የ12ኛ ክፍል ፈተና በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ መሰጠቱ ምን ለውጥ ያመጣል?

የፎቶው ባለመብት, SM
ከመስከረም 30/2015 ዓ.ም. ጀምሮ በሚካሄደው እና በ131 የፈተና ማዕከላት በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና 984 ሺህ ተማሪዎች ለፈተና ይቀመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አገር አቀፍ ትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ለቢቢሲ ገልጿል።
በወላይታ ዞን የሚኖረው ኢዮብ ፍቅሩ ደግሞ ዘንድሮ ለፈተና ከሚቀመጡት ተማሪዎች መካከል አንዱ ነው።
ኢዮብ ለ12ኛ ክፍል ፈተና አዲስ አይደለም።
አምና ተፈትኖ ውጤት አልመጣለትም።
“ተሰርቆ ወጥቶ ነበር” በተባለው እና ብዙ ውዝግቦች ያስተናገደው የአምና ፈተና የእሱንም ሕይወት ወዳ’ላሰበው አቅጣጫ ወስዶታል።
“እኔ በክፍል ውስጥ ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ። የእራሴንም አቅም አውቀዋለሁ። የተፈተኑኩትም ከማውቃቸው ተማሪዎች ጋር ነው። ግን ከእኔ ጋር የፈተኑ ለትምህርት ትኩረት የማይሰጡ ብዙ ተማሪዎች አልፈዋል። እኔ ግን ወድቂያለው” ብሏል።
ፈተናው ተሰርቆ ነበር ብሎ የሚያምነው ኢዮብ፣ በዚህም ሳቢያ እሱ ብቻ ሳይሆን ብዙዎች እንደተጎዱ ይናገራል።
“በጣም በማይሆን መንገድ ነበር ብዙ ያነበበ ተማሪ ጉድ የሆነው። ፈተናው ስለወጣ አንብቦ የሚሰራ ተማሪ በጣም ነበር የተጎዳው። በእራሱ ጥረት ለፈተና የተቀመጠ ተማሪ እና ውጪ ተሰርቶለት የመጣ ተማሪ እኩል አልታየም። ለትምህርት ብዙም ትኩረት የማይሰጡ ተማሪዎች ናቸው ከውጪ በገባ ፈተና ያለፉት” ሲል ያማርራል።
ዘንደሮ አምና ያጣውን ውጤት ለማግኘት በግሉ ተመዝቦ ለመፈተን ዝግጅት እያደረገ ነው።
ፈተናውን ግን አምና ከወስደበት በተለየ ቦታ ይሰጣል።
ኢዮብ ፈተናውን በሆሳዕና ዩኒቨርሲቲ ይወስዳል።
“ከዚህ በፊት ፈተና ወጥተው እንደሚሰረቁና ያለአግባብ በሆነ መንገድ ተሰርተው እንደሚገቡ ግልጽ ነበር” የሚለው ተማሪው ዘንድሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሰጡት ተማሪዎች የሰሩበትን ውጤት እንዲገኙ ያግዛል ይላል።
“ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መፈታናችን በራሳቸው ጥረት ለሚሰሩ ተማሪዎች እግጅ በጣም ጠቃሚ ነው። ከፍተኛ ቁጥጥር ስላለ እና የመሰረቅ ዕድሉም ዝቅተኛ ስለሆነ ለተዘጋጀ ተማሪ ጠቃሚ ነው” ብሎ ያምናል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆነችው እና ለዘንድሮ ፈተና ዝግጀት እያደረገች የምትገኘው ዲና እንድሪስም በኢዮብ ሃሳብ ትስማማለች።
ዘንደሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፈተና የምትቀመጠው ዲና፣ ከዚህ ቀደም ፈተናዎች ተሰረቁ የሚለው ዜና ይረብሻት እንደነበር ትናገራለች።
“ሞራልን ይጎዳል። ምክንያቱም እንደተማሪ ረጅም ዓመት የተለፋበት ነገር የመጨረሻ ፍሬው የሚታወቀው በ12ኛ ክፍል ፈተና ነው። ያንን ሁሉ ልፋት ላሰለፈ ተማሪ ፈተናው ተሰረቀ ሲባል ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው። ምንም ያልለፋ ሰው በለፋው ሰው ምትክ ጥሩ ደረጃ ይደርሳል። ለሚሰራ ተማሪ ተስፋ ያስቆርጣል” ትላለች።
እናም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለመፈትን የምትዘጋጀው ዲና፣ ዘንድሮ በከፍተኛ የመንግሥት ትምህርት ተቋማት ውስጥ ፈተናው መሰጠቱ የፈተና ወረቀት የሚሰረቀበትን ዕድል በመቀነስ “ሁሉም ተማሪ በልፋቱ፣ ባነበበው፣ በዕውቀቱ ልክ እንዲያገኝ ያግዛል” ብላ ታምናለች።
ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ፈተና
በሚቀጥለው ሳምንት ከሰኞ መስከረም 30/2015 ዓ.ም. ጀምሮ የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በጠንካራ ቁጥጥር ስር እንደሚደረግ የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፈተናው ተጀምሮ እስከ ሚጠናቀቅ ተማሪዎች ከትምህርት ተቋማቱ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው የገለጹ ሲሆን፣ በቦታ ውስንነት ምክንያት የማኅበራዊ እና የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት እንደሚፈተኑም ተናግረዋል።
በፈተናው ወቅት ተማሪዎች ተንቀሳቀሰሽ ስልኮችን ይዘው በፈተና ማዕከል ውስጥ መገኘት ያልተፈቀደላቸው ሲሆን፣ ይህንን ተላፍለው የተገኙ ተፈታኞች ከፈተናው ይታገዳሉ ተብሏል።
የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን ለመውሰድ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚቆዩ ከመሆናቸው ተጨማሪ፣ ፈተናውን የሚያስፈጽሙ ፈታኞችም ከትውልድ አካባቢያቸው ውጪ ባሉ ስፍራዎች እንደሚመደቡ የትምህርት ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በፈተና መስጫ ቦታዎችም የሚኖረው ጥበቃ በክልል ወይም በአካባቢ የፀጥታ አካላት ሳይሆን፣ ሙሉ ለሙሉ በፌደራል ፖሊስ አማካይነት እንደሚከናውን አስረድተዋል።
በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ባለ የፀጥታ ችግር ምክንያት 56 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ፈተናውን በሌላ ጊዜ እንደሚወስዱ የጠቀሱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ ከዚህ ውጪ ባሉ ምክንያቶች ፈተናውን መውሰድ ላልቻሉ ተማሪዎች ደግሞ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይሰጣል።
ፈተናው በዩኒቨርስቲዎች መሰጠቱ የሚኖረው ጥቅም
የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክትር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) እስከዛሬ ከነበረው ልምድ በተለየ የ12ኛ ክፍል መለቀቂያ ፈተና በሁሉም ከፍተኛ የመንግሥት ትምህርት ተቋማት ካምፓሶች ውስጥ እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ፈተናው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መሰጠት ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያስረዱ “ተማሪዎቹ ነገ ተፈትነው ሲያልፉ የሚገቡበትን ዩኒቨርሲቲ በተወሰነ ደረጃ እንዲያውቁ ይረዳል፣ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ነገ ስለምንልክላቸው ተማሪዎች እንዲያውቁ ያግዛል” ብለዋል።
እንዲሁም “እኛ እንደመንግሥት ልጆቹ ሳይረበሹ እንዲፈተኑ ጥበቃ እንድናደርግ ያግዘናል። ተረጋግተው እንደፈተኑ እናዳረጋለን ማለት ነው” ሲሉ አክለዋል።
ቀድም ሲል ፈተናዎች ከሚሰጡበት 3 ሺህ የፈተና ጣቢያዎች ወደ ወደ 131 ዝቅ ማለታቸውን ያነሱት ኃላፊው ይህ መሆኑ ፈተናዎች “አንዳንድ ሰዎች ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር በሚፈጥሩት ክፍተት” የነበሩ ስርቆቶችን በመቀነስ “ለፖለቲካ ፍጆታ” እንዳይውል ያግዛል ብለዋል።
በዚህም ተማሪዎች በሚገኙበት ክልል ውስጥ ባሉ እና በሚቀርቧቸው ካምፓሶች ውስጥ ፈተና የሚወስዱ ሲሆን፣ ከፈተና ማዕከላቱ ርቀው የሚገኙ ተማሪዎች ትራንስፖርት፣ ምግብ እና የመኝታ ስፍራ ይዘጋጅላቸዋል።
ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጀት መጠናቀቁን የገለጹት እሸቱ (ዶ/ር) “ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን አዘጋጅተዋል። እኛም ጋ የሚፈትኑ የሚያስፈትኑ ሰዎች ራሳቸውን አዘጋጅተው ወደ ሚፈትኑባቸው ተቋማት እየተንቀሳቀሱ ነው ያሉት” ብለዋል።
ፈተናዎችን ከስርቆት የመጠበቅ ጥረት
ፈተናው በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ስር በሚገኙ 102 ካምፓሶች ውስጥ በተደራጁ 131 የፈተና ማዕከላት ይሰጣል።
በፈተናው ቅድመ ዝግጅት ላይ በፀጥታ ችግር ያጋጠመ ችግር አለመኖሩን የሚያስዱት ኃላፊው ለፈተናው በቁ ሆነው በፀጥታ እና በሌሎች “ከአቅም በላይ” በሆኑ ምክንያቶች ከፈተናው የቀሩ ተማሪዎች ከዋናው ፈተና ጋር በእኩል ደረጃ የሚቀመጥ ፈተና በሌላ ዙር የሚፈተኑበት ዕድል እንዳለ ገልጸዋል።
በባለፉት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጡ ፈተናዎች ሾልከው በመውጣት ከተማሪዎች እጅ ሲደርሱ እንደነበር በስፋት መነጋገሪያ መሆኑ ይታወሳል።
ከዚሁ ክስተት ጋር በተያያዘም የተሰረቁ ፈተናዎችን ጥያቄዎችና መልሶችን በስፋት መሰራጨት ለመቆጣጠር ሲባል የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች በፈተና ሰሞን እንዲዘጉ የተደረጉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።
ቢሆንም ግን የብሔራዊ ፈተና ጥያቄዎች ተሰርቀው ወጥተዋል የሚሉ መረጃዎች በስፋት መሰራጨታቸው አልቀረም ነበር። ይህም በተፈታኞች ላይ ጫና እንደነበረው ተማሪዎች ይናገራሉ።
ይህንን ሁኔታ ለመቆጣጠር በሚል መንግሥት አገር አቀፍ ፈተናዎችን በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ ያለወረቀት በታብሌቶች አማካይነት ለመስጠት ከዚህ በፊት ዕቅድ ይዞ ነበር።
ይህንን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ገንዘብ እና የዲጂታል መሠረተ ልማት እንሚያስፈልግ የሚናገሩት እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
“መሠረተ ልማቶቹን የሟሟላት ሥራ ቀን ከሌት እየሰራን ነው። . . . ኮምፒውተርን መሰረት ያደረገ የፈተና ሥርዓት እንዲኖረን ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ሦስት ዓመት ሆኖታል” በማለት የዚህ ዓመቱ ግን በጥብቅ ቁጥጥር ስር በወረቀት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
“ፈተናዎች የማኅበረሰብ ሃብት ናቸው” የሚሉት እሸቱ (ዶ/ር) “በመንግሥትም ይሁን በሌላ አካል ያኮረፉ ግለሰቦች ከፈተና ጋር የሚፈጽሟቸው አሉታዊ ድርጊቶች የሚጎዱት ከምንም ውስጥ የሌሉ ተፈታኝ ልጆች መሆናቸውን መረዳት አለባቸው።
“. . . ስለዚህ በተቻለ መጠን የልጆቹን እና የቤተሰቦቻቸውን ሥነ ልቦና የሚረብሽ ወይም የወደፊት ተስፋቸውን የሚያጨልም ነገር ላይ እንደይሳተፉ በልጆቹ ስም በፈጣሪ ስም ልለምን እፈልጋለው” ብለዋል።












