የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት አገራዊ የምክክር ኮሚሽንን የማዋቀሩ ሂደት እንዲቆም ጠየቀ

ዶ/ር ራሄል ባፌ

የፎቶው ባለመብት, EPPJC/FB

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን የማዋቀር ሂደት ግልጽነትና ገለልተኝነት ላይ ቅሬታውን በመግለጽ ሂደቱ ለጊዜው እንዲቆም ጠየቀ።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ራሄል ባፌ የምክክር ኮሚሽኑን ለማቋቋም የተደረገው ሂደት ግልጽነት የጎደለው፣ ገለልተኛ እና አካታች ባለመሆኑ ምክር ቤቱ ቅሬታውን ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረቡን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ቅሬታውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እና ለምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ያስገባው ባለፈው የካቲት 03/2014 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔው ከተወያየ በኋላ ነው።

"ሂደቱ አስተማማኝ ካልሆነ የምንጠብቀውን ውጤት አያስገኝም" ያሉት ሰብሳቢዋ የጋራ ምክክሩ ለአገሪቷ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ኮሚሽነሮችን የመለየት እና የሹመት ሂደቱን ለጊዜው በማቆም እንደገና አካታችና ተዓማኒ ሂደት እንዲጀመር መጠየቃቸውን አስረድተዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነርነት ከሕዝብ ከተጠቆሙ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ግለሰቦች መካከል በዕጩነት የተለዩ የ42ቱን የስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል።

በቀጣይ ሂደትም ከ42ቱ መካከል ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኮሚሽነርነት የሚሰየሙትን ለመለየት በቀረቡት ዕጩዎች ላይ ሕዝብ አስተያየት እንዲሰጥ ምክር ቤቱ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

የምክክር ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ መሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል ሂደትን የሚመራና የሚያስተባብር አካል ነው።

ከዚህ ቀደም የምክክር ኮሚሽኑ አዋጅ ላይ አስተያየት ለመስጠት የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ረቂቅ አዋጁን አቅርበው 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች በተገኙበት መወያያታቸውን ያስታወሱት ዶ/ር ራሄል፤ በወቅቱ መሻሻል ያለባቸውን ነጥቦች ነቅሰው ማውጣታቸውንና ተጨማሪ ሃሳቦች መስጠታቸውን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ እነዚህ የተነሱት ነጥቦች ሳይካተቱና ሳይስተካከሉ ወደ ዕጩዎች መለየት እና ሹመት ተገብቷል ብለዋል።

ለኮሚሽኑ በዕጩነት የቀረቡት በኮሚሽኑ አዋጅ አንቀጽ 13 ላይ የተቀመጡ ደንቦችን ያሟሉ አይደሉም ሲሉም ይወቅሳሉ።

ከእዚህም ሁለት ዜግነት ያላቸው፣ የፖለቲካ ወገንተኝነት ያላቸው፣ በወንጀል የተከሰሱና ተፈርዶባቸው ታስረው የነበሩ ሰዎች በዕጩነት መካተታቸውን ለአብነት ያነሳሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን [ከአርባ ሁለቱ ውስጥ አራቱ ብቻ ሴቶች ናቸው]፣ ወጣቶች ተሳታፊ አለመሆናቸውን እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲው የጋራ ምክር ቤትም ከግምት ውስጥ አለመግባቱን አክለዋል።

ይህንን ቅሬታ ለማስገባት አልዘገያችሁም ወይ ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ራሄል "በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተነጋገርን በኋላ ተስተካክሎ ለሁለተኛ ግምገማ እንዲቀርብ ብንስማማም ድጋሚ ሳንነጋገርበት ጸድቋል" ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደ ተወካዮች ምክር ቤት ሲመራ እንዳይቀርብ ጠይቀው እንደነበር ሰብሳቢዋ አስታውሰዋል።

በተጨማሪም ለአፈ ጉባኤ ጽ/ቤት ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ለፕሬዚደንት ጽ/ቤት ፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር እና ለገዥው ፓርቲ ደብዳቤ ማስገባታቸውን አንስተዋል።

"ሰሚ አላገኘንም፤ በመንግሥታዊ ሥልጣን ነው የሄዱት። አሁንም ቅሬታችንን አቅርበናል ካልተቀበሉን ወደ ሕዝብ የሚሄድ ጉዳይ ይሆናል" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት የቆዩና ውይይትና መግባባት ላይ ሊደረስባቸው ይገባል በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ ውይይት እዲካሄድ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ይህንን የሚመራ 11 አባላት ያሉት ኮሚሽን ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው።

ነገር ግን የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ምስረታ ሂደትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በተጨማሪ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታና ተቃውሞ ሲያስሙ ቆይተዋል።