ሕዳሴ ግድቡ ለሱዳን ምን ይዞ ይመጣል? ከሱዳናዊቷ አንደበት

የሱዳን አርሶ አደር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የሱዳን አርሶ አደር

ሱዳናዊቷ ጋዜጠኛ ዘይነብ ሞሐመድ ሳሊህ፤ ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው አጨቃጫቂው ግድብ ለሱዳን ሊያመጣቸው ስለሚችላቸው በረከቶች ለቢቢሲ በላከችው ደብዳቤ እንደሚከተለው ታስነብባለች።

በዚህ ዓመት ሱዳን ባልተጠበቀ ጎርፍ ተጥለቅልቃ ከ100 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ከ875 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ላይ ደግሞ ጉዳትን አስከትሏል።

ይህ ብቻ አይደለም። የናይል ወንዝ ውሃ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ መኖሪያ መንደሮችን ሙሉ በሙሉ አውድሟል። የኤሌክትሪክ ምሶሶዎችን ደርምሶ ሚሊዮኖችን በጨለማ አስውጧል።

አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ግደብ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ጎርፉ ሱዳን ላይ ይህን ያክል ጉዳት ባልደረሰ ነበር።

በአባይ ወንዝ 85 በመቶ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ፤ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቡን መገንባት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል።

በዚህ ዓመት ደግሞ ግድቡ በውሃ መሞላት ተጀምሯል። ግድቡ በሙሉ አቅሙ ውሃ መያዝ ሲጀምር በአፍሪካ ትልቁ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ኃይል ይሆናል።

ይሁን እንጂ የታችኛው የተፋሰስ አገር የሆነችው ግብጽ፤ ግድቡ የውሃ ድርሻዬን ይቀንስብኛል ስትል ትሰጋለች።

ግድቡ በምን ያክል ጊዜ ይሞላ? የሚለው እስካሁን መግባባት ላይ አልተደረሰም።

የዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ እና ፖሊስ ባለሙያ የሆኑት ሱዳናዊው ሳልማን ሞሐመድ (ዶ/ር)፤ የግብጹ አስዋን ግድብ የጎርፍ ውሃን እንዴት አድርጎ በአግባቡ መጠቀም እንደሚቻል ያሳያል ይላሉ።

“ዘንድሮ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ እኛ ሱዳናውያን ብዙ ሕይወት እና ንብረት አጥተናል። ግብጽን ስንመለከት ግን ምን ችግር አልገጠማቸውም። ምክንያቱም የጎርፉን ውሃ ወደ ትልቁ አስዋን ግድብ ስለሚያስገቡት ነው። እኛም እንደዚህ አይነት ግድብ ቢኖረን አንጎዳም ነበር። የኢትዮጵያ ግድብ ያድነን ነበር” ይላሉ።

ይህ በእንዲህ አንዳለ ሱዳን በናይል ወንዝ ላይ 8 የኃይል ማመንጫ ገድቦች እንዳሏት መዘንጋት የለብንም።

“የእኛ ግድቦች በጣም ትናንሽ ናቸው” ይላሉ ሳልማን ሞሐመድ (ዶ/ር)። “ግብጽ የጎርፍ ውሃውን በአስዋን ግድብ አጠራቅማ በበረሃ ላይ እያካሄደች ላለችው የግብርና ሥራ ውሃን ትጠቀማለች።

የደህንነት ስጋቶች

በቅርቡ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት እየተካሄደው ባለው ድርድር፤ ግድቡ ምን ያህል ውሃ መያዝ አለበት? ምን ያህል መጠን ያለው ውሃ መለቀቅ አለበት? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ሱዳን ወደ ግብጽ ያጋደለች ትመስላለች።

ይህ አቋም በቀድሞ የሱዳን ፕሬዝደንት ኦማር አል-በሽር ይንጸባረቅ ነበር። አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የሱዳን የጦር መኮንኖች ጠንካራ የግብጽ አጋር ናቸው።

በፕሬዝደንት አል-በሽር የሥልጣን ዘመን ወቅት የሱዳን ተደራዳሪ የነበሩት አሕመድ ኤል-ሙፍቲ በግድቡ ላይ የደህንነት ስጋት እንዳላቸው ከዚህ ቀደም ገልጸው ነበር።

ግድቡ በአንዳች ምክንያት ጉዳት ቢደርስበት የሱዳን መዲናን ጨምሮ በቀጠናው ባሉ አገራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ብለው ነበር።

የሱዳን ባለስልጣናት ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችልን ግጭት ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት እየደረጉ ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የሰጡት አስተያየት ግን ሱዳን እያደረገች ካለችው ጥረት ጋር የሚጻረር ነው።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሱዳን እና እስራኤል የሰላም ስምምነት መድረሳቸውን በማስመልከት የሁለቱን አገራት ጠቅላይ ሚንስትሮች በስልክ እያነጋገሩ ባሉበት ወቅት፤ “ግብጽ ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች” ማለታቸው ይታወሳል።

እስከ ባለፈው ሐምሌ ወር ድረስ የሱዳን የሽግግር መንግሥት የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው ያገለገሉት አስማ አብደላ ለሶስቱ አገራት የሚበጀው ምክክር ብቻ ነው የሚል ጠንካራ አቋም ይዘው ነበር።

ሱዳን ግድቡ ጎርፍን ከመቆጣጠር በላይ ሌሎች ጥቅሞችን ይዞ እንደሚመጣ ስለምትረዳ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲኖር ትሻለች።

‘የአፍሪካ የኩራት ምንጭ’

እንደ ዶ/ር ሞሐመድ ከሆነ፤ የኢትዮጵያ ግድብ ሱዳን ከራሷ ግድቦች ከፍ ያለ ኤሌክትሪክ እንድታመነጭ ይረዳታል። ይህም ብቻ ሳይሆን ሱዳን ከኢትዮጵያ ርካሽ የሆነ ኤሌክትሪክ እንድትገዛ ይረዳታል።

ዶ/ር ሞሐመድ ግድቡ ለሱዳን ይዞ የሚመጣው ጥቅም ይህ ብቻ አይደለም ይላሉ።

የሱዳን ገበሬዎች እርሻ የሚያከናውኑት ጥቅምት እና ሕዳር ወራት ላይ መሆኑን ያስታውሳሉ። የአባይ ወንዝ ውሃ ፍሰት ላይ ቁጥጥር ማድረግ የሚቻል ከሆነ ግን ገበሬዎች በዓመት ከአንድ ግዜ በላይ ዘር ሊዘሩ እንደሚችሉ ያስረዳሉ።

በድርቅ ዓመታትም ግድቡ ተጨማሪ ውሃን በመልቀቅ የሚኖረውን የዝናብ ውሃ እጥረት ሊቀርፍ ይችላል።

በሱዳን መዲና ሰዎች ስለ ግድቡ ያላቸው አቋም ምን እንደሆነ ሲጠየቁ ድጋፋቸው ለኢትዮጵያ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

“እንደግፋቸዋለን ምክንያቱም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ርህራሄ አለን” ሲል የ44 ዓመቱ ሳላ ሃሰን ይናገራል። ሳላ የሚኖርበት ኦማዱሩማን ከተማ በቅርቡ በጎርፍ ከተጠቅለቀለቁት ከተሞች አንዷ ነች።

ነዋሪነቱ በካርቱም የሆነው የ37 ዓመቱ ሞሐመድ አሊ ግድቡን እንደ የአፍሪካ ኩራት እና ለበርካቶች የሥራ እድልን ይዞ እንደሚመጣ ፕሮጀክት ነው የሚመለከተው።

“በሱዳን የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ። ግድቡ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያውያኑ ከሱዳናውያን ጋር ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ሥራ የሚሰሩ ይመስለኛል” ይላል።

“ፕሮጅከቱ በርካታ አፍሪካውያንን እንደመጥቀሙ ግድቡን መቶ በመቶ ነው የምደግፈው። በአፍሪካ ቀንድ ያሉ አገራት በርካታ ችግሮችን አሳልፈዋል። እንዲህ አይነት የልማት ፕሮጀክት ያስፈልጋቸዋል” ብሏል ሌላው የካርቱም ነዋሪ።