በ12ኛ ክፍል ፈተና በሂሳብና ፊዚክስ ትምህርት 100 ያመጡት ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, OBN
የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና በሂሳብ የትምህርት ዘርፍ 100 ያስመዘገበችው ኢትዮጵያዊት ተማሪ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ከፍተኛ ሙገሳ እየተቸራት ይገኛል።
የ19 አመቷ ሲፋን ፊጣ በአዳማ ኦዳ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ ስትሆን የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና 542 አምጥታለች። ከ600 ከታረመው ፈተና በ2013 ዓ.ም በሃገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ከተፈኑ ሴት ተማሪዎች ከፍተኛና አንደኛ የተባለውን 542 አስመዝግባለች።
"''ከአስተማሪዎቼ ጋር ያለኝ ልዩ ግንኙነት እና የእነሱ ድጋፍ በሂሳብ እና በሌሎች የትምህርት ዓይነቶች ከፍተኛውን ውጤት እንዳስመዘግብ ረድቶኛል'' ስትል ሲፋን ተናግራለች።
የ2013 ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት ወይም ዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት በያዝነው ሳምንት ረቡዕ የሃገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ይፋ አድርጓል።
ሲፋን አክላም ''መምህራኖቻችን የሚኖሩት በዚሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ነው። በየትኛውም ጊዜ ጥያቄ ሲኖረን እኛን ሊደግፉን ዝግጁ ናቸው።'' ብላለች
ሲፋን በሂሳብ ትምህርት ያስመዘገበችው ውጤት በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሴት ተማሪ የተመዘገበ ሳይሆን እንደማይቀር የኦዳ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አቶ አበበ ዘውዲ ተናግረዋል።
ለዩኒቨርስቲ መግቢያ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡት ሌላኛው የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ኮኬት ተስፋዬ በፊዚክስ የትምህርት ዘርፍ 100 አግኝቷል።
በአጠቃላይ በድምሩም ከ600 ፣ 548 ውጤት ያስመዘገበው ኮኬት ለትምህርት ቤቱ ከፍተኛው እንዲሁም ምናልባት በኢትዮጵያም ደረጃ ከከፍተኛዎቹ ሶስት ውጤቶች መካከል ሳይሆን እንዳልቀረም ተገልጿል።
ኮኬት በዩኒቨርስቲ ቆይታው የምህንድስና ትምህርት መማር የሚፈልግ ሲሆን ሲፋን በበኩሏ የሶፍትዌር ምህንድስና የትምህርት ዘርፍ ነው ማጥናት የምትፈልገው።
የኦዳ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አበበ ዘውዴ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ለመግቢያ ፈተና ከተቀመጡት 177 ተማሪዎች መካከል 101 ተማሪዎች ከ500 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን ይህም በአንድ ትምህርት ቤት የተመዘገበ ከፍተኛው ውጤት ነው። ከ500 በላይ ውጤት ካስመዘገቡ 101 ተማሪዎች መካከል 32ቱ ሴቶች ናቸው።
''መምህራኖቻችን ከተማሪዎቻችን ጋር በአንድ ግቢ ውስጥ ይኖራሉ። ከተማሪዎቻችን ጋር በቀን 18 ሰአት አብረዋቸው ይሰራሉ። ተማሪዎቻችን ያለ ቤተሰባቸው ከማደሪያቸው (ከዶርማቸው) እንዲወጡ አንፈቅድም። አንዳንድ ጊዜ እሁድ ዩኒፎርማቸውን ለብሰው በቡድን ሆነው ወጥተው ራሳቸውን እንዲያዝናኑ እንፈቅዳለን። የአዳማ ከተማ ነዋሪ በሙሉ ተማሪዎቻችንን ያውቃቸዋል ›› ይላሉ አበበ።
በአገሪቱ አጠቃላይ በ2013 ዓ.ም ከፍተኛ ውጤት ያመጣው የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነው አላዛር ተካ ገመቹ ሲሆን ያስመዘገበውም ውጤት 563 መሆኑን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
አላዛር በሂሳብ እና ፊዚክስ የትምህርት ዓይነቶች መቶ ያመጣ ሲሆን በሁለት የትምህርት ዓይነቶች እንዲህ አይነት ውጤት ሲመጣ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
በዘንድሮው ዓመት ለከፍተኛ ትምህርት ወይም ዩኒቨርስቲ ገብተው ለመማር የሚያስችለውን ውጤት ይፋ ያደረገው ኤጀንሲው በዚህም መሰረት አጠቃላይ አማካይ ነጥብ 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚልም መስፈርት አስቀምጧል።
ሆኖም በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ገብተው ለሚማሩ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲዎችን የመቀበል አቅም ባገናዘበ መልኩ ዝርዝር የመግቢያ ነጥብ ወደፊት እንደሚገለጽም አመልክቷል።
በ2013 ዓ.ም መሰጠት የነበረበት የ12ኛ ክፍል ፈተና በተለያዩ ሃገራዊ ምክንያቶች ወደ 2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተሸጋግሮ በሁለት ዙር ተሰጥቷል።
በመጀመሪያው ዙር 544 ሺህ 568 ተማሪዎች የተፈተኑ ሲሆን በፀጥታ ችግር ምክንያት መፈተን ያልቻሉ ደግሞ በሁለተኛው ዙር 54 ሺህ 435 ተማሪዎች ተፈትነዋል።
በአጠቃላይ በሁለቱም ዙር ከተመዘገቡት 617 ሺህ 991 ተማሪዎች ውስጥ 599 ሺህ 003 (96.9 በመቶ) ተማሪዎች ፈተናውን መውሰዳቸው ተገልጿል።












