ኤርዶሃን የሩሲያን እርምጃን እንደሚቃወሙ ለዩክሬኑ ፕሬዝደንት ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቱርኩ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን የሩሲያን ወቅታዊ እርምጃን እንደማይደግፉ ለዩክሬኑ አቻቸው ተናገሩ።
ሩሲያ ከዩክሬን ለተገነጠሉ ሁለት ግዛቶች እውቅና መስጠቷን ተከትሎ ኤርዶሃን የዩክሬንን የግዛት አንድነት የሚጻረር የሩሲያን እንቅስቃሴ እንደማይደግፉ ለዩክሬኑ ፕሬዝደንት ተናግረዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሩሲያ በሚደገፉ አማፂያን ቁጥጥር ሥር ላሉ ግዛቶች እውቅና መስጠታቸው ይታወቃል።
ይህ የኤርዶሃን አስተያየት የተሰማ ዩናይትድ ኪንግደም በሩሲያ ላይ ማዕቀብ መጣሏን፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት በተመሳሳይ ማዕቀብ ለመጣል በዝግጅት ላይ ሳሉ ነው።
ማዕቀብ መጣልን በመርኅ ደረጃ የሚቃወሙት ኤርዶሃን፤ አገራቸው ቱርክ ከሩሲያ እና ዩክሬን ጋር በጥቁር ባሕር በኩል ትዋሰናለች።
ኤርዶሃን ከዘለነስኪ ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር የሩሲያን ውሳኔ ተቀባይነት የሌለው እና ቀውሱን ለመፍታት ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መደረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የዩናይትድ ኪንገድም ማዕቀብ
የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሩሲያ ላይ ያነጣጠሩ ማዕቀቦችን አገራቸው መጣሏን ይፋ አድርገዋል። ዩኬ በአምስት የሩሲያ ባንኮች እና ሦስት ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የሩሲያው ፕሬዝደንት የዩክሬንን ሉአላዊ ግዛትን በመካድ ለመጠነ ሰፊ ወረራ እየተዘጋጁ ነው ብለዋል።
"ለፑቲን ቀጣዩ እቅድ እራሳቸችን ማዘጋጀት አለብን" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገራቸው የእንደራሴዎች ምክር ቤት ተናግረዋል።
ኃያላኑ ምዕራባውያን በሩሲያ እና በመሪያዋ ቭላድሚር ፑቲን ላይ ሊጥሉ ከሚችሏቸው ማዕቀቦች መካከል አንዱ የገንዝብ ዝውውር ዕቀባዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ቀደም ሲል ተንታኞች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ነበር።
በሩሲያ ባንኮች ላይ ማዕቀብ መጣሉ ባንኮቿ ከሩሲያ ውጪ ካሉ ባንኮች ጋር የገንዘብ ዝውውር ማድረግን በእጅጉ አዳጋች ያደርግባቸዋል።
ይሁን እንጂ የዩኬ ምክር ቤት አባላት በባንኮች እና በሦስቱ ግለሰቦች ላይ የተጣለው ማዕቀብ በቂ አይደለም ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ የቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ከሩሲያዋ ቅዱስ ፒተርስበርግ ወደ ሌላ ከተማ ሊሸጋገር እንደሚችልም ጠቁመዋል።












