ከትዊተርና ፌስቡክ የታገዱት ዶናልድ ትራምፕ የራሳቸውን ማኅበራዊ ሚዲያ ፈጠሩ

ትራምፕ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል የተባለ ማኅበራዊ ሚዲያ ፈጥረው እያስተዋወቁ ነው።

በአሜሪካ የአፕል ስልክ መተግበሪያ መጫኛ ለተጠቃሚዎች የቀረበው ትሩዝ ሶሻል፤ ከትዊተር ጋር ተመሳሳይነት አለው።

ትራምፕ አምና ከትዊተር፣ ፌስቡክ እና ዩቲዩብ መታገዳቸው ይታወሳል።

አዲሱን የትራምፕ ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም የፈለጉ ሰዎች ለመመዝገብ እንደተቸገሩ አሳውቀዋል።

የማኅበራዊ ሚዲያው ፕሮጀክት መሪ የሆኑት የቀድሞው የኮንግረስ አባል ዴቪን ኑንስ ማኅበራዊ ሚዲያው በቀጣዩ ወር ማገባደጃ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልጸዋል።

የትራምፕን ማኅበራዊ ሚዲያ የፈጠረው አምና የተመሠረተው ትራምፕ ሚዲያ ኤንድ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ነው።

በይፋ ከመለቀቁ በፊት በ500 ሰዎች ተሞክሯል።

ባለፈው ሳምንት የትራምፕ ልጅ የሆነው ትራምፕ ጁንየር በማኅበራዊ ሚዲያው አባቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የጻፉትን ጠቅሶ "የምትወዱትን ፕሬዝዳንት ከሰሞኑ ታገኙታላችሁ" ብሏል።

በካፒቶል ሂል ከተነሳው ነውጥ በኋላ ትዊተር ትራምፕን ማገዱን አስታውቆ ነበር።

አዲሱ የትራምፕ ማኅበራዊ ሚዲያ ልክ እንደ ትዊተር ምላሽ መስጫ (ሪፕላይ)፣ መልሶ ማጋሪያ (ሪትዊት) እነና የመውደድ (ላይክ) አማራጮች ይዟል።

ማኅበራዊ ሚዲያው እየተዋወቀ ያለው "ማንኛውንም ፖለቲካዊ አቋም ሳያገል ነጻ፣ ግልጽ እና እውነተኛ ውይይትን የሚያበረታታ" በሚል ነው።

ትራምፕ እንደሚሉት በትዊተር እና ፌስቡክ ያለውን "ሳንሱር" ለማለፍ የእሳቸው አይነት ማኅበራዊ ሚዲያ አንድ አማራጭ ነው።

የማኅበራዊ ሚዲያ ፕሮጀክቱ መሪ "ትሩዝ ሶሻል ከሳንሱር የጸዳ ነው" ብለዋል።

በእርግጥ አፕስቶር እንዲሁም ጉግል ፕለይ የተባሉት የመተግበሪያ መጫኛዎች ላይ ሕግ የሚጥስ ይዘት ሲሰራጭ ይሰርዛሉ።

ይህ ማለት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ሳንሱር የሌለበት ማኅበራዊ ሚዲያ አለ ለማለት አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ትራምፕ ቀድሞ ትዊተር ላይ ሳሉ 88 ሚሊዮን ገደማ ተከታዮች ነበሯቸው።

በብሩኪንግስ ተቋም ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ባለሙያው ዳሬል ዌስት እንደሚሉት፤ በአንድ ጊዜ ማኅበራዊ ሚዲያን ገናና ማድረግ ቀላል አይደለም።

"እነ ትዊተር እዚ የደረሱት በአንድ ጀንበር አይደለም። ትራምፕ ዘርፉን ካሰቡት በላይ ከባድ ሆኖ ያገኙታል" ብለዋል።

ፓርለር በተባለው መተግበሪያ ላይ የተሰራጩ መልዕክቶች ሕግ የጣሱ ናቸው ተብሎ አፕል እና ጉግልም መተግበሪያውን ከገጻቸው ማውረዳቸው ይታወሳል።

ይህንን እንደ ማስረጃ በመጥቀስም የቴክኖሎጂ ባለሙያው "ትራምፕ የራሳቸው ማኅበራዊ ሚዲያ ቢኖራቸውም መርሕ ከጣሱ ከአፕ ስቶር መባረራቸው አይቀርም" ይላሉ።

ከትራምፕ ማኅበራዊ ሚዲያ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ገተር መተግበሪያ ቃል አቀባይ ጄሰን ሚለር በበኩላቸው "ይህንን ማኅበራዊ ሚዲያ እውን ለማድረግ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎችን ማግኘት ይጠይቃል" ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

"ብዙዎች ትልልቅ የማኅበራዊ ሚዲያ ተቋሞችን የሚተች አስተያየት በመስጠታቸው ይፈራሉ። አማራጭ ሐሳብ ማቅረቢያ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲኖሩ ግን ይህ ስጋት ይቀረፋል" ብለዋል።

እንደ ገተር እና አዲሱ የትራምፕ ዓይነት ማኅበራዊ ሚዲያዎች "መንግሥታትን ጨምሮ ስኬታማ እንዳይሆኑ የሚፈልጉ አሉ" ሲሉም ተናግረዋል።