያ ሠራዊትን መገዳደር ጀምሯል።
የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሙሴቪኒ ወደ ሥልጣን እንዲወጡ የሽምቅ ውጊያ በማድረግ ይታወቃል።
ልዩ ወታደራዊ ዕዙ አንድ ቀን ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር ይጋጫል ብለው የፖለቲካ ተንታኞች ይሰጋሉ።
በሱዳን ውስጥ ያሉት ሁለት ተፎካካሪ ሠራዊቶች አገሪቱን ወደ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ካስገቧት ዓመታት ተቆጥረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኡጋንዳ ልዩ ዕዝ የተመሠረተው ሙሴቪኒ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ነበር።
በካናዳ ዮርክ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ትውልደ ኡጋንዳዊ ዶ/ር ጄራልድ ባርቤ "ዕዙ በኡጋንዳ ጠንካራው ኃይል ነው። ከፍተኛ ሁኔታ የሠለጠነ እና ከፍተኛ ገንዘብም የወጣበት ነው።"
"ታማኝነትን የመሰለ ነገር የለም" የሚል መሪ ቃልም አለው።
ቢቢሲ የኡጋንዳ መከላከያ ሠራዊት እና የኡጋንዳ ልዩ ኃይል ዕዝ አስተያየት እንዲሰጡ ቢጠይቅም ፈቃደኛ አልሆኑም።
ሙሴቪኒ ዕዙ የተቋቋመው ለኡጋንዳውያን ነው ብለው ተናግረዋል። ለኡጋንዳ በጎ የሚመኙ ዕዙን እንደሚደግፉም ገልጸዋል።
ተቃዋሚዎች ግን ከዚህ የተለየ ዕይታ አላቸው።
ሙሴቪኒ ኡጋንዳን የቤተሰባቸው ንብረት አድርገዋታል ተብለው ይከሰሳሉ። ባለቤታቸው ጃኔት የትምህርት ሚኒስትር ናቸው።
የሙሴቪኒ የልጅ ልጅ በመከላከያ ሠራዊቱ ተመልምሏል። የቤተሰቡን የሥልጣን መንበር እንደሚረከብም ይጠበቃል።
የፕሬዝዳንቱ ልጅ የልዩ ኃይል ዕዙን ከአንድም ሁለቴ መርቷል። ይህ የልዩ ኃይል ዕዝ ከ10,000 በላይ አባላት እንዳሉት ይታመናል። መደበኛው የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት 40,000 አባላት አሉት።
የቀድሞው ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣን እንዳሉት፣ ዕዙ ልዩ ሥልጠና ይሰጠዋል። ከመደበኛው ሠራዊት የተለየ ዘመናዊ መሣሪያም ታጥቀዋል።
የፕሬዝዳንቱ ልጅ ጄነራል ሙሆዚ ከዕዙ ዋና መቀመጫ ሆኖ ትዕዛዝ ያስተላልፋል። ሕንጻው በአባቱ ስም የተሰየመ ነው። ከኢንቴቤ 34 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
በድረ ገጹ ላይ ሠራዊቱ ያለው መሣሪያ ዘመናዊ እንደሆነ ተጠቅሷል። ዋናውን አውሮፕላን ማረፊያ እና የነዳጅ ማምረቻዎችን ይጠብቃል።
ከወራት በፊት ወደ ጎረቤት ኬንያ ድንበር ዘልቀው በመግባት የፕሬዝዳንት ሜሴቪኒ ተቀናቃኝ የሆኑትን ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ኪዛ ቤሲጄን ይዘው ወስደዋል።
ተቃዋሚ ፖለቲከኛው በአንድ ወቅት የሙሴቪኒ የግል ሐኪም ነበሩ። ከኬንያ ከተወሰዱ በኋላ በአገር ክህደት ተከሰዋል።
የመከላከያው ዐቃቤ ሕግ የኡጋንዳ ፀጥታ ኃይሎች ፖለቲከኛውን እንደያዙ ጠቁመዋል።
ዶ/ር ጄራልድ እንደሚሉት፤ ዕዙ የሙሴቪኒ አስተዳደር ዘላቂነትን ያረጋግጣል። ከተቃዋሚዎች ከሚነሳው ፉክክር ባሻገር ወታደራዊ አመራሮችም አስተዳደሩን እንዳይገዳደሩ ይከላከላል።
"ውስጣዊም ውጫዊም ፀረ መንግሥት ተቃውሞዎችን ያመክናሉ" ሲሉ ያስረዳሉ።
ዕዙ በዕገታ እና በሰብአዊ ብዝበዛ እጁ አለበት የሚለውን ክስ ያስተባብላል።
የ32 ዓመት የዕዙ ወታደር ሦስት ሰዎችን ተኩሶ በመግደል እና የአንድ ዓመት ልጅን ጨምሮ ሁለት ሰዎችን በማቁሰል ሞት ተፈርዶበታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ የሞተር ሳይክል ሹፌር በዕዙ አባላት ስቅይት ደርሶበታል መባሉን ተከትሎ ምርመራ እንደሚደረግ ተገልጿል።
ግለሰቡ ነፍሰ ጡር ባለቤቱን ወደ ሆስፒታል እያደረሰ ሳለ ነበር ዕዙ በቁጥጥር ሥር ያዋለው።
ከዚህ ክስተት ከአንድ ወር በኋላ፤ ለቀናት ጠፍቶ የነበረ የተቃዋሚ ፖለቲከኛ ጠባቂ በዕዙ መያዙን የፕሬዝዳንቱ ልጅ ገልጸው ቁጣ ተቀስቅሷል።
"የእኔ ልጆች ኤድዋርድ ሴቦፉን ይዘውታል። ቤቴ ሥር ባለው ክፍል ይገኛል" ብሎ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፏል።
የተቃዋሚ ፖለቲከኛው ጠባቂ ፀጉሩን ተላጭቶ የሚያሳይ ምሥልም ለጥፏል።
"ፀጉሩን የላጩት የእኔ ልጆች ስለሆኑ አምሮበታል" ሲልም የፕሬዝዳንቱ ልጅ ተሳልቋል።
የኡጋንዳ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር እንደሚለው፣ ከጠባቂው በተጨማሪ ሌሎችም ሰዎች በዚህ ሠራዊት ተይዘዋል።
"ዕዙ ስልታዊ በሆነ መንገድ የተቃውሞ ድምጾችን ለማፈን ይንቀሳቀሳል። የነጻነት ናፋቂ ሕዝብን ተስፋ ይቀጫል" ብሏል ማኅበሩ።
የተቃዋሚ ፖለቲከኛው ጠባቂ በዕዙ መያዛቸው "አደገኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ጭቆና መኖሩን ያሳያል" ሲልም አክሏል።
ዕዙ ምሥጢራዊ እንቅስቃሴ ማድረጉ የሰብአዊ መብት ጥሰት ክሶችን አጠናክሯል። አመሠራረቱ ሕገ ወጥ ነው በሚልም ይተቻል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የአገሪቱ ፓርላማ ያፀደቀው መመሪያ ዕዙን ከኡጋንዳ አራት ወታዳራዊ ክንፎች አንዱ ያደርጋል።
ተቃዋሚ የሕዝብ እንደራሴዎች ውሳኔውን ነቅፈዋል። ዕዙ ሕጋዊ ዕውቅናው እንዲነሳም ጠይቀዋል።
ተቃዋሚ ፖለቲከኛው ሴሙጁ ንጉንዳ "በሕገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀስ ዕዝን ሕጋዊ ገጽታ የሚያላብስ ውሳኔ ነው" ብለዋል።
ዶ/ር ጄራልድ እንደሚሉት፤ ዕዙ ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘቱ "ያለውን የበላይነት የበለጠ የሚያጠናክር ነው።"
ኡጋንዳዊው ተንታኝ ጎድበር ቱሙሼቤ "አሁን ጦርነት ስለሌለ ነው ነገሮች ሰላም የሚመስሉት" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ዕዙ እየተጠናከረ በመምጣቱ መደበኛው ሠራዊት ደስተኛ አይደለም።
ዕዙ ውስጥ በብዛት የሚገኙት የሙሴቪኒ ጎሳ አባላት መሆናቸውን የቢቢሲ ምንጮች ጠቁመዋል።
ተቃዋሚው የሕዝብ እንደራሴ "ከምሥረታው ጀምሮ በዕዙ የሚካተቱት የሙሴቪኒ ጎሳ አባላት ናቸው" ይላሉ።
ከአውሮፓውያኑ 2007 ጀምሮ ቁልፍ አመራር ላይ ከነበሩ ስድስት ኮማንደሮች መካከል አንደኛው ብቻ ከምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ናቸው።
ከሙሴቪኒ በኋላ በሚኖረው የአገሪቱ ታሪክም መደበኛው ሠራዊት እና ልዩ ዕዙ ተገዳዳሪ ሆነው እንደሚቀጥሉ ስጋት አለ።
ተቃዋሚ ፖለቲከኛው "ትልቁ ፍርሃቴ ከሙሴቪኒ በኋላ ምን እንደሚከሰት አለማወቃችን ነው" ይላሉ።
በሁለቱ ኃይሎች መካከል የሚፈጠር የጥቅም ግጭት ወደ ፖለቲካዊ ቀውስ እንደሚያመራም ስጋት አለ።
በሌላ በኩል የፕሬዝዳንቱ ልጅ ሙሉ በሙሉ ዕዙን በመቆጣጠር የሙሴቪኒን አስተዳደር ያስቀጥላሉ ብለው የሚካረከሩም አሉ። ይሄንን አካሄድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሚቀበሉት አይሆንም።
ተቃዋሚ ፖለቲከኛው ቦቢ ዋይን (ሮበርት ኪጉላኒ) ላይ የሙሴቪኒ ልጅ የግድያ ዛቻ መሰንዘሩ ይታወሳል።
ነገሩ "ቀልድ ነበር" በማለት ጽሑፉን ከማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ቢያጠፋም፤ ቁጣ ማስነሳቱ አልቀረም።
ቦቢ ዋይን ይህ ዕዝ መበተን እንዳለበት ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"አገዛዙ በሥልጣን እንዲቆይ መሣሪያ የሆነ ኃይል ነው። ሕገ ወጥ ነው። ፕሬዝዳንቱን እና ልጁን ነው የሚጠብቁት" ብሏል።















