"ወደድንም ጠላንም ከአንድ ወንዝ ስለምንጠጣ መተባበርን መማር አለብን" ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር)

ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር)

የፎቶው ባለመብት, UN TV

የምስሉ መግለጫ, ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር)

የውሃ፣ መስኖና፣ ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ በኢትዮጵያ፣ በግብጽ እና በሱዳን መካከል የሚደረገው ድርድር ወደተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት መሄድ አልነበረበትም አሉ።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ በሦስቱ አገራት መካከል የሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ሕብረት የበላይ አሸማጋይነት እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ከጸጥታው ምክር ቤት መፍትሔ እንደማይገኝ የጠቆሙት ሚንስተሩ፤ አገራቱ አለመግባባታቸውን መፍታት የሚችሉት በአፍሪካ ሕብረት በኩል መርህ የተከተለ ውይይት ሲያደርጉ ነው ብለዋል።

ግብጽ እና ሱዳን ታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የጸጥታው ምክር ቤት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀው ትላንት ስብበሳ በተካሄደበት ወቅት ንግግር ያደረጉት ኢ/ር ስለሺ "ግድቡን በሚመለከት ይህ የጸጥታው ምክር ቤት የመጨረሻ ስብሰባ እንደሚሆን እጠብቃለሁ" ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት በአግባቡ ውይይቱን እየመራ ሳለ ሱዳን እና ግብፅ ጉዳዮን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ማምጣታቸው ያሳዝናል ያሉት ሚንስትሩ "የጸጥታው ምክር ቤት ከኃላፊነቱ ወጥቶ ለውሃ ጉዳይ መፍትሔ እንዲሰጥ መደረጉ አግባብ አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል።

የግድቡ የውሃ ሙሌት የግድቡ ግንባታ አካል እንደሆነ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ግብጽንም ይሁን ሱዳንን የሚጎዳ ተግባር እንዳልፈጸመች አስምረውበታል።

ከኢ/ር ስለሺ በፊት ለጸጥታው ምክር ቤት ንግግር ያደረጉት የግብጽ እና የሱዳን ተወካዮች፤ የውሃ ሙሌቱ አገሮቻቸው ላይ ተጽዕኖ እንሚያሳድር ገልጸዋል።

ሦስቱ አገራት ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ኢትዮጵያ የግድቡን ሁለተኛ ዙር ሙሌት መጀመሯ የተቃወሙት ግብጽ እና ሱዳን፤ የኢትዮጵያ ውሳኔ ሁለቱን አገራት ችላ ያለ እንዲሁም መርህ ያልተከተለ ነው ብለዋል።

ኢ/ር ስለሺ በበኩላቸው ግብጽ እና ሱዳን ትልልቅ እንዲሁም ትንንሽ ግድብ እና ካናል ሲገነቡ ኢትዮጵያን እንዳላማከሩ ገልጸው፤ "አባይ 70 በመቶ የውሃ ሀብታችን ምንጭ ነው። አባይን አለመጠቀም አንችልም" ብለዋል።

"እኛ እንደ ሱዳን እና ግብጽ ሌላ አማራጭ የለንም። ከአባይ ውጪ አማራጭ የለንም" ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል።

የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው...

ሚንስትሩ በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር ስለ አባይ ሲያብራሩ የኦሮምኛ እና የአማርኛ ምሳሌያዊ አባባሎችን አጣቅሰዋል።

በአማርኛ "የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው" ካሉ በኋላ በኦሮሚኛ "ጎዋን ቢሻን ኬሳ ዳበቴ ዴቦታ" (ሞኝ ውሃ ውስጥ ቆሞ ይጠማል) ያሉት ሚንስትሩ፤ "ግድቡ በኢትዮጵያውያን ደም፣ እምባና ላብ እየተገነባ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

ግብጽ እና ሱዳን በቅኝ ግዛት ወቅት የተደረሰ ስምምነትን እያጣቀሱ ነው ያሉ ሲሆን፤ "ወደድንም ጠላንም ከአንድ ወንዝ ስለምንጠጣ መተባበርን መማር አለብን" ሲሉ ጠንካራ ንግግር አሰምተዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያውያን ከጨለማ የሚወጡበት እንደሆነ ጠቁመው፤ የአርሶ አደሩ፣ የላብ አደሩ፣ የነጋዴው፣ የዳያስፖራው አሻራ አለበት በማለትም ስለ ሕዳሴ ግድቡ ተናግረዋል።

"ግብጽ እና ሱዳን ጉርብትናን እንዲሁም አብሮ ማደግን ሊማሩ ይገባል" ያሉት ኢ/ር ስለሺ፤ የሕዳሴ ግድቡ መገንባት "ተሰደው ከሄዱበት አገር በባዶ እግራቸው የሚባረሩ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት የሚቀይር ነው" ብለዋል።

ኢ/ር ስለሺ ኢትዮጵያውያን የአባይ ውሃ የመጠቀም መብት እንዳላቸው የጸጥታው ምክር ቤት ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መሞላት ሊቀይር የማይችል ፊዚክሳዊ ቀመር መሆኑንም አክለዋል።

ከተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት መካከል በርካቶቹ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት ሊቀጥል እንደሚገባ የገለጹ አሉ።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የጋራ ተጠቃሚነታቸውን አስከብረው በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት አለመግባባቱን እንዲፈቱ ከመከሩ መካከል አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ኬንያ፣ ሩሲያ፣ አየርላንድ፣ ሜክሲሶ እና ሕንድን መጥቀስ ይቻላል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እየተከናወነ ያለው ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን እአአ በ2015 በመሪዎቻቸው አማካኝነት በሱዳን፣ ካርቱም በፈረሙት የመርኅ ስምምነት መሠረት እንደሆነ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት (የ18.5 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ ሙሌት) የጀመረችው ባለፈው ሳምንት ሲሆን ነሐሴ መጨረሻ ላይ እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል።

የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሜርያም አልሳዲግ አልማህዲ (ግራ) እና የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚንሰትር ሳሚ ሹክሪ (ቀኝ)።

የፎቶው ባለመብት, UN TV

የምስሉ መግለጫ, የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሜርያም አልሳዲግ አልማህዲ (ግራ) እና የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚንሰትር ሳሚ ሹክሪ (ቀኝ)።

ግብፅ እና ሱዳ ምን አሉ?

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውይይት እንዲያደርግ የጠየቁት ግብጽ እና ሱዳን በወኪሎቻቸው በኩል ጠንካራ መልዕክት ነው ያስተላለፉት።

ኢትዮጵያ ያለ ሦስትዮሽ ስምምነት የመጀሪያውን እንዲሁም ሁለተኛውንም ዙር የውሃ ሙሌት ማድረጓን ኮንነዋል።

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚ ሹክሪ ግድቡ ያለ ስምምነት መሞላቱ፣ መገንባቱና ወደ ሥራ መግባቱ ከቀጠለ "የግብጽን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት አደጋ ውስጥ የሚከት ነው" ብለዋል።

በአፍሪካ ሕብረት በኩል መፍትሔ ለማግኘት ብንሞክርም አልተሳካም ያሉት ሚንስትሩ፤ ኢትዮጵያ ያለ ስምምነት የታችኛው ተፋሰስ አገራትን በሚጎዳ መልኩ ግድቡን ለሁለተኛ ጊዜ መሙላት ጀምራለች ሲሉ ወንጅለዋል።

ኢትዮጵያ የተናጠል ውሳኔ ላይ ደርሳለች ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተው፤ "ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን ጥሳለች" ሲሉም ከሰዋል።

ይህ አካሄድ የቀጠናው ሰላም፣ መረጋጋትና ደኅንነት እንደሚያውክ ጠቁመው፤ የጸጥታው ምክር ቤት ለአባል አገራቱ ባወጣው መተዳደሪያ መርኅ መሠረት መፍትሔ እንዲያበጅ ጠይቀዋል።

"ዝም አትበሉ። ሕይወት አደጋ ውስጥ ነው" ያሉት የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር፤ ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ያማከለ ስምምት ላይ ሳይደረስ እርምጃ ከመውሰድ እንድትታቀብ ጠይቀዋል።

ድርቅ ቢከሰት ምን እርምጃ እንደሚወሰድ፣ የውሃ መጠን ቢቀንስ ምን እንደሚደረግ ስምምነት ላይ እንዲደርስም አሳስበዋል።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሜርያም አልሳዲግ አልማህዲ ለጸጥታው ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ስለ ድርቅ እና የውሃ መጠን መቀነስ ያነሱትን ስጋት ተጋርተዋል።

"ድርቅን ለመከላከል እና የውሃ እጥረት እንዳይከሰት ስምምነት ላይ መድረስና መተባበር አለብን። ስምምነት ላይ ሳይደረስ የውሃ ሙሌት መጀመር የሱዳንን ሕዝብ አስጊ ሁኔታ ውስጥ ይከታል" ብለዋል።

ግድቡ ቀጠናውን በኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ ጎርፍ በመከላከል ወይም በሌላ መንገድ ጥቅም እንዲሰጥ እንዲሁም የሦስቱንም አገራት ተጠቃሚነት እንዲያስጠብቅ ከተፈለገ የጋራ እንጂ የተናጠል ውሳኔ መወሰድ የለበትም ሲሉም አክለዋል።

የተናጠል የውሃ ሙሌት ውሳኔ የሱዳን ፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ላይ ጫና አለው ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ምክር ቤቱ በሦስቱ አገራት ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ አንዳች መፍትሔ እንዲሰጥ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የየአገራቸውን አቋም ባሰሙበት በሐሙሱ የጸጥታው ምክር ቤት ውይይት ላይ ጎልቶ የተሰማው የአባል አገራት አስተያየት፤ የሕዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት የበላይ አሸማጋይነት ይቀጥል የሚለው ነው።