ከ‘ትግራይን እከላከላለሁ’ እስከ ‘ናይሮቢን እቆጣጠራለሁ’ የሚሉት አወዛጋቢው ጄኔራል

የኡጋንዳ የምድር ጦር አዛዥ ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የኡጋንዳ የምድር ጦር አዛዥ ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ እና የኡጋንዳ ጦር ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ሌ/ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ አነጋጋሪ የሆኑ አስተያየቶችን መስጠታቸውን ቀጥለዋል።

የኡጋንዳ የምድር ጦር አዛዥ የሆኑት ሌ/ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገራትንና መሪዎችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በመጻፍ ቅሬታን ሲፈጥሩ ቆይተዋል።

በተለይ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነትን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሯቸው መልዕክቶች ምክንያት በኢትዮጵያውያን ዘንድ መነጋገሪያ ለመሆን በቅተዋል።

ሌ/ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ ከሁለት ቀናት በፊት በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ፣ “. . . ትግራይን እከላከላለሁ” ብለው ካሰፈሩ ከሰዓታት በኋላ “ዳግማዊ ሚኒሊክ አያታችን ናቸው” በማለት ኢትዮጵያን የተመለከተ ሌላ ትዊት ለጥፈው ነበር።

በአፍሪካ በሥልጣን ላይ ለረጅም ዓመታት በመቆየት ከሚጠቀሱት አንዱ የሆኑትን አባታቸውን ዩዌሪ ሙሴቬኒን በመተካት ቀጣይ የኡጋንዳ መሪ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉት የጦር መሪ ሰኞ ዕለት በኬንያውያን ዘንድ መነጋገሪያ ሆነዋል።

ጄኔራሉ ምንም ባልተፈጠረበት ድንገት ብድግ ብለው “እኔ እና ሠራዊቴ የኬንያን መዲና ናይሮቢ ለመያዝ ሁለት ሳምንታት ይበቃናል” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

ሌ/ጄኔራል ካይኒሩጋባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ስለ ኢትዮጵያ እና ኬንያ እያነሱ መጻፋቸው ከአገራቸው መንግሥት አቋም ጋር የሚያያዝ ስለመሆኑ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም አነጋጋሪ በመሆን ትኩረትን ስበዋል።

ይህንንም ተከትሎ የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማክሰኞ መስከረም 24/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ የጄኔራሉን የትዊተር መልዕክት በቀጥታ ሳይጠቅስ፣ ከጎረቤት ኬንያ ጋር ለሚኖር ሰላም እና ትብብር ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።

እሁድ መስከረም 22/2015 ዓ.ም. በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሳፈሩት ጽሑፍ፤ “ትግራይ ሁሌም በልቤ አለች! ትግራይን እንድወድ እና እንድከላከል ከፈጣሪዬ ከእየሱስ ክርስቶስ የመጣ ትዕዛዝ ነው” ብለዋል።

በተመሳሳይ ዕለት ከሰዓታት በኋላ ደግሞ ጄኔራሉ ኢትዮጵያን በተመለከተ ባሰፈሩት ሌላኛው ጽሑፍ፤ “ዳግማዊ ሚኒሊክ አያታችን ናቸው። ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ አካል ናት። እንድትወድም አንፈቅድም። ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንወዳለን!” ሲሉ ጽፈዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት, 1
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ, 1

የ48 ዓመቱ ጎልማሳ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን የተመለከተ በተለይ ደግሞ ከትግራይ ጋር የተያያዙ አስተያየቶችን ሲሰጡ ነበር።

ጄኔራሉ የኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት አንድ ዓመት በደፈነበት ጥቅምት 2014 ዓ.ም. ላይ የትግራይ ኃይሎችን ደግፈው ትዊት አድርገው ነበር።

“የትግራይ መከላከያ ኃይሎች . . . የቆማችሁበትን ዓላማ እደግፋለሁ። የትግራይ እህቶቻችንን የደፈሩ እና ወንድሞቻችንን የገደሉ መቀጣት አለባቸው” ሲሉ ጽፈው ነበር።

ይህን የሌ/ጀነራል ሙሆዚ ትዊት ተከትሎ የኡጋንዳ መንግሥት አስተያየቱ የጄኔራሉ እንጂ የጦሩን አቋም አይወክልም የሚል ማስተባበያን ሰጥቶ ነበር።

በተጨማሪም ጄኔራሉ ከአገራቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ከጥቂት ወራት በፊት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋርም ተገናኝተው ነበር።

‘ናይሮቢን እቆጣጠራለሁ’

የኡጋንዳ የምድር ጦር አዛዥ የሆኑት ሌ/ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ የጎረቤት አገር ኬንያ መዲና ናይሮቢን በተመለከተ በትዊተር ገጻቸው ላይ የለጠፉት ሐሳብ ስላቅ ይሁን ጽኑ ፍላጎት ኬንያውያን ያስደሰተ አልነበረም።

ጄኔራሉ “እኔ እና ሠራዊቴ ናይሮቢን ለመያዝ ሁለት ሳምንት ቢወስድብን ነው” ብለዋል። ቀጠል አድርገውም “ጦራችን ናይሮቢን ከቆጣጠረ በኋላ የት መኖር መጀመር አለብኝ? ዌስትላንድስ ወይስ ሪቨርሳይድ?” ሲሉ የናይሮቢ አካባቢዎችን በመጥቀስ ትዊት አድርገዋል።

ይህ የጄኔራሉ ትዊት ግን ኬንያውያንን ያስቆጣ ሆኗል። አንዳንዶች ሙሴቪኒ የሰፋቸውን ሙሉ ልብስ ለብሰው የሚያሳይ ምስል በማያያዝ “ቅደሚያ የአባትህን ልብ ሰፊ ተቆጣጠር” በሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት, 2
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ, 2

ከሰኞ ጀምሮ ኬንያውያን በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የጄኔራሉን ጉዳይ በማንሳት ትችት እየሰነዘሩ ሲሆን፣ አንዳንዶችም ጄኔራሉ እንደሚባለው የአባታቸውን ሥልጣን የሚረከቡ ከሆነ ለአገራቸው ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ጽፈዋል።

ሌሎች ደግሞ በኬንያ እና ኡጋንዳ መካከል ያለውን ዴሞክራሲ በማነጻጸር የሙሴቪኒ ቤተሰብ ኡጋንዳውያንን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነፍገዋል ሲሉ ተችተዋል።

ይህን የጄኔራሉን አስተያየት ተከትሎ የኬንያ መንግሥትም ሆነ የኡጋንዳ ባለሥልጣንት በይፋ ያሉት ነገር የለም።

የኡሁሩ ለሦስተኛ ዙር አለመወዳደር

ሌ/ጄኔራል ካይኒሩጋባ ኬንያን በተመለከተ ሌላ ጸሁፋቸው ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ያለኝ ብቸኛው ችግር ለሦስተኛ ዙር አለመወዳደራቸው ነው ብሏል።

በኬንያ ሕገ-መንግሥት መሠረት አንድ ፕሬዝዳንት አገር መምራት የሚችለው ለሁለት የሥልጣን ዘመን ብቻ ነው። በዚህ መሠረት ኡሁሩ ከሁለት ወራት በፊት በተካሄደው ምርጫ ሳይሳተፉ ሥልጣን አስረክበው መንበራቸውን ለቀዋል።

ሌ/ጄኔራል ካይኒሩጋባ ግን “ከተወዳጁ ትልቁ ወንድሜ ጋር ያለኝ ብቸኛ ችግር ለሦስተኛ ዙር አለመወዳደሩ ነው። በቀላሉ ማሸነፍ እንችል ነበር” ሲሉ ጽፈዋል።

‘ጥሎሽ’ ለጣሊያናዊቷ ፖለቲከኛ

የ X ይዘትን ይለፉት, 3
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ, 3

የምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኡጋንዳ የምድር ጦር አዛዡ በሌላኛው አነጋገሪ ጽሑፋቸው ደግሞ ቀጣይዋን የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር የተመለከተ ነው።

ባለፈው ሳምንት በተደረገ ምርጫ ፓርቲያቸው በማሸነፉ የጣሊያን መሪ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ሰፊ ግምት ለተሰጣቸው ሴት ፖለቲከኛ ጂዮርጂ ሜሎኒ ጥሎሽ የመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተዋል።

“ለቀጣይዋ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ስንት ከብቶችን ልትሰጡ ትችላለችሁ?” ሲሉ ትዊተር ላይ የጠየቁት ጄኔራሉ፤ “አውሮፓውያን ለሚወዷቸው ሴቶች አበባ ይሰጣሉ፤ በአገሬ ባህል ግን ለምንወዳቸው ሴቶች የምንሰጠው ከብቶችን ነው” በማለት ባለ ግዙፍ ቀንድ ከብቶችን ምስል አያይዘው ትዊተር ላይ ለጥፈዋል።

ቀደም ብሎ ደግሞ በኡጋንዳ የጣሊያን አምባሳደር የጥሎሽ ዋጋ እንዲደራደሩ ሽማግሌ አድርጌ መርጫለሁ ሲሉ ጽፈው ነበር።

የጄኔራሉ አነጋጋሪነት ለምን?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አነጋጋሪው ጄኔራል በኡጋንዳ ጦር ሠራዊት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሲሆን፣ የሚሰጧቸው አስተያየቶችም መነጋገሪያ ከመሆን አልፈው ቁጣን እያስከተሉ ነው።

ሌ/ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ በተለይ በትዊተር ላይ የሚያሰፍሯቸው አነጋጋሪ እና አወዛጋቢ ፖለቲካዊ አስተያየቶች፣ በርካታ ተከታዮችን እያፈራለቸው ነው። ከዚህ አንጻር ግባቸው መነጋገሪያ በመሆን በርካታ ተከታዮችን ማግኘት ነው የሚሉ ሰዎች አሉ።

የኡጋንዳ መንግሥት ጄኔራሉ ትዊተር ላይ በሚያሰፍሯቸው መልዕክቶች ዙሪያ ብዙ ጊዜ ዝምታን የሚመርጥ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ግን የጄኔራሉ ሐሳብ የአገሪቱ መንግሥት አቋም ሳይሆን የግለሰቡ አስተያየት ነው በማለት ያስተባብላል።

አሁንም ኬንያውያን ከጄኔራሉ ሳይሆን የኡጋንዳ መንግሥት በይፋ የጄኔራሉን ጽሁፍ የሚያስተባብል ምላሽ እንዲሰጥ እንደሚፈልጉ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየጠየቁ የነበሩ ሲሆን ይፋዊ መግለጫም ወጥቷል።

የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጄኔራሉን የትዊተር መልዕክት ሳይጠቅስ በተዘዋዋሪ የተሰነዘረው ሐሳብ የመንግሥት እንዳልሆነ ገልጿል።

በዚህም የኡጋንዳ መንግሥት ከየትኛውም አገር ጋር የሚኖረው ግንኙነትን በተመለከተ ከማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚገኙ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል በሚተላለፉ መልዕክቶች አማካይነት አይሆኑም ብሏል።

ጨምሮም ኡጋንዳ ከኬንያ መንግሥት እና ሕዝብ ጋር ላለው ግንኙነትን ከፍተኛ ዋጋ እንደምትሰጥና ይህም የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደምትፈልግ ገልጿል።

ጄኔራሉ ግን በትዊተር ላይ ያሰፈሩት መልዕክት የቀሰቀሰውን ቁጣ ተከትሎ ማስተባበያ፣ ምላሽ ወይም ማብራሪያ ሳይሰጡ ሌሎች ጉዳዮችን በማንሳት ትዊት ማድረግ መቀጠላቸው በርካቶችን ግራ አጋብቷል።