ግብጽ የተባበሩት መንግሥታት በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ ጠየቀች

Ministry of Water, Irrigation and Energy of Ethiop

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Water, Irrigation and Energy of Ethiop

ግብጽ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያና ከሱዳን ጋር በሚደረገው ድርድር ጣልቃ ገብቶ እንዲያሸማግላት ጠየቀች።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በርቀት በቪዲዮ አማካይነት ለቀናት ሲካሄድ በሰነበተው የሦስቱ አገራት ድርድር ላይ በርከት ባሉ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መደረሱ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም በቀሪ ጉዳዮች ላይ ልንግባባ አልቻልንም ያለችው ግብጽ ጉዳዮን ወደ ተባበሩት መንግሥታት ወስዳዋለች።

ግብጽ ጉዳዩን በይፋ ወደ ጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ከመውሰዷ በፊት የኢትዮጵያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በግብጽ እየተከተለችው ያለው አካሄድ በድርድሩ ችግሮችን ለመፍታት ሳይሆን በተለያዩ አቅጣጫዎች በኢትዮጵያ ላይ ጫናን ማሳደር እንደሆነ ባለፈው ሳምንት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸው ነበር።

ጨምረውም "በአንድ በኩል ከእኛ ጋር ይደራደራሉ በሌላ በኩል ደግሞ ወደተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት በተለይም ወደ ጸጥታ ምክር ቤት ጉዳዩን ለማቅረብ ጥረት ያደርጋሉ" በማለት "አንድ እግራቸውን ኒው ዮርክ (የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት) ሌላ እግራቸውን ድርድሩ ውስጥ አድርገው ቀጥለዋል" ብለዋል።

ትናንት የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው "እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስነው ኢትዮጵያ በያዘችው አውንታዊ ያልሆነ አቋም ምክንያት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተደረገ ያለው ድርድር በመጓተቱ ነው" ሲል ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የተወሰደበትን ምክንያት ገልጿል።

በተቃራኒው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ማክሰኞ ዕለት እንደተናገሩት ግብጽ በያዘችው ግትር አቋም ድርድሩ ወደተፈለገው ደረጃ ሊሄድ እንዳልቻለ ገልጸው፤ በዚህም ግብጽ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርህ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ ብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳለ ተናግረው ነበር።

በድርድሩ ላይ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌትና ዓመታዊ አለቃቅና አስተዳደርን የተመለከተ ሰነድ ያቀረበች መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ በቀረበው ሰነድ ላይ ውይይት አድርጎ ውጤት ከማምጣት ይልቅ ድርድሩን የማፋረስና ኢትዮጵያን የማጠልሸት ሥራዋን ቀጥላለች በማለት ወንጅለዋል።

"ድርድር በባህሪይው ሰጥቶ መቀበል ነው። እኛ እየተደራደርን ያለነው ምንም መስጠት ከማይፈልጉ ነገር ግን ሁሉንም መውሰድ የሚፈልጉ ኃይሎች ጋር ነው።"

በምዕራብ ኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው ግዙፉ የህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ያልተጠናቀቀ ቢሆንም በመጪዎቹ ሳምንታት ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ ውሃ የመሙላት ሥራ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ መንግሥት ማሳወቁ ይታወሳል።

ከወራት በፊት የግድቡ ውሃ አሞላልና ቀጣይ ሥራን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ዋሽንግተን ውስጥ ተከታታይ ሲደረጉ የነበሩት ድርድሮች ውጤት ሳያመጡ መጠናቀቃቸው የሚታወስ ነው።

ግብጽ ኢትዮጵያ በሐምሌ ወር ግድቡን በውሃ የመሙላት ሥራውን እንደምትጀምር ካሳወቀች በኋላ በተካሄዱት ንግግሮች ሁሉ ስምምነት ሳይደረስ ውሃ ሙሌት እንዳይጀምር ግፊት ስታደርግ ቀይታለች።

የውጭ ጉዳይ መኒስትሩ አቶ ገዱ እንዳሉት ግብጾች የተለያየ መንገድ ፈልገው ድርድሩን ለማቋረጥ ሃሳብ እንዳላቸው አመልክተው "ለመስማማት የፈለግነውን ስጡን ይላሉ። ካልሰጣችሁን አንስማም ይላሉ። የሚፈልጉትን በሙሉ ካላገኙ አንስማማም ይላሉ። ካልተስማማን ደግሞ ውሃ አትሞሉም" የሚል አቋም እንዳላቸው ገልጸው ነበር።

አቶ ገዱ ኢትዮጵያ የአባይን ውሃን በፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ የመጠቀም እንጂ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራትን በፍጹም የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላትም አረጋግጠዋል።