የ2013 የ12ኛ ክፍል የመጀመሪያው ዙር የሲቪክስ የፈተና ውጤት ለዩኒቨርስቲ መግቢያ እንዳያገለግል ተወሰነ

ሃገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታውቋል

የፎቶው ባለመብት, National Educational Assessment and Examinations

የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የመጀመሪያው ዙር የሲቪክስ የፈተና ውጤት ለዩኒቨርስቲ መግቢያ መወዳደሪያነት እንዳያገለግል መወሰኑን ሃገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ለዚህ በምክንያትነት ያቀረበው "የመጀመሪያው ዙር የሲቪክስ ፈተና በሁሉም ትምህርት ቤቶች በሚባል ደረጃ የውጤት መመሳሰልና ግሽበት" በመታየቱ ነው ብሏል።

ኤጀንሲው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ መሆኑን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ከሲቪክስ ፈተና ውጪ ባሉ የትምህርት ዓይነቶች ያለው ውጤት ምንም እክል ስላልታየበት እንዲመዘገብ ተደርጓል ብሏል።

በ2013 ዓ.ም መሰጠት የነበረበት የ12ኛ ክፍል ፈተና በተለያዩ ሃገራዊ ምክንያቶች ወደ 2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተሸጋግሮ በሁለት ዙር ተሰጥቷል።

በመጀመሪያው ዙር 544 ሺህ 568 ተማሪዎች የተፈተኑ ሲሆን በፀጥታ ችግር ምክንያት መፈተን ያልቻሉ ደግሞ በሁለተኛው ዙር 54 ሺህ 435 ተማሪዎች ተፈትነዋል።

በአጠቃላይ በሁለቱም ዙር ከተመዘገቡት 617 ሺህ 991 ተማሪዎች ውስጥ 599 ሺህ 003 (96.9 በመቶ) ተማሪዎች ፈተናውን መውሰዳቸው ተገልጿል።

አጠቃላይ የፈተና እርማቱም ደኅንነታቸው አስተማማኝ በሆኑ ማሽኖች፣ በፌደራል ፖሊስና በሴኩሪቲ ካሜራዎች ታግዞ በጥንቃቄ መከናወኑን ኤጀንሲው አስታውቋል።

ሆኖም ከዚህም ጋር ተያይዞ የፈተና ደንብ ጥሰት የፈጸሙ 141 ተማሪዎች ላይ ከውጤት መሰረዝ ጀምሮ በየደረጃው የተለያየ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱንም አስታውቋል።

በዘንድሮው ዓመት ለከፍተኛ ትምህርት ወይም ዩኒቨርስቲ ገብተው ለመማር የሚያስችለውን ውጤት ኤጀንሲው ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት አጠቃላይ አማካይ ነጥብ 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚልም መስፈርት አስቀምጧል።

ሆኖም በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ገብተው ለሚማሩ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲዎችን የመቀበል አቅም ባገናዘበ መልኩ ዝርዝር የመግቢያ ነጥብ ወደፊት እንደሚገለጽም አመልክትቷል።