በአፍሪካ ግዙፉ የኃይል ማመንጫ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኤሌክትሪክ ማመንጨት ጀመረ

ታላቁ ህዳሴ ግድብ

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ እሁድ የካቲት 13/2014 ዓ.ም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀመረ።

ይህ ግንባታው አስራ አንድ ዓመታት ያህል ባስቆጠረው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ትልቅ ምዕራፍ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የተለያዩ ባለሥልጣናት በቤንሻንጉል ጉሙዝ በጉባ ወረዳ በታደሙበት ዝግጅት ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጨት መጀመሩ ተበስሯል።

በባለፉት ሁለት ዓመታት ክረምት ወቅቶች ሙሌቱ የተከናወነውና ለዓመታት በቀጣናው የውዝግብ ምንጭ የሆነው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በይፋ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል።

ግድቡ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል አንዱ ተርባይን ነው ከተሳካ ተከላ እና ሙከራ በኋላ የመጀመሪያውን ኃይል የማመንጨት ሥራ የጀመረው።

ይህ ሥራ የጀመረው ተርባይን 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተገልጿል።

የ13ቱም ተርባይኖች ግንባታ ሲጠናቀቅ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የማመንጨት አቅም 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት እንደሚደርስ የተገለጸ ሲሆን ይህም በአፍሪካ ውስጥ ትልቁ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ አመንጪ ያደርገዋል።

በኢትዮጵያውያን የቦንድ ግዥና በመንግሥት በጀት እየተገነባ ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እስካሁንድ ደረስ 163 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበትም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ግድቡ ግንባታ ጅማሮው ላይ በ80 ቢሊዮን ብር ወጪ ይገነባል የሚል ዕቅድም ተይዞ ነበር።

ግድቡ 145 ሜትር ከፍታና ወደ ጎን ደግሞ 1 ሺህ 780 ሜትር ርዝመት ሜትር አለው።

ግድቡ የሚይዘውን 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ሙሉ በሙሉ ሲይዝም ውሃው የሚተኛበት ስፍራ ርዝመት 246 ኪሎ ሜትር እንደሚደርስም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኃይል ማመንጨት ጅማሮውን አስመልክቶ ባስተላፉት መልዕክትም "ዛሬ የአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ የሕዳሴ ግድብ ሥራውን ጀምሯል። ይህ ለአህጉራችን እንዲሁም አብረናቸው ሠርተን በጋራ ለመጠቀም ለምንሻ የታችኛው ተፋሰስ አገራት የምሥራች ነው።

"አባይ ወንዛችንን አገራችንን አልምቶ ጎረቤቶቻችንን ሊያረሰርስ ጉዞውን ቀጥሏል። ዛሬ ለኢትዮጵያ የብርሀን መባቻ ነውና መላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አለን!" ብለዋል።

ለዓመታት ያህል በግብፅ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የሦስትዮሽ ድርድር የተካሄደበት ታላቁ ግድብ ጉዳዩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲፈታ ተመርቶ ነበር።

በሦስቱ አገራት መካከል የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር አፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ በተለያዩ አሸማጋዮች እልባት እንዲያገኝ ቢሞከርም ሊቋጭ አልቻለም፤ አሁንም በእንጥልጥል ላይ ይገኛል።

በተለይም ከሙሌቱ ጋር ተያያይዞ አሳሪ ስምምነት ሳይኖር መከናወን የለበትም በሚል ግብፅና ሱዳን ቢሞግቱም በ2012 እና በ2013 ክረምቶች ሙሌቱ በተሳካ ሁኔታ መከናወኑ ተገልጿል።

ለግንባታው ከ4.5 ቢሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በ2012 ዓ.ም 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዙ በወቅቱ ተገልጿል። የግድቡ ቁመትም ከባህር ጠለል በላይ 565 ሜትር ደርሶ ነበር።

የሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታው ሂደት ወደ 84 በመቶ መድረሱም ተገልጿል።

ግድቡ የውሃ የመያዙ አቅሙ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን ለባለፈው ዓመት ክረምትም 13.5 ቢሊዮን ያህል ውሃ ሙሌት ታቅዶ ነበር።

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ክረምት ላይም የውሃ ሙሌቱን በተመለከተ ግቧን ማሳካቷን አሳውቃለች ፤ ይህም ማለት ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል በቂ ውሃ አለ ማለት ነው።

ይህም ውሃ በታችኛው ተፋሰሰስ አገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስና የመጀመሪያ ደረጃ የግድቡ የውሃ ሙሌት መመሪያም የተወሰደው ሦስቱ አገራት ከተስማሙበት የግድብ ትብብር መግለጫ ስምምነት መሆኑንም በወቅቱ ኢትዮጵያ ጠቅሳለች።

ለዓመታት ያህል በግብፅ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ሲደረግ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ፍሬ ሳያፈራ የቀረ ሲሆን ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌቱን ተከትሎ ግብፅና ሱዳን ጉዳዩን ወደ ተመድ የፀጥታ ጉባኤ ምክር ቤት ወስደውት ነበር።

በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር ሲደረግ የነበረው ድርድር ምንም ፍሬ አላፈራም ሲሉም ነበር ወደ ምክር ቤቱ ጉዳዩን የወሰዱት።

ምክር ቤቱ የሕዳሴ ግድብን ውዝግብ ከተለያዩ ወገኖች ከሰማ በኋላ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ወደ አፍሪካ ሕብረት እንዲመለሱ ምክር ለግሶ ልኳቸዋል።

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ግብፅ የቅኝ ግዛት ውሎችን ሙጥኝ እንዳለችና ኢ-ፍትሃዊና አግላይ የሆነውን ስምምነት ተቀባይነት እንዲያገኝ ጫና እያደረገች ነው በማለትም ትወቀሳለች።

ባልነበረችበት የተፈረመ ስምምነት ለአባይ ወንዝ 77 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ለምታመነጨው ኢትዮጵያ ምንም ድርሻ የማይሰጥና ተፈጥሯዊም ሆነ ሕጋዊ መብቴን የሚነጥቅ ነው በማለትም ኢትዮጵያ ትከራከራለች።

ግብፅ በጎርጎሳውያኑ 1959 የተፈረመውና፣ የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት አጥብቃ በመያዝ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርህ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት አላትም ስትል ኢትዮጵያ ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ባስገባችው ደብዳቤ ወቅሳለች።

ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብጽ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንድታገኝና 86 በመቶ የአባይን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይና ኢፍትሃዊ ስምምነት ነው፤ የኢትዮጵያንም ሉዓላዊነትንም ይጥሳል -ትላለች ኢትዮጵያ።

ግብፅ ግድቡ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቴን ይቀንሰዋል እንዲሁም ለእርሻ የሚያስፈልገኝ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በየዓመቱ ይገባኛል ስትል የቆየች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ አሜሪካ በነበረው ድርድር 31 ቢሊዮን ኪዩቡክ ውሃ በዓመት ለመልቀቅ ሃሳብ አቅርባ ነበር።

ግብፅ በተጨማሪ ከምታነሳቸው ቅሬታዎች መካከል ኢትዮጵያ ግድቡን ሙሉ አቅም እየተጠቀመች ድርቅ ቢያጋጥም ችግሩ የሦስቱም አገራት ጉዳይ ነው የሚል አቋም ላይ መድረሷን ነው።

ረዘም ላለ ጊዜ ድርቅ የሚከሰት ከሆነ ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ጥቅምን ለመጠበቅ ዋስትና ልትሰጠን ይገባል በማለትም ግብፅ ትከራከራለች።

ኢትዮጵያ በበኩሏ የግብፅ ሃሳብ በአባይ ወንዝ ላይ ተፈጥሯዊ መብት እንዳይኖራት ወይም ምንም ዓይነት የውሃ ልማት ያልተገነባበት ፍሰት እንዲኖር የሚጠብቅ ነው በማለትም ተችታለች።