ሩሲያ ዩክሬንን 'መውረር ጀምራለች' ያሉት ባይደን ሞስኮ ላይ ማዕቀብ ጣሉ

ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሜሪካ ሩሲያ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን ጣለች።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ ዩክሬንን 'መውረር ጀምራለች' ካሉ በኋላ አስተዳደራቸው በሞስኮ ላይ ጠንካራ መዕቀብ መጣሉን ያስታወቁት።

"ሩሲያን ከምዕራቡ ዓለም አገራት የፋይናንስ ፈሰስ እንቆርጣታለን" ብለዋል።

ውሳኔው ላይ የደረሱት ሩሲያ ወታደሮቿን ወደ ሁለት የዩክሬን ክልሎች ከላከች በኋላ ነው።

ሁለቱ ክልሎች በአማጽያን የተያዙ ሲሆኑ፤ ሩሲያ ከሰሞኑ ራሳቸውን የቻሉ ግዛቶች ናቸው ስትል እውቅና ሰጥታለች።

ሁለቱ በአማጽያን የተያዙ ክልሎችን ሩሲያ ነጻ ብላ ማወጇን ዩክሬን በጥብቅ ተቃውማለች። በተመሳሳይ በርካታ ምዕራባውያን አገራት በፑቲን እርጅማ ተበሳጭተዋል።

ሩሲያ ወደ ሁለቱ ክልሎች የገባችው ወረራውን ለማስፋፋት እንደሆነ ምዕራባውያኑ ሰግተዋል።

ዶንቴስክ እና ሉሀንስክ ወደተባሉት ክልሎች ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወታደሮቻቸውን የላኩት "ሰላም ለማስከበር ነው" ብለዋል።

ከሳተላይት የተገኘ ምስል እንደሚያሳየው ባለፉት 24 ሰዓታት አዳዲስ ወታደሮች እና መሣሪያዎች ወደ ምዕራብ ሩሲያ ተጠግተዋል።

በዩክሬን ጎረቤት ቤላሩስ ውስጥ ወታደራዊ ተሸከርካሪዎችም ታይተዋል።

በጉዳዩ ላይ ሩሲያ አስተያየት አልሰጠችም።

"ሩሲያ ከዩክሬን ግዙፍ ክፍል ልትወስድ እንደሆነ አስታውቃለች" ሲሉ ባይደን ተናግረዋል።

የጣሉት ማዕቀብ የሩሲያን የውጭ ብድር የሚገታ ሲሆን፣ ሩሲያ ከምዕራባውያን የፋይናንስ ተቋማት መበደር አትችልም ማለት ነው።

ባይደን የሩሲያ አመራሮችም "ሊቀጡ ይገባል" ብለው ማዕቀብ ጥለውባቸዋል።

በዩክሬን በአማጽያን የተያዙት ሁለት ክልሎች ውስጥ አሜሪካውያን እንዳይነግዱ ውሳኔ ተላልፏል።

17ቱ የአውሮፓ ኅብረት አገራት የሩሲያ ምክር ቤት አባላት ላይ ማዕቀብ ለመጣል ተስማምተዋል።

ይህም ሁለቱ የዩክሬን ክልሎችን ነጻ ግዛት ብለው ውሳኔ ያሳለፉ አመራሮችን ይጨምራል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እንዳሉት በአምስት ባንኮች የሩሲያውያን ሀብታሞች ተቀማጭ ገንዘብ ታግዷል።

በተጨማሪም ዩኬ የጉዞ እገዳ ጥላለች።

ጀርመን ከሩሲያ ወደ አውሮፓ ነዳጅ የሚያስተላልፈውን ግዙፍ ትቦ ሥራ አቋርጣለች።

አሜሪካ ጦሯን በሩሲያ አቅራቢያ ወደሚገኙት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) አባል አገራት ኢስቶኒያ፣ ላቲቪያ እን ሊቱኒያ እያስጣጋች ነው።

ጣልያንም ተዋጊ ጀቶችና ሄሊኮፕተሮችን ጨምሮ በፖላንድ ጦር እያሰፈረች ትገኛል።

የሩሲያ እና ዩክሬንን ፍጥጫ ለማርገብ የተሞከሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ፍሬ አላፈሩም።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ዲፕሎማሲን ፊት የነሳችው ሩሲያ አቋሟን ከለወጠች አሜሪካ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ናት ብለዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከሩሲያ ጋር አገራቸው ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሚያቋርጡ ተናግረዋል።

ዩክሬን አሁንም ዴፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንደምትሻ ቢናገሩም ለጥንቃቄ ሲሉ ወታደሮችን ወደ ሥልጠና ጠርተዋል።