የህዳሴው ግድብ ድርድር ወደ ማይታረቅ ቅራኔ ደረጃ ደርሶ ይሆን?

የህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

ኢትዮጵያ የሦስትዮሽ ስምምነት ከመደረሱ በፊት የግድቡን ውሃ ሙሌት የምትጀምር ከሆነ ጉዳዩን ወደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት እንወስደዋለን ስትል የነበረችው ግብፅ በባለፈው ሳምንት አርብ ምክር ቤቱ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቃለች።

ግብፅ ባስገባችው የስልሳ ሦስት ገፅ ደብዳቤ ላይ ሦስቱ አገራት በድርድሩ እንዲቀጥሉና ፍትሃዊና ሚዛናዊ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ምክር ቤቱ ጣልቃ በመግባት እንዲያረጋግጥ ጠይቃለች።

ምክር ቤቱ ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ኢትዮጵያ ውሃ ከመሙላት እንድትታቀብና ጣልቃ በመግባት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብላለች። በተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይም በመገኘት ጉዳዪን ማስረዳትም እንደምትፈልግ በደብዳቤው ላይ ገልፃለች።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት አርብ ከአሶሺየትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ግድቡን ለመሙላት የሦስትዮሽ ስምምነት አስገዳጅ እንዳልሆነና በታቀደለትም የክረምት ወቅት የመጀመሪያ ደረጃ ሙሌት ይካሄዳል በማለት አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ግብጽ "በወንዛችን ላይ የሚደረገውን ልማት ለመቆጣጠር እየሞከረችም ነው" በማለት ወቅሰዋል።

ስምምነት ላይ መድረስ ፈታኝ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ገዱ " ስምምነት ላይ መድረስ ባንችልም በያዝነው ዕቅድ መሰረት የግድቡን የውሃ ሙሌት እንጀምራለን። የሌሎቹን ምርቃት የምንጠብቅ ከሆነ ግድቡ ለዓመታት ምንም ሳንሰራበት ጥቅም አልባ ነው የሚሆነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ አንፈቅድም" ብለዋል።

አክለውም "ኢትዮጵያ በራሷ ውሃ ለማልማት ግብጽና ሱዳንን አትለምንም" ያሉት አቶ ገዱ ግድቡን በራሷ ወጪ መስራቷንም ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አክለውም ግድቡ የቀጠናው ትብብር ማጠናከሪያ ነው እንጂ፤ ውዝግብና ጦርነት መጎሰሚያ መሆን አይገባውም ብለዋል።

"ግብጽውያን በህዳሴ ግድብ ላይ የያዙትን ፕሮፓጋንዳ አጠናክረውታል። የፖለቲካ ቁማርም ነው እየተጫወቱ ያሉት። አንዳንዶቹም ጦርነት እንዲነሳ የሚጠብቁ ይመስላሉ" ብለዋል።

ግብጽ ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ የመሙላት ተግባር በቀጠናው እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ሰላምና ደኅንነት ጠንቅ ነው ማለቷ እንዳሳዘነውም በተጨማሪ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት በላከው ደብዳቤ ገልጿል።

የሦስትዮሽ ስምምነቱ ሳይጠናቀቅ ግብጽ ምክር ቤቱን ጣልቃ እንዲገባ መጠየቋ ግራ የሚያጋባ ቢሆንም "ድርድሩ ፍሬ አልባ እንዲሆን እየሰራች ከነበረችው ግብጽ" የሚጠበቅ ነው ብሏል።

የግድቡ ድርድር ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው እየጣረች እንደሆነ ያተተው መግለጫው ግብጽ ቀጠናዊ እንዲሁም አህጉራዊ መፍትሄዎችን ያልሻተችውና የዘለለችው በዚሁ ምክንያት ነው ይላል።

ግብጽ በጎርጎሳውያኑ 1959 የተፈረመውና፣ የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት ሙጥኝ ብላ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርህ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ደብዳቤው ጠቅሷል።

ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብጽ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንድታገኝና 86 በመቶ የናይልን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይና ኢፍትሃዊ ስምምነት ነው።

ግብፅጽ ድርድሩን ምክንያት በማድረግ ይህንን ስምምነት ኢትዮጵያ እንድትቀበል ኢትዮጵያ ላይ ጫና እያደረገች ሲሆን ይህ በማንኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የለውም ብላለች ኢትዮጵያ።

ለዓመታት ሲካሄድ የነበረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ፍሬ ሳያፈራ ባለፈው ሳምንት ተቋርጧል። ከሰኔ 2-10 ድረስ የተካሄደው የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት እና ዓመታዊ የውሃ አለቃቀቅን በተመለከተ በበይነመረብ የተካሄደው የቪዲዮ የሦስትዮሽ ድርድርም መቋጫ ሳያገኝ ቆሟል።

ከሰሞኑ በህዳሴው ግድብ ቁልፍ የሕግ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ባለመደረሱ፣ ጉዳዩ ለአገራቱ መሪዎች እንዲተላለፍ ሱዳን ሃሳብ ማቅረቧን አልጀዚራ ዘግቧል።

የሱዳን የውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ያሲር አባስን ዋቢ አድርጎ አልጀዚራ እንደዘገበው ሦስቱ አገራት በድርድሩ ስምምነት ላይ መድረስ አቅቷቸዋል ብሏል። የሦስትዮሽ ድርድሩ ለጊዜው የተቋረጠው ሱዳን ጉዳዩ በመሪዎች ደረጃ እንዲታይ ሃሳብ ማቅረቧን ተከትሎ እንደሆነም የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በላከው ደብዳቤ አስረድቷል።

ያሲር አባስ ለሪፖርተሮች እንደተናገሩት ከ90-95 በመቶ የሚሆኑ የቴክኒካል ጉዳዮች ላይ መስማማት እንደተቻለ፤ ነገር ግን ሕጋዊ ጉዳዮች ላይ አሁንም ቢሆን ምንም ስምምነት አለመደረሱን ተናግረዋል።

በተለይም ከውሃ ክፍፍል ጋር በተገናኘ አገራቱ መስማማት ስላቃታቸው በመሪዎች ደረጃ ሊፈታ ይገባል እንደተባለም ዘገባው ጨምሮ አስነብቧል።

የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርም በበኩሉ ተመሳሳይ መግለጫ ያወጣ ሲሆን በቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ስምምነት ቢደረስም በውሃ ሙሌት እና አለቃቅ የሕግ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ልዩነቶች እንዳሉ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ከሰሞኑም ድርድሩ ከህዳሴው ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ አልፎ በውሃ ድርሻና አጠቃቀም ላይም እንዲሆንና የኢትዮጵያን የወደፊት በአባይ ውሃ የመጠቀም መብትን የሚገድብ ዓይነት ስምምነት ላይ እንዲደረስ ፍላጎቶች ያሉ መሆናቸውንም ጠቁሟል።

ደብዳቤውም ላይ እንደተጠቀሰው ግብጽ በተደጋጋሚ የውሃ ክፍፍል ድርድር ነው በማለት በላይኛው ተፋሰስ አገራት የሚሰሩ ልማቶችን ለማገድ ብትሞክርም በአንፃራዊው ይህ ድርድር የህዳሴ ግድብ ውሃ አለቃቀቅና የግድቡ አሰራርን በተመለከተ እንደሆነ ደብዳቤው ገልጿል።

"የውሃ ክፍፍል ከሆነ ሌሎች የተፋሰሱ አገራትም ሊሳተፉ ይገባ ነበር፤ እነሱም ተጠቃሚዎች ከመሆናቸው አንፃር በውሃ ክፍፍሉ ሦስቱ አገራት ብቻ ሊወስኑላቸው አይችሉምም" ብሏል።

የህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመፍጠር ለማንበርከክና ምክር ቤቱንም በተሳሳተ መንገድ ለመውሰድ እየሞከረች ነው ያለችው ኢትዮጵያ ከሰሞኑ የደረሱባቸው ስምምነቶችም ኢትዮጵያ ምን ያህል ግድቧም ቢሆን ልዩነቶችን ለማጥበብ እየሰራች መሆኑን ማሳያ እንደሆነም ደብዳቤው ጠቅሷል።

የግብፅጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ በበኩላቸው ግብጽ ጉዳዩን ወደ ምክር ቤቱ የወሰደችው የዓለም አቀፉን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንጂ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለማስጣልም ሆነ ሌላ እርምጃ እንዲወሰድባት አይደለም ማለታቸውን ኢጅፐት ኢንዲፔንደንት ዘግቧል።

የ150 ሚሊዮን ግብጻውያንና ሱዳናውያን ህይወት ላይ ተፅእኖ የሚያደርስ ከመሆኑ አንፃር የግድቡን ቀውስ በኃላፊነት የመፍታቱ ጉዳይ የምክር ቤቱ ነውም ብለዋል።

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ስምምነቱ ሳይፈረም ግድቡን አልሞላም ትበል እንዲሁም ወደ ስምምነቱም ትመለስ ብሏል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አንዳርጋቸው ግብጽ ጉዳዩን ወደ ምክር ቤቱ የወሰደችው ከግድቡ ድርድር ለማምለጥ ነው ማለታቸውን እንደማይስማሙና አሁንም ቢሆን በድርድሩ እንደሚቀጥሉ ሳሜህ ምላሽ መስጠታቸውን ኢጅፕት ኢንዲፔንድንት ዘግቧል።

ዘገባው አክሎም ኢትዮጵያ ስምምነቱ ከመደረሱ በፊት የመጀመሪያ ዙር የግድቡን ውሃ ሙሌት የማትጀምር ከሆነ በድርድሩ እንደሚሳተፉ ማስታወቃቸው ተዘግቧል።

ሰኞ ዕለትም የሱዳኑ የውሃና የመስኖ ሚኒስትር ያሲር አባስ በሰጡት መግለጫ የህዳሴ ግድብ መቋጨት የሚችለው በሦስትዮሽ ድርድር መሆኑን አስታውቀው ሱዳን በድርድሩ ተስፋ እንደምታደርግ አስምረዋል።

ሁኔታው ከተባባሰ ወደ ግጭት እንደሚያመራ የጠቆሙት ሚኒስትሩ "ድርድሩ ብቻ ነው ተስፋው ብለዋል" አክለውም "የግድቡ ሙሌትን ለመጀመር ስምምነት ላይ ሊደረስ ይገባል ሱዳንም ይህንን ለመጠየቅ መብቱ አላት" ብለዋል።

በግብጽ መንግሥትን በሚደግፉ ሚዲያዎችም ላይ ኢትዮጵያ ይህንን አቋሟን እንድትለውጥ ግብፅ እርምጃ መውሰድ አለባትም ሲሉ ተሰምተዋል። የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ግብጽ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደማትፈልግና ፖለቲካዊ መፍትሔን እንደምትሻ ጠቁመው ኢትዮጵያም ግድብ የመገንባት መብቱ አላት ብለዋል።

"በባለፉት ስድስት ዓመታት ግብጽ ወታደራዊ እርምጃ እንወስዳለን የሚል ፍንጭ አላሳየችም" ያሉት ሚኒስትሩ ነገር ግን ምክር ቤቱ ኢትዮጵያን ወደ ድርድሩ የማያመጣት ከሆነና የግድቡ ሙሌት ከተጀመረ ግን " ምን አይነት እርምጃ እንደምንወስድ በዚያን ጊዜ ግልፅ አድርገን እናሳውቃለን። ሁኔታውን ዝም ብለን አናይም" ብለዋል።

በግብጽም ጥያቄ መሰረት የአረብ ሊግ አገራት ጉዳዩን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አማካይነት ትላንት ማክሰኞ መወያየታቸው የተሰማ ሲሆን ግብጽ ግድቡን በተመለከተ ያቀረበችው ሃሳብ በአንዳንድ አባል አገራት ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ ተሰምቷል።

በውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ የሚካሄደው ድርድር ወደ መሪዎች ይመራ የሚለው መቋጫ ያላገኘ ሲሆን ኢትዮጵያ በበኩሏ ምንም አይነት ስምምነት ላይ ይደረስም አይደረስ የመጀመሪያ ደረጃ የግድቡ ውሃ ሙሌት ሐምሌ ወር ላይ የመጀመር እቅድ አላት።

ይሄ ጉዳይ ግን በግብጽ ብቻ ሳይሆን ለግብጽ ወግናለች ተብላ ስትወቀስ በነበረችው አሜሪካም ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም። ከሰሞኑም የአሜሪካ ብሔራዊ ፀጥታ ምክር ቤት ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ ሙሌት ከመጀመሯ በፊት የሦስትዮሽ ስምምነት ሊደረስ ይገባል የሚል የማሳሰቢያ መልዕክት በትዊተር ገፁ ላይ አስፍሯል።

"257 ሚሊዮን የሚሆን የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝብ ኢትዮጵያ ጠንካራ አመራር እንድታሳይ ይጠብቃል። ይህ ማለት ፍትሃዊ የሆነ ስምምነት ነው ብሏል። በህዳሴ ግድብ ላይ ያሉ የቴክኒክ ጉዳዮች መፍትሔ አግኝተዋል፤ አሁን ደግሞ የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ስምምነት ላይ የሚደረስበት ጊዜ ሊሆን ይገባል" ብሏል በትዊተር ገፁ።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ለዚህ በሰጠው ምላሽ "ግድቡን አስመልክቶ ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች ተቋማት የሚሰጡ መግለጫዎች ወገንተኝነትን አለማሳየታቸውን እንዲሁም የሚደረጉ ድርድሮች ላይ እክል እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ ያሻቸዋል። ፍትሃዊ የሆኑ መግለጫዎች መሆን አለባቸው አለበለዚያ መግለጫ ከመስጠት መቆጠብ ያስፈልጋል" ብሏል።

የግብጽ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ቃል አቀባይም ከሰሞኑ ድርድሩ ፍሬ አልባ ነው ሲሉ የተቹ ሲሆን ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የኢትዮጵያ "ግትርነት" ነው በማለት ተችተዋል።

ቃለ አቀባዩ ኢትዮጵያ እያቀረበችው ያለው ሰነድ ቴክኒካልና ሕጋዊ መርሆችን የሚጥስ እንዲሁም የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ፍላጎትንም ሆነ መብታቸውን የሚጋፋ ነው በማለት ወቅሰዋል።

ሰነዱንም "የሚረብሽ" ያሉት ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ በድርድሩ ስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት የላትም ማለታቸውን የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በተደጋጋሚ ግብጽ የቅኝ ግዛት ውሎችን ሙጥኝ እንዳለችና ኢ-ፍትሃዊና አግላይ የሆነውን ስምምነት ተቀባይነት እንዲያገኝ ጫና እያደረገች ነው በማለትም ትወቀሳለች።

ባልነበረችበት የተፈረመ ስምምነት ለናይል ወንዝ 77 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ለምታመነጨው ኢትዮጵያ ምንም ድርሻ የማይሰጥና ተፈጥሯዊም ሆነ ሕጋዊ መብቴን የሚነጥቅ ነው በማለትም ኢትዮጵያ ትከራከራለች።

ግብጽ ከምታነሳቸው ቅሬታዎች መካከል ኢትዮጵያ ግድቡን ሙሉ አቅም እየተጠቀመች ድርቅ ቢያጋጥም ችግሩ የሦስቱም አገራት ጉዳይ ነው የሚል አቋም ላይ መድረሷን ነው።

ረዘም ላለ ጊዜ ድርቅ የሚከሰት ከሆነ ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ጥቅምን ለመጠበቅ ዋስትና ልትሰጠን ይገባል በማለትም ግብጽ ትከራከራለች።

ኢትዮጵያ ያለ ታችኛው ተፋሰስ አገራት ስምምነትም ግድቡን ለመሙላት መወሰኗም ሁለቱን አገራት የማስገደድ ውሳኔ ነው ብለውታል ቃለ አቀባዩ።

የሦስትዮሽ ስምምነቱ እልባት ሳያገኝ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዙር የግድቡን ውሃ ሙሌት ብትጀምርም አለመረጋጋቶችና ግጭቶች በቀጠናው እንደሚከሰትም ከሰሞኑም አስጠንቅቃለች።

ይህንንም ተከትሎ ከሰሞኑም ኢትዮጵያውያን #ግድቡ የኔ ነው በሚል በትዊተር ላይ ዘመቻም ጀምረዋል። ኢትዮጵያ ግድቡን በመሙላት እንድትቀጥልበትም ድጋፋቸውን ለግሰዋል።

የአሜሪካ፣ አውሮፓ ሕብረትና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርን አገራቱ በበይነ መረብ አማካይነት በርቀት የሚያደርጉትን ድርድር እየታዘቡት ይገኛሉ።

የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች እንዲሁም የሕግ እና የውሃ ጉዳይ የቴክኒክ ባለሞያዎች በዋሽንግተን ዲሲ ሲደራደሩ በነበረበት ወቅት በዓመታት የተራዘመ ድርቅ እንዲሁም በተራዘመ ዓመታት አነስተኛ የውሃ ፍሰት ላይም መሰረታዊ መግባባት ተደርሷል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ያለምንም ውጤት መቋረጡ ይታወሳል።

በወቅቱም ግብጽ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቴን ይቀንሰዋል እንዲሁም ለእርሻ የሚያስፈልገኝ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በየዓመቱ ይገባኛል ስትል የቆየች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ 31 ቢሊዮን ኪዩቡክ ውሃ በዓመት ለመልቀቅ ሃሳብ አቅርባ ነበር። ነገር ግን አሜሪካ በበኩሏ 37 ቢሊዮን ኪዩብክ ሜትር እንዲለቀቅ መጠየቋ ተነግሮ ነበር።

ኢትዮጵያ ወንዙ በግድቡ ስፍራ እንደሚኖረው ዓመታዊ የፍሰት መጠን ከ4 -7 ዓመታትን በሚወስድ የሙሌት ደረጃ ግድቡን የመሙላት እቅድን ብታቀርብም ግብፅጽ በበኩሏ ጥቅሜን የሚጋፋ ነው በማለት ከ12 እስከ 21 ዓመታት መውሰድ አለበት ትላለች።

ኢትዮጵያ ዋሽንግተን ሲካሄድ የነበረውንም ድርድር ያቋረጠችበት ምክንያት በግብጽ ፍላጎት ታዛቢ እንዲሆኑ የገቡት አሜሪካና የዓለም ባንክ ለግብጽ ከመወገን አልፈው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ላይ ጫና ለማሳደር ሞክረዋል በማለት ኢትዮጵያ መውቀሷ የሚታወስ ነው።

አሜሪካ፣ የዓለም ባንክ ከግብጽ ጎን ቆመው ነበር በተባለው በዚህ ድርድር ላይ ከመጀመሪያው ሙሌት በኋላ ኢትዮጵያ ለምትጠቀመው ውሃ ለግብጽ የተጠራቀመ የውሃ ጉድለት ማካካሻ እንድትሰጥ የሚያስገድድ እንደሆነም ተገልጾ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ የግብጽ ሃሳብ በአባይ ወንዝ ላይ ተፈጥሯዊ መብት እንዳይኖራት ወይም ምንም ዓይነት የውሃ ልማት ያልተገነባበት ፍሰት እንዲኖር የሚጠብቅ ነው በማለትም ትተቻለች።

የህዳሴ ግድብ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ 90 በመቶ የተጠጋ የሲቪል ሥራው፣ 44 በመቶ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው እና 20 በመቶ የብረታ ብረት ሥራው እና አጠቃላይ የግንባታው ሂደት ወደ 75 በመቶ መድረሱም ተገልጿል።