"እየተካሄደ ያለው ድርድር የተጓተተው ግብፅ የቅኝ ግዛት ስምምነቱን ሙጥኝ በማለቷ ነው"

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲካሄድ የነበረው ድርድር ቀጥሎ ለአራተኛ ቀንም በትናንትናው ዕለት ተካሂዷል።
በትናንትናው ዕለትም የግብፅ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ምላሸ ሰጥቷል።
ቃለ አቀባዩ የሦስቱ አገራት ድርድር እንደተፈለገ መካሄድ ያልቻለው በኢትዮጵያ ችግር ነው ማለታቸው ውንጀላ መሆኑን የገለፀው ሚኒስቴሩ፤ በተቃራኒው ስምምነቶቹ ውጤታማ መሆን ያልቻሉት ግብፅ የቅኝ ግዛትን የውሃ ስምምነት ሙጥኝ ብላ በመያዟ እንደሆነ ገልጿል።
ይህ ስምምነት ኢትዮጵያንም ሆነ የላይኛው ተፋሰስ አገራትን የተፈጥሮና ተገቢ የውሃ መብታቸውን የሚከለክል ነው ብሏል።
ሚኒስቴሩ አክሎም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብንም ግራ ለማጋባትም ሆነ ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ስምምነትን እንድትቀበል የሚደረግ ጫና፣ ግፊም ሆነ ዘመቻ ተቀባይነት የለውም ብሏል።
ኢትዮጵያ በሌለችበት የተፈረመ ስምምነት እንዲሁም ሕጋዊ ከሆነው የአባይን ወንዝ መጠቀም መብት ለመካለከል ግብፅ የምትሄድበት መንገድንም እንደሚቃወም አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ከሰሞኑ የተደረጉ ድርድሮችን በተመለከተም በሱዳን ሊቀ መንበርነት አገራቱ የውሃ ሙሌቱን በተመለከተና የግድቡን አጠቃላይ አሰራርን በተመለከተ ቴክኒካዊ ውይይቶች ማካሄዳቸውን ጠቅሶ፣ ድርድሩ ከናይል ወይም አባይ ውሃ ክፍፍል ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ አስታውቋል።
በመግለጫውም የግድቡን የመጀመሪያ ደረጃ ሙሌት እንዲሁም አጠቃላይ የህዳሴ ግድብ አሰራርን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከታችኛው ሁለት የተፋሰስ አገራት ጋር በመርሆች ስምመነት መመሪያዎችና ሕጎች እንደምትመራ አስታውቋል።
አገራቱ የሚያደርጓቸው ድርድሮች ቀናና ግልፅ በሆነ መንገድ ማካሄድ ከተቻለ ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚችሉም ተስፋ እንደሰነቀም መግለጫው ጠቁሟል።
አገራቱ የግድቡን ደኅንነት ሕጎች፣ አካባቢያዊና ማኅበራዊ ግምገማ ጥናት እንዲሁም መመሪያዎችና ሕጎች አጠቃቀም ላይም የጋራ መግባባት ላይ እንደደረሱ ገልፆ፤ ድርድሩ በነገው ዕለትም [ሰኞ] የሚቀጥል ሲሆን በግብፅ የሊቀመንበርነት የሚካሄድ ይሆናል።












