ከጉባ እስከ ፀጥታው ምክር ቤት የደረሰው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of water
በ2003 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከትልልቅ የአገሪቱ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው።
ኢትዮጵያ በአገሪቱ ውስጥ ለጀመረቻቸውና የምጣኔ ሀብት እድገት ያመጣሉ ላለቻቸው ፕሮጀክቶች ያለባትን የኃይል አቅርቦት እጥረት ለመፍታት የግድቡን መጠናቀቅ እና ወደ ሥራ መግባት በጉጉት ስትጠብቅ ቆይታለች።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ በጉባ ወረዳ ላይ እየተገነባ የሚገኘው ይህ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ግድብ ግን ለግብፅ እና ለሱዳን ስጋትን ፈጥሮ ቆይቷል።
ግብፅ እና ሱዳን ኢትዮጵያ የአባይ ውሃ ፍሰትን መጠን በግድቡ ግንባታ የተነሳ ትገታዋለች እንዲሁም ይቀንሳል ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በገነባችው ግዙፍ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ "ታላቁ የሕዳሴ ግድብ" የተነሳ የተወዛገቡት ኢትዮጵያ ሱዳን እና ግብፅ በተከታታይ ድርድር እና ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡ የሦስቱንም አገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው ስትል የምትሞግት ሲሆን፣ ግብፅ እና ሱዳን ደግሞ አሳሪ ስምምነት ላይ ተደርሶ ፊርማ እንዲቀመጥ ሲወተውቱ ሰንብተዋል።
ከግድቡ ግንባታ ጀምሮም ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በተደጋጋሚ ውይይት እና ድርድር ሲያደርጉ ቢቆዩም ይህ ነው ከሚባል ስምምነት ላይ አልደረሱም።
በእርግጥ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም ላይ የመርሆዎች ስምምነት ላይ ፊርማቸውን አኑረው ነበር።
ይህን ስምምነት የፈረሙት በኢትዮጵያ በኩል የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲሆኑ፣ በግብፅ በኩል ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ እንዲሁም የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝደንት ኦማር አልበሽር ነበሩ።
ሦስቱ አገራት በደረሱት በዚህ ስምምነት መሠረትም የትኛውም አገር የአባይ ወንዝን ሲጠቀም በሌሎች የተፋሰሱ አገራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አለማስከተሉን ማረጋገጥ አለበት።
በዚህ የመርሆዎች ስምምነት መሰረት ግጭት እና አለመስማማት መፍታትን በተመለከተ፤ የዚህ ስምምነት አተረጓጎምም ወይም አፈጻጸም ተከትሎ የሚከሰት አለመግባባት በመልካም መርህ ላይ ተመስርቶ በውይይት ወይም በድርድር የሚፈታ ይሆናል ይላል።
ይሁን እንጂ ሦስቱ አካላት አለመግባባቱን በምክክር ወይም በድርድር መፍታት ከተሳናቸው በጋራ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ለአገራቱ ርዕሰ ብሔራን ጉዳዩን ሊየቀርቡ ይችላሉ።
መቋጫ ያላገኙ ድርድሮች
ለአባይ ወንዝ 85 በመቶውን ውሃ የምታበረክተው ኢትዮጵያ፤ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቡን መገንባት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል።
ምንም እንኳን ከግብፅና ከሱዳን ተደጋጋሚ ተቃውሞ ቢነሳም ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በሁለት ዙር ግድቡን በውሃ የመሙላት ሂደትን አከናውናለች።
ግድቡን በውሃ የመሙላት ሂደት በምን ያክል ጊዜ ይከናወን የሚለው ቁልፍ ጉዳይ ላይ በአገራቱ መካከል መግባባት ላይ አልተደረሰም።
ግንባታው ከ10 ዓመት በላይ የፈጀው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ እስከ 6450 ሜጋ ዋት ማመንጨት ይችላል ተብሏል።
ሱዳን እና ግብጽ ሦስቱ አገራት በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚያደርጉት ድርድር ከአፍሪካ ሕብረት ውጪ ሌሎች እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ሲወተውቱ ቆይተዋል።
ሁለቱ አገራት ጉዳዮን ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ከመውሰድ ጀምሮ አራተኛ አደራዳሪ እንዲኖር እስከመጠየቅ ደርሰውም ነበር።
ኢትዮጵያ ግን በአደራዳሪነት የአፍሪካ ሕብረትን ብቻ እንደምትቀበል እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ስትገልጽ ቆይታለች።
እስካሁንም በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ታዛቢነት ድርድሩ ሲካሄድ ቢቆይም ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።

ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ድርድር ሰበብ የአባይ ወንዝ ተጠቃሚነቷን የሚገድብ ስምምነት እንደማትቀበል በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።
ግብፅና ሱዳን ድርድሩ ተካሂዶ ከስምምነት ላይ ከመደረሱ በፊት ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ እንዳትሞላ እና ሥራ እንዳትጀምር ቢወተውቱም ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት በ2012 ክረም ወራት ላይ አካሂዳለች።
ይህንንም ተከትሎ በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም የትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ከስምምነት ሳትደረስ ግድቡን መሙላት በመጀመሯ ምክንያት ለአገሪቱ ከሚሰጠው እርዳታ ላይ ቅነሳ እንደሚያደርግ አስታውቆ ነበር።
ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ ሙሌትን ስምምነት ሳይደረስ በማካሄዷ የተነሳ ከአሜሪካ መንግሥት ታገኝ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ አጥታለች።
በዚያው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ያካሄደች ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ግብፅ እና ሱዳን ለፀጥታው ምክር ቤት ያስገቡት ቅሬታ ላይ ምክር ቤቱ ተወያይቷል።
በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ለተከሰተው አለመግባባት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ቀደም ሲል ባልታየ ሁኔታ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ሐምሌ 2013 ዓ.ም ላይ ተሰብስቦ ነበር።
ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመለከተ የፀጥታው ምክር ቤት መወያየቱን እንደማትቀበለው በማስታወቅ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ምንም ዓይነት የደኅንነት ስጋት በሱዳንና በግብፅ ላይ እንደማያስከትል ለምክር ቤቱ አስረድታለች።
ምክር ቤቱ በውይይቱ መደምደሚያ ላይም ጉዳዩ ቀደም ሲል በተያዘበት በአፍሪካ ሕብረት በኩል መቋጫ እንዲያገኝ ውሳኔ ሰጥቷል።
በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ከታችኛው የተፋሰሱ አገራት ጋር ሲደረግ የነበረው ድርድር በአፍሪካ ሕብረት ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ግብፅና ሱዳን በውሀ አያያዝና አለቃቀቅ ላይ አስገዳጅ ስምምነት ይፈረምልን በማለታቸው ኢትዮጵያ ይህ ስምምነት ጥቅሜን ይጎዳል በማለት በመቃወሟ ድርድሩ ሳይቋጭ ቀርቷል።
ጥቂት እውነታዎች ስለሕዳሴ ግድብ
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በስተምዕራብ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በጉባ ወረዳ ይገኛል።
የግንባታው መሠረተ ድንጋይ መጋቢት 24/2003 ዓ.ም በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ነበር የተቀመጠው።
የግድቡን ግንባታ ከሚያከናውኑ ሥራ ተቋራጮች መካከል የጣሊያኑ ሳሊኒ ኢምፕሬጂሎ ይጠቀሳል።
ግድቡን ለመገንባት የሚያስፈልገው ገንዘብ 80 ቢሊየን ብር (ከ4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ) እንደሆነ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት መረጃ ያሳያል።
የዋናው ግድብ ከፍታ 145 ሜትር ሲሆን፤ ርዝመቱ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው።
የዋናው ግድብ ውፍረት የግድቡ ግርጌ ላይ 130 ሜትር ሲሆን፤ የግድቡ ጫፍ ወይም የላይኛው ክፍል ደግሞ 11 ሜትር ነው።
ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፤ ግድቡ የሚሸፍነው የቦታ ስፋት ደግሞ 1 ሺህ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በ2012 ዓ.ም እና 2013 ዓ.ም ሁለት ክረምቶች ለተከታታይ ጊዜ የውሃ ሙሌት አካሂዷል።
በ2012 ዓ.ም ክረምት የግድቡ ቁመት ከባህር ጠለል በላይ 565 ሜትር ላይ ደርሶ 4.9 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ የያዘ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ክረምት ደግሞ መንግሥት የግድቡን ቁመት እና የያዘውን ተጨማሪ ውሃ በቁጥር ባይገልፅም የውሃ ሙሌቱ በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Maxar Technologies via Reuters
ግድቡ የሚገነባበት የአባይ ወንዝ
አባይ ከዓለማችን ረዛዥም ወንዞች በቀዳሚነት ይቀመጣል። 6696 ኪሎ ሜትር እንደሚረዝም መረጃዎች ያሳያሉ።
በአባይ ተፋሰስ ውስጥ አስር አገራት አሉ። እነዚህም ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን፣ ግብፅ እና ደቡብ ሱዳን ናቸው።
ነገር ግን ግብፅ እና ሱዳን አገራት አባይን በብቸኝነት ተከፋፍለው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
በቅኝ ግዛት ወቅት በእንግሊዝ አደራዳሪነት በተደረገ ስምምነት ወንዙን ለመከፋፈል ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
በዚህም ግብፅ 66 በመቶ የውሃ ድርሻ ሲኖራት 22 በመቶ ደግሞ የሱዳን ነው። 12 በመቶ የሚሆነው ውሃው በትነት የሚባክን ሲሆን ኢትዮጵያ ምንም ድርሻ የላትም።














