የህዳሴ ግድብ ድርድርና ለፀጥታው ምክር ቤት የተላኩት ደብዳቤዎች

የህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

በህዳሴ ግድብ ላይ ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር መቋጫ ሳያገኝ ግብፅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቃለች።

ግብፅ ባስገባችው ባለስድሳ ሦስት ገፅ ደብዳቤ ላይ ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ኢትዮጵያ ውሃ ከመሙላት እንድትታቀብና ምክር ቤቱ ጣልቃ በመግባት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብላለች።

ግብፅ ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት የምትጀምር ከሆነ ለቀጠናው ሰላምና ደህንነት ስጋት ስለሚሆን ምክር ቤቱ ይህንን ጉዳይ ቸል እንዳይል እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያሳድርም ጠይቃለች።

ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ የሰጠ ሲሆን፤ ግብፅ ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ የመሙላት ተግባር በቀጠናው እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ሰላምና ደኅንነት ጠንቅ ነው ማለቷ እንዳሳዘነውም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሪቬሬ በላኩት ደብዳቤ ገልፀዋል።

የሦስትዮሽ ስምምነቱ ሳይጠናቀቅ ግብፅ ምክር ቤቱን ጣልቃ እንዲገባ መጠየቋ ግራ የሚያጋባ ቢሆንም "ድርድሩ ፍሬ አልባ እንዲሆን እየሰራች ከነበረችው ግብፅ" የሚጠበቅ ነው ብሏል።

የሦስትዮሽ ስምምነት ከመደረሱ በፊት የግድቡ ሙሌት መጀመር የለበትም በማለት ተቃውሞዋን ያሰማችው ግብፅ ብቻ ሳትሆን ጉዳዩ በመሪዎች ደረጃ እንዲፈታ ያቀረበችው ሱዳን ናት።

ሱዳን ለፀጥታው ምክር ቤት ባስገባችው የአቤቱታ ደብዳቤ ኢትዮጵያ የሦስትዮሽ ስምምነት ከመደረሱ በፊት በሚቀጥለው ወር ግድቡን የምትሞላ ከሆነ በታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚኖሩ ሚሊዮኖች አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ ብላለች።

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤትም የህዳሴ ግድብ ላይ ያሉ ቅራኔዎችን ለማየት በመጪው ሰኞ ቀጠሮ መያዙን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አንድ ዲፕሎማትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

የቪዲዮ ኮንፈረንሱ የተጠራው ግብፅን በመወከል ከአሜሪካ መሆኑንም ዲፕሎማቱ መናገራቸው ተጠቅሷል። በግብፅ ጥያቄ መሰረት ምክር ቤቱ የዝግ ስብሰባ አድርጎ የነበረ ሲሆን ሦስቱ አገራት የላኳቸውንም ደብዳቤዎች ላይ ይፋዊ ያልሆነ ውይይት አድርገዋል ተብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ቃለ አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ ሦስቱ አገራት ያሏቸውን ቅራኔዎች ፈትተው፤ በሰላማዊ መንገድ ድርድሩንም እንዲቋጩ ጥሪ አድርገዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም ሃገራቱ በተፈራረሙት የትብብር መርህ መግለጫ ስምምነት መሠረት ድርድሩን በሰላም እንዲቋጩ መልዕክት ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው።

በተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይም በመገኘት ጉዳዪን ማስረዳት እንደምትፈልግ በቅርቡ የገለፀችው ግብፅ ሦስቱ አገራት በድርድሩ እንዲቀጥሉና ፍትሃዊና ሚዛናዊ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ምክር ቤቱ ጣልቃ በመግባት እንዲያረጋግጥ ጠይቃለች።

ከዚህ ቀደም የህዳሴ ግድብን በይፋ ስትደግፍ የነበረችው ሱዳን፣ በአሁኑ ሰዓት የአቋም ለውጥ እንዳደረገች ለመንግሥታቱ ድርጅት የላከችው ደብዳቤ እንደሚጠቁም አንዳንዶች ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት ያለ ታችኛው ተፋሰስ አገራት መሙላት የምትጀምር ከሆነ የሱዳንን ሮዚየርስ ግድብ ደኅንነት እንዲሁም በታችኛው ተፋሰስ አገራትም ላይ አደጋ ይደቅናል ብላለች ሱዳን።

ሱዳን ከህዳሴ ግድብ የሚለቀቀው ውሃ የሮዚየርስ ግድብን በጎርፍ የመጥለቅለቅ አደጋ እንዳያጋጥመውም ስጋት አለኝ ብላለች። መለቀቅ የሚገባውንም የውሃ መጠንንም አስቀምጣለች።

በሦስቱ አገራት በኩል በድርድሩ ላይ ያለው የፖለቲካ ፈቃደኝነት ተመሳሳይ አይደለም ያለችው ሱዳን፤ የፀጥታው ምክር ቤትም የአገራቱን መሪዎች በመጋበዝ ፖለቲካዊ ፈቃደኝነታቸውንና የቀሩትን ህጋዊ ጉዳዮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እንዲያደርግ ጠይቃለች።

ከሰኔ 2 እስከ 10 ድረስ የተካሄደው የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት እና ዓመታዊ የውሃ አለቃቀቅን በተመለከተው ድርድርም ለአገራቱ መሪዎች እንዲተላለፍ ሱዳን ሃሳብ አቅርባ ነበር።

የሱዳን የውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ያሲር አባስ ለሪፖርተሮች እንደተናገሩት ከ90-95 በመቶ የሚሆኑ የቴክኒካል ጉዳዮች ላይ መስማማት እንደተቻለ፤ ነገር ግን ሕጋዊ ጉዳዮችና የውሃ ክፍፍል ጋር ተያይዞ አሁንም ቢሆን ምንም ስምምነት አለመደረሱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ ድርድሩ ከህዳሴው ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ አልፎ በውሃ ድርሻና አጠቃቀም ላይም እንዲሆንና የኢትዮጵያን የወደፊት በአባይ ውሃ የመጠቀም መብትን የሚገድብ ዓይነት ስምምነት ላይ እንዲደረስ ፍላጎቶች ያሉ በመሆናቸው ድርድሩ ወደፊት ሊሄድ አልቻለም ብላለች።

ግብጽ በጎርጎሳውያኑ 1959 የተፈረመውና፣ የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት አጥብቃ በመያዝ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርህ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ደብዳቤው ጠቅሷል።

ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብጽ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንድታገኝና 86 በመቶ የናይልን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይና ኢፍትሃዊ ስምምነት ነው፤ የኢትዮጵያንም ሉዓላዊነትንም ይጥሳል ብሏል።

ደብዳቤውም ላይ እንደተጠቀሰው ግብጽ በተደጋጋሚ የውሃ ክፍፍል ድርድር ነው በማለት በላይኛው ተፋሰስ አገራት የሚሰሩ ልማቶችን ለማገድ ብትሞክርም በአንፃራዊው ይህ ድርድር የህዳሴ ግድብ ውሃ አለቃቀቅና የግድቡ አሰራርን በተመለከተ እንደሆነ ደብዳቤው ገልጿል።

ደብዳቤው ጨምሮም ግብፅ የውሃ ክፍፍል እንዲካተተት በመጠየቋ ድርድሩ እንዲሰናከል ምክንያት ሆኗል ብሏል ሲል ለድርድሩ አለማሳካት ግብፅን ተጠያቂ አድርጓል።

"የውሃ ክፍፍል ከሆነ ሌሎች የተፋሰሱ አገራትም ሊሳተፉ ይገባ ነበር፤ እነሱም ተጠቃሚዎች ከመሆናቸው አንፃር በውሃ ክፍፍሉ ሦስቱ አገራት ብቻ ሊወስኑላቸው አይችሉምም" ሲልም የግብፅን አካሄድ አግላይ ነው ሲል ተችቷል።

ግብፅ ኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመፍጠር ለማንበርከክና ምክር ቤቱንም በተሳሳተ መንገድ ለመውሰድ እየሞከረች ነው ያለችው፤ ከሰሞኑ አገራቱ የደረሱባቸው ስምምነቶችም ኢትዮጵያ ምን ያህል ግድቧም ቢሆን ልዩነቶችን ለማጥበብ እየሰራች መሆኑን ማሳያ እንደሆነ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በላከችው ደብዳቤ ላይ ጠቅሳለች።

ሦስቱ አገራት ለፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ሲያስገቡ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ግብፅ ከወር በፊት የምክር ቤቱን መተዳደሪያ አንቀፅ 35 በመጥቀስ ያለው ሁኔታ የዓለምን ደኅንነትና ሰላም የሚያደፈርስ ነው ብላ ነበር።

ግብፅ በዓመታት ውስጥ ሲደረግ የነበረው ድርድር ፍሬ አለማፍራቱንና ዋሽንግተን ውስጥ በአሜሪካና በዓለም ባንክ አሸማጋይነት ሲካሄድ የነበረው ድርድርም የሦስቱን አገራት ጥቅም ያማከለ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውድቅ እንዳደረገው ጠቅሳለች።በቅርቡም የነበረው ድርድር የፈረሰው ከኢትዮጵያ በኩል ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት ባለመገኘቱ እንደሆነም ደብዳቤው አትቷል።

ኢትዮጵያ ያለሦስትዮሽ ስምምነት የግድቡን ሙሌት እጀምራለሁ ማለቷም ከአምስት ዓመታት በፊት የተፈራረሙትን የህዳሴ ግድብ የትብብር መግለጫ ስምምነትም የሚጥስና የታችኛው ተፋሰስ ሃገራትንም የሚጎዳ ነው ብላለች። የግድቡ ሙሌት መጀመር ለግብፅ ህዝብ አደጋ እንደሚጋረጥም ደብዳቤው ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት መጀመር የለባትም የሚል አቋም የያዘው ደብዳቤው በይዘትም በቅርቡ ከተላከው ጋር ተመሳሳይ ያለው ሲሆን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ የትብብር መግለጫ ስምምነቱን እንድታከብርና ወደ ድርድሩም እንድትመለስ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ነው። ቀደም ያለው ባለአስራ ሰባቱ ገፅ የግብፅ አቤቱታ ኢትዮጵያ ከግድቡ ሙሌትም እንድትታቀብ ይጠይቃል።

ኢስቶኒያ የፀጥታ ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር ከመሆኗም ጋር ተያይዞ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳሜህ ሹክሪህ የኢስቶኒያ አቻቸውንም ኡርማስ ሬይንሳሉን ደውለው እንዳነጋገሩ ዘገባዎች አመልክተዋል።

ኢትዮጵያም በበኩሏ ለዚህ ምላሽ የሰጠች ሲሆን የግድቡን ውሃ ሙሌት ለመጀመር የግብፅ አዎንታዊ ሁኔታን ማግኘት አስገዳጅ እንዳልሆነ በላከችው ደብዳቤ ጠቅሳለች።

ለድርድሩ መቆም እንዲሁም መጓተት ግብፅ ምክንያት እንደሆነች አመልክታለች። ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ ሙሌት በማካሄድም እንደምትጸና አስታውቃለች። ሚያዝያ መጀመሪያ ላይ ባቀረበችውም ዕቅድ መሰረት በመጀመሪያው ዓመት 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትርና፣ በሁለተኛው ዓመትም 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃም ለመሙላት ማሰቧንም በደብዳቤው ላይ አካታለች።

ይህም ውሃ በታችኛው ተፋሰሰስ አገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስና የመጀመሪያ ደረጃ የግድቡ የውሃ ሙሌት መመሪያም የተወሰደው ሦስቱ አገራት ከተስማሙበት የግድብ ትብብር መግለጫ ስምምነት መሆኑንም አፅንኦት ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ የግብፅን ፈቃድ የማግኘት ህጋዊ ግዴታ እንደሌለበት ያሰመረው ደብዳቤው ግብፅ የግድቡን ድርድር ለማሰናክለ እንደምትሰራ ተጠቅሷል።

ደብዳቤው አክሎም ኢትዮጵያ የአባይን ውሃን በፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ የመጠቀም እንጂ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራትን በፍጹም የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላትም አረጋግጧል።

የግብፅ ለዘመናት የዘለቀ ተጠቃሚነቷን የጠቀሰው ደብዳቤው የአስዋንን ግድብ ስትገነባ ኢትዮጵያን ሳታማክር ሲሆን ግብፅ ይህንኑ አካሄድ በመቀጠል የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳለም አፅንኦት ሰጥቷል።

ይህ ታሪካዊ ስህተት መስተካከል አለበት ያለው ደብዳቤው በተለይም ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ያለ መብራት እንዲሁም በድህነት ውስጥ ላሉባት ኢትዮጵያ ግድቡ ያለውን ጠቀሜታም በዝርዝር ተጠቀምጧል።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ኢትዮጵያ የግድቡን ወሃ ሙሌት ለማካሄድ ያላትን አቋም እንዲደግፉም ደብዳቤው ጥሪ ቀርቧል።

ግብፅ ከምታነሳቸው ቅሬታዎች መካከል ኢትዮጵያ ግድቡን ሙሉ አቅም እየተጠቀመች ድርቅ ቢያጋጥም ችግሩ የሦስቱም አገራት ጉዳይ ነው የሚል አቋም ላይ መድረሷን ነው።

ረዘም ላለ ጊዜ ድርቅ የሚከሰት ከሆነ ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ጥቅምን ለመጠበቅ ዋስትና ልትሰጠን ይገባል በማለትም ግብፅ ትከራከራለች።

ኢትዮጵያ በበኩሏ የግብፅ ሃሳብ በአባይ ወንዝ ላይ ተፈጥሯዊ መብት እንዳይኖራት ወይም ምንም ዓይነት የውሃ ልማት ያልተገነባበት ፍሰት እንዲኖር የሚጠብቅ ነው በማለትም ተችታለች።