የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢው ፕ/ር መስፍን አርአያ ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Ebs
ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀረቡ 11 ዕጩ ኮሚሽነሮችን ሲያጸድቅ፣ ፕ/ር መስፍን አርአያ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ሆነው ተሰይመዋል።
ከአስራ አንዱ ኮሚሽነሮች መካከል በሰብሳቢነት ፕ/ር መስፍን ሲሾሙ፣ ወይዘሮ ሒሩት ገብረሥላሴ ደግሞ የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ ሆነዋል።
ለመሆኑ ፕ/ር መስፍን አርአያ ማናቸው? እስካሁንስ በሙያቸው ምን አበርክተዋል?
ፕ/ር መስፍን ከሩሲያ ትምህርት ቤት እስከ ኢትዮጵያ ሆስፒታሎች
የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ ነሐሴ 1946 ዓ. ም. ነው።
በ1972 ዓ. ም. ከሩሲያው ቅዱስ ፒተርስበርግ የሕክምና ትምህርት ቤት በሕክምና የዶክትሬት ዲግሪ (MD) አግኝተዋል።
ከዚያም በ1982 ዓ. ም. ኔዘርላንድስ ከሚገኘው ግሮኒንገን ዩኒቨርሲቲ በአእምሮ ሕክምና ስፔሻሊቲ ዲፕሎማ (DPM) ተቀብለዋል፡፡
በተጨማሪም በ2000 ዓ. ም. ስዊድን ከሚገኘው ኡሜዮ ዩኒቨርሲቲ ዶክተር ኦፍ ፊሎሶፊ ዲግሪ (PhD) አግኝተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ከተሞች እንዲሁም የሕክምና ተቋሞች ለዓመታት አገልግለዋል።
ከእነዚህም መካከል ከ1974-75 ዓ. ም. በትግራይ፣ አዲግራት ከተማ በራስ ስብሐት ሆስፒታል በጠቅላላ ሐኪምና የሕክምና ዳይሬክተርነት እንዲሁም ደሴ በሚገኘው ደሴ ሆስፒታል ከ1975-76 ዓ. ም. በጠቅላላ ሐኪምና የሕክምና ዳይሬክተርነት ማገልገላቸው ይጠቀሳል።
ከ1976-79 ዓ. ም. በአማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ በጠቅላላ ሐኪምና የሕክምና ዳይሬክተርነት ሠርተዋል።
ከ1982 እስከ 1987 ዓ. ም. ደግሞ በዚያው ሆስፒታል በአእምሮ ሐኪምነት አገልግለዋል።
ፕ/ር መስፍን፣ ከ1987 አንስቶ ለዓመታት በዘውዲቱና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች በአእምሮ ሐኪምና መምህርነት ሠርተዋል።
ከ1997 ዓ. ም. ጀምሮ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአእምሮ ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ እንዲሁም መምህር ሆነው አገልግለዋል።
ከ2001-2003 ዓ. ም. የቅዱስ ጳውሎስ የሕክምና ትምህርት ቤት ዲን እንዲሁም ከ2003-2006 ዓ. ም. የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ ከፍተኛ የትምህርት አመራር ሆነዋል።
የፕ/ር መስፍን ተሳትፎና አበርክቶ
ፕ/ር መስፍን በተለይም በጤናው ዘርፍ በርካታ ማኅበራትን በመመሥረት፣ በአባልነት በማገልገልና እና በመምራትም ይታወቃሉ።
ለአብነት የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ጤና አጠባባቅ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የአእምሮ ሕክምና ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ይጠቀሳሉ።
የብሔራዊ ኤችአይቪ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት አደራጅ ግብረ ኃይል አባል፣ የብሔራዊ ኤችአይቪ መከላከልና መቆጣጠር ምክር ቤት መሥራችና አባል በተጨማሪም የተስፋ ጎሕ ቫይረሱ በደማቸው ያለ ወገኖች ማኅበር የአማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ሠርተዋል።
ፕ/ር መስፍን የብሔራዊ ይቅርታ ቦርድ አባል፣ የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ጆርናል ዋና አዘጋጅ፣ የመድኃኒትና ሕክምና አቅራቢ ድርጅት (ፋርሚድ) የቦርድ ሰብሳቢ፣ የአእምሮ ጤና ክብካቤ ማኅበር በኢትዮጵያ የቦርድ አባልም ናቸው።
በተጨማሪም የፌዴራል ሆስፒታሎች አመራር ቦርድ አባል፣ የአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አመራር ቦርድ አባል እንዲሁም የመድኃኒትና ምግብ ቁጥጥርና አስተዳደር የአማካሪ ቦርድ አባል ሆነው ሠርተዋል።
ወደ 30 በሚጠጉ ታዋቂ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የሕክምና መጽሔቶች ጽሑፎቻቸውን አሳትመዋል።
ፕ/ር መስፍን ያገኟቸው ሽልማቶች
ፕ/ር መስፍን ከአገራዊው የበጎ ሰው ሽልማት አንስቶ በአገር ውስጥና በውጭ አገራትም የተለያዩ የዕውቅና ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።
የበጎ ሰው ሽልማት መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነትን በብቃት በመወጣት ዘርፍ ነበር የሸለማቸው።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ላከናወኗቸው የአእምሮ ጤና አገልግሎቶች ከአሜሪካው ቴዎዶርና ቫዳ ስታንሊ ፋውንዴሽን ሽልማት አግኝተዋል።
ፒፕል ቱ ፒፐል፣ የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር፣ ተስፋ ጎህ ቫይረሱ በደማቸው ያለ ወገኖች ማኅበር፣ ፋርሚድ እና ራድዮ ፋናም ለአበርክቷቸው እውቅና ሰጥተዋል።
በተጨማሪም በ1998 ዓ.ም. የአእምሮ ጤናን ለማሻሻል ባበረከቱት አስተዋጽኦ የሮበርት ጊል የወርቅ ሜዳሊያን አግኝተዋል።
የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር በ2003 ዓ. ም. ለተምሳሌታዊ የሕክምና አገልግሎት የወርቅ ሜዳሊያ ሰጥቷቸዋል።
በ2006 ዓ. ም. የጤና ሚኒስቴር ለረዥም ጊዜ ተምሳሌታዊ የጤና አገልግሎት የወርቅ ሜዳሊያ አበርክቶላቸዋል።
በተጨማሪም የምግብና መድኃኒት ቁጥጥርና አስተዳደር ለዓመታት የጤናው ዘርፍ አገልግሎታቸው በ2006 ዓ. ም. የወርቅ ዋንጫ ሰጥቷቸዋል።
የበጎ ሰው ሽልማት መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነትን በብቃት በመወጣት ዘርፍ ነበር የሸለማቸው።












