በኢትዮጵያ፣ በናይጄሪያና በብራዚል መካከል በሚደረግ የዕፅ ዝውውር የተጠረጠረ ፖሊስ ተያዘ

የተቀነባበረ ክስ ነው የቀረበብኝ የሚለው አባ ኪያሪ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የተቀነባበረ ክስ ነው የቀረበብኝ የሚለው አባ ኪያሪ

በናይጄሪያ፣ በኢትዮጵያ እና በብራዚል መካከል የአደንዛዥ ዕፅ ከሚነግድ የዕፅ ዝውውር ቡድን ጋር ይሰራል የተባለ አንድ ከፍተኛ የናይጄሪያ ፖሊስ መኮንን በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነገረ።

አባ ኪያሪ የተባለው የፖሊስ መኮንን አህጉር አቋራጭ የሆነ ሕገ ወጥ የዕፅ ዝውውርን ከሚያካሂድ ቡድን ጋር አብሮ ይሰራል በሚል ነው ባለፈው ሳምንት በናይጄሪያ ፀረ ዕፅ ተቋም ተይዞ የታሰረው።

የፖሊስ መኮንኑ አባ ኪያሪ የቀረበበት ክስ በናይጄሪያ፣ በኢትዮጵያና በብራዚል በኩል ዕፅ ከሚያዘዋውር ቡድን ጋር ተባብሮ ይሰራል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ናይጄሪያዊው የፖሊስ መኮንኑ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ከሥራው የታገደ ሲሆን ከዓለም አቀፍ የዕፅ ዝውውር ቡድን ጋር በተያያዘ የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ከምዕራብ አፍሪካ በተለይም ከናይጄሪያ በሚደረጉ በረራዎች ላይ በሚያደርገው ክትትል በተለያዩ ጊዜያት በተለያየ መንገድ ሊዘዋወሩ የነበሩ ዕፅችንና አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን በተደጋጋሚ ሲገልጽ እንደነበር ይታወሳል።

ተከሳሹ በናይጄሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ውስጥ ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርቦ በጠበቆቹ በኩል በሰጠው ምላሽ የቀረበበት ክስ ሆን ተብሎ ስሙን ለማጥፋት የተቀነባበረ ነው ሲል ክዷል።

የናይጄሪያ የአደንዛዥ ዕፅ ተቆጣጣሪ አካል ባቀረበው ክስ የፖሊስ መኮንኑ ከዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ ከተያዘ 25 ኪሎ የሚመዝን ኮኬይን ተሽጦ ተቆጣጣሪ መኮንኖች እንዲከፋፈሉት በገንዘብ ሊያግባባቸው ሙከራ አድርጓል ብሏል።

ነገር ግን የፖሊስ መኮንኑ የቀረበበትን ክስ አልተቀበለውም።

ጨምሮም የዕፅ አዘዋዋሪዎችን ጠቁሞ ላስያዘ በሚሰጥ የገንዘብ ሽልማት ጥያቄ በማቅረቡ ሌሎቹ የዕፅ ተቆጣጣሪ መኮንኖች ሆን ብለው ወጥመድ ውስጥ እንዳስገቡት ገልጾ ተከራክሯል።

የፖሊስ መኮንኑን ከወከሉት ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ሐምዛ ኑሁ ዳንታኒ ለቢቢሲ እንደገለጹት ደንበኛቸው በዋስ እንዲለቀቅ ማመልከቻ አስገባለሁ ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን ሐሙስ ዕለት ይመለከተዋል ተብሏል።

ተከሳሹ አባ ኪያሪ በናይጄሪያ ውስጥ ሰዎችን የሚጠልፉ የወንጀለኛ ቡድኖችን እና የማጭበርበር ወንጀሎችን የሚዋጋውን የናይጄሪያ ፖሊስ ክፍል በመምራት ታዋቂነት አትርፎ ነበር።

ግለሰቡ በኢንተርኔት አማካኝነት በዓለም ዙሪያ የማጭበርበር ድርጊት ተጠርጥሮ አሜሪካ ውስጥ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እያታየ ካለው ሃሽፑፒ ከተባለው ግለሰብ ጋር ግንኙነት አለው በሚል ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከሥራው ታግዶ ነበር።

"ታላቁ ፖሊስ" በሚል የሚታወቀው አባ ኪያሪ ይህንንም ክስ በወቅቱ ውድ ቅ አድርጎት ነበር።