ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ልጃቸውን የአገሪቱ ጦር አዛዥ አድርገው ሾሙ

 ጄነራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ ከባለቤታቸው ቻርለት ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄነራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ ከባለቤታቸው ቻርለት ጋር

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የመጀመሪያ ልጃቸውን የአገሪቱ ሠራዊት አዛዥ አድርገው ሾሙ።

ፕሬዝዳንቱ ለበኩር ልጃቸው ጄነራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ ከፍተኛ የጦር ስልጣን መስጠታቸው እርሳቸውን እንዲተካ እያዘጋጁት ነው የሚለውን መላምት ያጠናከረ አድርጎታል።

አወዛጋቢው ጄነራል ካይኔሩጋባ እንደ አውሮፓውያኑ 2022 ከእግረኛ ጦር ኃይል አዛዥነታቸው ከተነሱ በኋላ በልዩ ዘመቻዎች ላይ የፕሬዝዳንቱ ከፍተኛ አማካሪ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ሐሙስ ዕለት በተካሄደው እና አምስት ሚኒስትሮች በተባረሩበት የካቢኔ ሹም ሽርም ደግሞ የአገሪቱ ሠራዊት አዛዥ ሆነው አዲስ ሹመት ተቀብለዋል።

የሠራዊት አዛዥ የነበሩት ጀነራል ዊልሰን የንግድ ሚኒስትርነት ተደገርው ተሹመዋል።

የ49 ዓመቱ ጄነራል በትዊተር ገጻቸው ላይ በሚያሰፍሯቸው ፅሑፎች ብዙውን ጊዜ መነጋገሪያ ናቸው።

በአንድ ወቅት ኬንያን ለመውረር ዝተው ነበር። ይህን ተከትሎም ካምፓላ ናይሮቢን በይፋ ይቅርታ ለመጠየቅ ተገድዳ ነበር።

ከዚህ በኋላም ጄነራል ካይኒሩጋባ ከአገሪቱ የምድር ጦር ኃይል አዛዥነት ሥልጣናቸው ተነስተዋል።

ጄነራሉ ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያን የተመለከተ በተለይ ደግሞ ከትግራይ ጋር የተያያዙ አስተያየቶችን ሲሰጡ ነበር።

የኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት አንድ ዓመት በደፈነበት ጥቅምት 2014 ዓ.ም. ላይ የትግራይ ኃይሎችን ደግፈው ትዊት አድርገው ነበር።

የጄነራል ሙሆዚ ትዊት ተከትሎ የኡጋንዳ መንግሥት አስተያየቱ የጄነራሉ እንጂ የጦሩን አቋም አይወክልም የሚል ማስተባበያን ሰጥቶ ነበር።

መስከረም 22/2015 ዓ.ም. በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሳፈሩት ጽሑፍ፤ “ትግራይ ሁሌም በልቤ አለች! ትግራይን እንድወድ እና እንድከላከል ከፈጣሪዬ ከእየሱስ ክርስቶስ የመጣ ትዕዛዝ ነው” ብለዋል።

ሐሙስ ዕለት በፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ በተደረገው ሹም ሹር ሌሎች ሹመቶች የተሰጡ ሲሆን ከኃፊነት የተሰናበቱም አሉ።

የጄነራል ካይኔሩጋባ ሁለት የቅርብ አማካሪዎች ሚኒስትር ተደርገው ተሹመዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት ክዳን የብረት ቆርቆሮች ስርቆት የሙስና ክስ የተመሰረተባቸው የካራሞጃ ክልል ሚኒስትር ሜሪ ጎሬቲ ኪቱቱ ደግሞ ከሥልጣናቸው ተነስተዋል።

ከአውሮፓውያኑ 1986 ጀምሮ ሥልጣን ላይ ያሉት ሙሴቪኒ፣ የ49 ዓመቱን ጀነራል ልጃቸው የሥልጣናቸው ወራሽ ለማድረግ እያመቻቹ ነው የሚለው መላምት ለዓመታት ቆይቷል።

ይህም በኡጋንዳ ንጉሥዊ ሥርዓትን ይፈጥራል የሚል ትችትን አስከትሏል።

ይሁን እንጂ ሙሴቪኒ የቀረበባቸውን ክስ አጣጥለውታል።

ሆኖም ጀነራሉ ልጃቸው የአባታቸውን የሥልጣን መንበር ለመረከብ ያላቸውን ፍላጎት ከሁለት ዓመታት በፊት ገልጸው ነበር።

ጄነራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ በወቅቱ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ እናታቸውን ፕሬዝዳንት በመሆን እንደሚክሷት ገልጸዋል። የአባታቸው ሥልጣን ወራሽ ናቸው የሚለውን ጥርጣሬ የሚያረጋግጥ መልዕክት ማስፈራቸው ብዙዎችን አስደንቆ ነበር።

ኡጋንዳ በ2026 ምርጫ ታካሂዳለች።