ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ሆኑ

ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

የፎቶው ባለመብት, Ebs

የምስሉ መግለጫ, ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮችን የቀረቡ አስራ አንድ ዕጩዎችን ሲሾም፣ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ሆነው ተሰየሙ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ሰኞ የካቲት 14/2014 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው በአፈ ጉባኤው ታገሰ ጫፎ በቀረቧቸው 11 ዕጩ ተሿሚዎች ላይ ድምጽ ተሰጥቶ ሹመታቸው ጸድቋል።

ከአስራ አንዱ የኮሚሽነሮች መካከል በሰብሳቢነት ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ሲሾሙ፣ ወይዘሮ ሂሩት ገብረሥላሴ ደግሞ የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ ሆነዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት 335 አባላት በተገኙበት በተሰጠው ድምጽ፣ አምስቱ ድምጸ ታዕቅቦ ያደረጉ ሲሆን ቀሪዎቹ እንደራሴዎች ሹመቱን ደግፈው አጽድቀውታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ መሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል ሂደትን የሚመራና የሚያስተባብር አካል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ለማቋቋም ጥቆማ መካሄዱ ይታወሳል።

ከጥቂት ወራት በፊት ለሕዝብ በቀረበ ጥሪ መሠረት 632 ዕጩዎች ለኮሚሽኑ አባልነት በተለያዩ ወገኖች ተጠቁመው ከእነዚህ መካከልም ኮሚሽኑን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ መስፈርቶች መሠረት 42ቱ ተለይተው ኅብረተሰቡ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ዝርዝራቸው ይፋ መድረጉ ይታወሳል።

ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኮሚሽነርነት ከቀረቡት ከ42ቱ ዕጩ ተጠቋሚዎች መካከል መስፈርቱን በከፍተኛ ደረጃ አሟልተዋል የተባሉት ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ተሹመዋል። በዚህ መሠረትም፦

1. ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

2. ወይዘሮ ሂሩት ገብረሥላሴ

3. ዶክተር ተገኘወርቅ ጌቱ

4. አምባሳደር ዶክተር አይሮሪት መሐመድ

5. ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ

6. ዶክተር ዮናስ አዳዬ

7. አምባሳደር መሐሙድ ድሪር

8. ወይዘሮ ብሌን ገብረመድኅን

9. አቶ ዘገየ አስፋው

10. አቶ መላኩ ወልደማሪያም

11. አቶ ሙሉጌታ አጎ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስራ አንዱን ኮሚሽነሮች ከመሰየሙ በፊት ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነርነት የተጠቆሙትን የ42ቱን ግለሰቦች ዝርዝር ከአጭር የትምህርትና የሥራ መግለጫ ጋር በድረ ገጹ ላይ ይፋ አድርጎ ሕዝቡም አስተያየት እንዲሰጥባቸው ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ከዚህ ሂደት በኋላም በተጠቋሚ ዕጩዎቹ ላይ በተዘጋጀው መስፈርት መሠረት ከሕዝብ የሚቀርበው አስተያየት ተገምግሞ የመጨረሻዎቹ 11 ዕጩ ኮሚሽነሮች ተለይተው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ እንዲሾሙ አድርጓል።

ኮሚሽኑ በአገሪቱ ለዘመናት የቆዩ ናቸው በተባሉ የተለያዩ አወዛጋቢና ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸው ወገኖችንና ኃይሎችን በማቀራረብ ውይይት ተደርጓ መግባባት ላይ እንዲደረስ ለማድረግ የሚያስችሉ ምክክሮችን ይመራል ተብሎ ይጠበቃል።